107 የተቋሙ ሰራተኞች እና 300 የሚዲያ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን ለቢቢሲ አመራር ይፋዊ ደብዳቤ ፅፈዋል።
በደብዳቤውም ቢቢሲ የእስራኤል ጉዳይ ላይ ሲመጣ “ሳንሱር” እና “ለእስራኤል መንግስት እና ወታደራዊ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ስራ በማከናወን ላይ ነው” በማለት ተቋሙ ላይ ክስ ሰንዝረዋል።
በዴድላይን የታተመው ደብዳቤው በተለይ የቢቢሲ የጋዛ ሜዲክስ ዶክመንተሪ ፊልም እንዳይሰራጭ መወሰኑን ተከትሎ ይህ የቅርብ ጊዜ ውሳኔ “በአጀንዳ ከተመሩ ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ነው” ብለዋል።
ሰራተኞቹ “አብዛኛው የቢቢሲ ሽፋን በፀረ-ፍልስጤም ዘረኝነት ይገለጻልም” ብለዋል።
በተጨማሪም ቢቢሲ የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት በፍልስጤማውያን ላይ በሚደረገው ጦርነት የጦር መሳሪያ ሽያጮችን ወይም የህግ አንድምታዎቻቸውን ጨምሮ ምንም አይነት ጉልህ ትንታኔ አላቀረበም ብለዋል።
“የቢቢሲ ኤዲቶሪያል ውሳኔዎች ከእውነታው የራቁ ይመስላሉም ያሉ ሲሆን፤ ውሳኔዎች የተመልካቾችን ፍላጎት ከማገልገል ይልቅ የፖለቲካ አጀንዳን ለማሟላት የሚሰጡ ናቸው ብለን ለመደምደም ተገድደናልም” ብለዋል።
ደብዳቤውን የፈረሙት የቢቢሲ ሰራተኞች ስማቸው ይፋ ያልተደረገ ቢሆንም ጥሪያቸውን ከሚደግፉ የኢንዱስትሪው ሰዎች ግን ካሊድ አብደላ እና ሚርያም ማርጎልየስ ይገኙበታል ተብሏል።
