Home የአቡጀዲ ግርግር በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ተዘጋጀ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ተዘጋጀ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ተዘጋጀ

በዓለማችን ላይ አንድ ሚሊዮን አካል ጉዳተኛ ሰዎች እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች ዘገባ ያመለክታል፡፡ በአህጉራችን አፍሪካ ደግሞ ከ100 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ እንዲሁም በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያጠቁማል፡፡

በታዳጊ ሀገሮች የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች ለሥነ ልቦና፣ ለምጣኔ ሃብት እና ለሌሎች ፈርጀ ብዙ ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በማህበረሰቡ በተፈጠረው የግንዛቤ እጥረት ምክንያት ዋጋ ከፋይ ለመሆንም ተገድደዋል፡፡ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የሚኖሩ አካል ጉዳተኞችም የዚህ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ብቻ ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ በማህበረሰቡ መገለል እና መድሎ የሚደርስባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ውድ የሆነውን የልጅነት ጊዜያቸው ከማህበረሰቡ ተለይተው በብቸኝነት ቤታቸው ለማሳለፍ የተገደዱም በርካታ ናቸው፡፡

በሰዎች ዘንድ የሰረጸውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየርም ሆነ ለማሻሻል ተገቢውን የግንዘቤ ማስጨበጥ ተግባር በሚመለከተው አካል በተገቢው መንገድ ሳይከናወን ቀርቷል፡፡ ሆኖም የአካል ጉዳተኛ ወላጆች ከማኅበረሰቡ የሚሰነዘሩ ተጽዕኖዎችን ለመሸሽ ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ የሚደብቁ ትንሽ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት የአካል ጉዳተኞች እምቅ ችሎታና ተሰጥዖ ተደብቆ የሚቀርበት እድል ሰፊ ሆኗል፡፡ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው የውጣ ውረድ ሕይወት በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩ የጤና፣ የትምህርት፣ የሥራ እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ሁኔታ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡

አካል ጉዳተኞች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማከናወን በግል እና በመንግሥት ተቋማት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ መጉላላት ይደርስባቸዋል፡፡ ይህ ማለት በሀገራችን ያሉ የግል እና የመንግሥት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ማለት ግን አይደለም፡፡ በትራንስፖርት መጓጓዣዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመሥሪያ ቤቶች፣ በሕንጻዎች መወጫጫዎች፣ የመፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም በመጻሕፍት ሕትመት በተመለከተ የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጁ አይደሉም፡፡

ዓለም በሰለጠነችበት በአሁኑ ወቅት ቢሆንም ወላጆች አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን ከማህበረሰቡ እና ከችሎታቸው ለይተው የሚያኖሩትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አካል ጉዳተኝነት በማኛውም ሰው በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሊያጋጥም እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚገኙት እድል ዝቅተኛ የሚባል ሲሆን፤ ይህን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነት በመሆኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ ለለውጥ መሥራት ተገቢ ይሆናል፡፡

የአካል ጉዳተኞችን ልዩ ችሎታዎች በመረዳት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ የማድረግ ሥራ ብዙ የሚቀረው ተግባር ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች ሆነው የተሳሳተውን የማህበረሰባችን አስተሳሰብ ሰብረው የወጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ ይልቁንም ያላቸውን አቅም እና ችሎታዎችን በተለያዩ መድረኮች ላይ ማስመስከር ችለዋል፡፡ ከብዙ ጥረትና ትግል በኋላ ዓላማቸው ግብ መቶ ለሌሎች ሰዎች አርአያ የሚሆኑ ተፈጥረዋል፡፡ የግል እና የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ሕብረተሰቡ ይህን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት አካል ጉዳተኞችን ማገዝ እና እውቅና መስጠት አኩሪ ተግባር ነው፡፡

ዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ቀን በዓለማቸውን ለ30ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ29ኛ ጊዜ ‹አካል ጉዳተኞችን መሪነትና ተሳታፊነት በማድረግ አካታች፣ ተደራሽና ዘላቂ ድኅረ ኮቪድ 19 ዓለም እንገባ› በሚል፤ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን እና በሱማሌ ክልል አዘጋጅነት በጅጅጋ ከተማ ተከብሯል፡፡

የመጀመሪው የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች የፊልም ፌስቲቫል እና ሽልማት ሥነ ሥርዓት በፎክስ ኦን አቢሊቲ ኢትዮጲያ አጭር የፊልም ፌስቲቫል አማካኝነት መዘጋጀቱ ተገልጹዋል፡፡ የፌስቲቫሉ አስተባባሪ ቤዛ ዳምጠው ለግዮን መጽሔት እንደገለጹት፤ ፌስቲቫሉ በሀገራችን ያለው በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ብዙ አካታች የሆኑ ጉዳዮች እየሰሩ ባለመሆኑ እና በኪነ ጥበብ ዙሪያ ሰዎችን ለማነቃቃት ያለመ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፊልም ፌስቲቫሉ ትኩረታቸውን በአካል ጉዳት ላይ ያደረጉ እና በአካል ጉዳተኛ ጥበበች የተሰሩ አጫጭር 33 ሀገራዊ ፊልሞች እና 14 የውጭ ሀገር ፊልሞች ለተመልካች እይታ እንደሚቀርቡ አንስተው፤ የአካል ጉዳተኞች ሕይወት በፊልሙ በልዩ ሁኔታ እንደሚዳሰስ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል  መክፈቻ በታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም በቫምዳስ ሲኒማ እና በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል የተካሄደ ሲሆን ፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በጤና ሚኒስትር የወጣውን መመሪያ ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ የሚከናወን መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ መቀመጫውን ስዊዲን አውስትራሊያ ያደረገው  ፎከስ ኦን አቢሊቲ  የፊልም ፊስቲቫል ፤ ላለፉት 13 ተከታታይ ዓመታት ከሀገር ውጭ የፊልም ፌስቲቫሎችን ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡    

የፌስቲቫሉ የመክፈቻ ፊልም ‹ሕሊና› የተሰኘው ፊልም ነው፡፡ ይህ ፊልም በዚህ ዓመት በዓለም አቀፍ የአጭር ፊልም በአውስትራሊያ አሸናፊ በሆነው በእስክንድር አብርሃ ፊልም መኾኑ ታውቋል፡፡ በፌስቲቫሉም ኢትዮጵያዊያን ወጣት የፊልም ሰሪዎችን ከአንጋፋ የፊልም ባለሞያዎች ጋር የሚያገናኝ የውይይት፣ የጥያቄ እና መልስ መድረክ እንደሚኖር ተነግሯል፡፡ የሚከናወነው ውይይት ‹የአካል ጉዳተኞችን ማካተት› እና ‹አጭር የፊልም ጥበብ› በሚሉ ርዕሶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የውይይት መድረክ የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ መቻል ወደ ሚለው አስተሳሰብ የማምጣት እና የሥራ ቀጣሪዎች አካል ጉዳተኞችን ሲያሳትፉ የሥራ ሁኔታውን ለነሱ አመቺ በሆነ መልኩ እንዲተገብሩ ማስቻል እንዲችል ያደርጋል ብለዋል፡፡

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል የሽልማት ሥነ ሥርዓት ታህሳስ ሦስት በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በተጋባዥ ዳኞች እና ጥሪ በተደረገላቸው እንግዶች ብቻ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በፎከስ ኦን አቢሊቲ የፊልም ፊስቲቫል እና ባዛር ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ሙሉ በሙሉ አካል ጉዳተኞች ብቻ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡

እንደ ቤዛ ገለጻ ፊስቲቫሉ እነዚህን ሀገር በቀል ፊልሞች ለማበረታተት እና ለማስተዋወቅ በ10 የተለያዩ ዘርፎች፤ በምርጥ ተዋናይ ዘርፍ፣ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ፣ በምርጥ ጽሑፍ ዘርፍ፣ በምርጥ ዳይሬክቲንግ ዘርፍ፣ በምርጥ ኤዲቲንግ ዘርፍ በምርጥ አኒሜሽን ዘርፍ ፣ በምርጥ ሳውንድ ስኮር ዘርፍ ፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፍ፣ በምርጥ አጭር ፊልም ዘርፍ እና ምርጥ ዶክመንተሪ ዘርፍ ናቸው፡፡ ፌስቲቫሉ በኢትዮጵያ መካሄዱ አካል ጉዳተኞች በራሳቸው ራሳቸውን ታሪክ እንዲሰሩ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ አክለውም በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሚሳተፉበት ፌስቲቫል በመሆኑ ተደራሽነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በኪነ ጥበብ ዘርፍ ላይ ተሳታፊ ለማድረግ ማስተዋወቅ ሥራ አለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የፌስቲቫሉን ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ከአውስትራሊያው ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የተጀመረው ፌስቲቫል ለማጎልበት ሁሉም በየድርሻው ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ከግዮን መጽሔት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡