የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በእንስሳት ላይ ባከናወናቸው የቅድመ እና ድህረ ዕርድ ምርመራ ከ200 በላይ የሚሆኑት እንስሳት ላይ እርድ እንዳይፈጸም መደረጉን አስታውቋል፡፡
በ193 ሺሕ 356 የሚጠጉ የዳልጋ ከብቶች፣ ከ42 ሺሕ 911 በጎች፣ 39 ሺሕ 292 ፍየል እንዲሁም 1 ሺሕ 868 ግመል እና 33 አሳማዎች ላይ የድህረ እና ቅድመ ምርመራ መከናወኑን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ጸጋ ለማ የተናገሩ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ የቁጥጥር ሥራ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
አክለውም “አባሰንጋ እንዲሁም ቲቢ በሽታ ጨምሮ እንስሳቱ በሚጓጓዙበት ጊዜ በሚደርስባቸው ምት ምክንያት ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር ምረመራ ይከናወናል” ያሉ ሲሆን፤ በቅድመ ዕርድ ላይ የእንሳት ምርመራ ከተከናወነ በኋላ ከስጋው ናሙና በመውሰድ በላብራቶሪ በታገዘ መልኩ ምርመራ እንደሚከናነወን እና ደህንቱ በምርመራ ከተረጋጋጠ ለማህበረሰቡ እንዲሰራጭ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በኮሚሽኑ ምርመራ በተደረገባቸው እንስሳት ውስጥ የእንስሳት ሕመም፣ የከሱ እና መደለብ ያለባቸው ተብለው የተለዩ እንዲሁም ነብሰ ጡር የሆኑት እንስሳት ላይ እርድ እንዳይፈጸምባቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት ውስጥ በከተማዋ በሚገኙ ሦስት ቄራዎች ላይ የቅድመ እና ድህረ ዕርድ በእንስሳት ላይ ምርመራ ማከናወኑን ኮሚሽነሩ የገለጹም ሲሆን፤ “በምርመራ ወቅት 176 እንስሳት ለዕርድ ብቁ አለመሆናቸው በመረጋገጡ እንዲሁም የእርግዝና ምርመራ ተከናውኖ 96 የሚሆኑ ሴት እንስሳት ወደ ዕርድ እንዳይገቡ ተደርጓል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በሦስቱም ቄራዎች ውስጥ በሚያከናውነው የእንስሳት የቅድመ እና ድህረ እርድ ምርመራ ከ40 በላይ በሚሆኑ የስጋ ምርመራ በሚያከናወን የሕክምና ባለሞያዎች ምርመራው እንደሚከናወንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ በእንስሳቱ ላይ ከሚያከናውነው የጤና ምርመራ በተጨማሪ ዕርድ ከተከናወነ በኋላ የድህረ ዕርድ ምርመራ እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡
