የኢትዮጵያን የቡና ምርት ለቻይና ገበያ በስፋት ለማስተዋወቅ እና ቀጥተኛ የንግድ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ የልዩ ቡና የንግድ ማዕከል በቻይና ሁናን ግዛት፣ በይፋ ተመርቋል።
ይህ የማዕከል ምረቃ የተካሄደው በሁለቱ አገራት መካከል የተካሄደውን የ”ቻይና-ኢትዮጵያ የቡና ኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር ኮንፈረንስ” ተገን በማድረግ ነው።
በአሁኑ ወቅት ቻይና የኢትዮጵያ ቡና በብዛት ከሚላክባቸው አገራት መካከል በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 16,300 ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ቻይና የተላከ ሲሆን፣ ይህም 113 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ እንደገለጹት፣ ይህ ማዕከል የኢትዮጵያን ቡና ለቻይናውያን ሸማቾች በቀጥታ ለማድረስ ትልቅ በር ይከፍታል።
ማዕከሉ የዙዙ ከተማን የድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሮኒክ ንግድ መሠረተ ልማት በመጠቀም፣ የንግድ ስራውን ቀልጣፋ እና ተደራሽ ያደርገዋል።
ከንግድ ልውውጡ በተጨማሪ፣ ማዕከሉ የኢትዮጵያን የቡና ባህል ለቻይናውያን በማስተዋወቅ ዘላቂ ደንበኞችን ለማፍራት እንደሚሰራ ተገልጿል።
በዚሁ የኮንፈረንስ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ እና በቻይና ኩባንያዎች መካከል በቡና ግብይት፣ በምርት ልውውጥ እና በታዳሽ ሃይል ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነቶች ተፈርመዋል።
