Home ቢዝነስ ዜና ባለፉት ሦስት ዓመታት 3.5 ትሪሊዮን ብር በቴሌብር ዝውውር መደረጉ ተገለጸ

ባለፉት ሦስት ዓመታት 3.5 ትሪሊዮን ብር በቴሌብር ዝውውር መደረጉ ተገለጸ

ባለፉት ሦስት ዓመታት 3.5 ትሪሊዮን ብር በቴሌብር ዝውውር መደረጉ ተገለጸ
  • የእንስሳት ዲጂታል ክትትል ቴክኖሎጂ ይፋ ተደርጓል

ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 ዓ.ም. ባስጀመረው የቴሌብር አገልግሎት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 51 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት 3.5 ትሪሊዮን ብር ዝውውር መፈጸሙን አስታወቀ፡፡

የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. የግብርናውንና የማኑፋክቸር ዘርፉን፣ እንዲሁም ትምህርት፣ ኢንተርፕራይዞችንና የሌሎች ተቋማትን አቅም ይገነባሉ የተባሉ ሰባት የዲጂታል ሶሉዩሽኖችን ይፋ ሲያደርግ ነው ያስታወቀው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የቴሌኮምና የዲጂታል ሶሉውሽን እያስገባ መሆኑን፣ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጨዋታ ቀያሪ›› ሲሉ የጠሩት የቴሌብር በአገልግሎት ሰጪና በተቀባይ መካከል የነበረውን የክፍያ ሥርዓት በእጅጉ እያቃለለ እንደሚገኝ ገልጸው፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ አገር በማስገባት በተቋማት ላይ ለውጦችን ስለማስመዝገቡ አክለዋል፡፡

ይፋ የተደረጉት ዲጂታል ሶሉዩሽኖች ክላውድ ቤዝድ በመሆናቸው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የማይጠይቁና በዳታ ብቻ የሚሠሩ መሆናቸውን የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው በቀላሉ ወደ ሥራ መሰማራት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ይፋ ከተደረጉት ሶሉዩሽኖች መካከል አንዱ የዲጂታል ላይቭ ስቶክ (የእንስሳት ዲጂታል ክትትል) ነው፡፡ የእንስሳት ጤንነትና የዝርያ ዓይነት፣ እንዲሁም ቀለማቸውንና ያሉበትን ቦታ በቀላሉ ለመከታተል እንደሚያስችል የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ‹‹የእንስሳት አርቢዎች በቀላሉ የብድርና የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፤›› ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የእንስሳት ዕርባታን ዘመናዊ በማድረግ አገሪቱ ያላትን ግዙፍ የእንስሳት ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀም የሚያስችል መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንስሳቱ ያሉበትን ቁመናና ሌሎች መረጃዎችን ለማወቅና ለመከታተል አስቸጋሪ እንደነበር የጠቀሱት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ይህም አርሶና አርብቶ አደሮች በሬ ወይም ግመላቸውን አስይዘው ከባንክ ብድር ለመጠየቅና ኢንሹራንስ ለመግባት ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሮችን ችግር ይፈታል የተባለው ይህ የእንስሳት መከታተያ ዲጂታል ላይቭስ ትራኪንግ ሶሉዩሽን፣ የእንስሳቱን ወቅታዊ ቁመና ማየት የሚያስችል በመሆኑ ባንኮች የብድር አገልግሎት ዋስትና መሆን እንደሚቻል ገልጸው፣ በዚህም አርሶ አደሮች በእንስሳቶቻቸው የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል አክለዋል፡፡

 መረጃዎችን የሚመዘግቡ አነስተኛ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች በእንስሳት ጆሮና በአንገታቸው፣ እንዲሁም በቆዳቸው ውስጥ የጂፒኤስ ቺፕ ሴት (GPS Chipsets) ቴክኖሎጂ በመቅበር ቀለማቸውን፣ ፆታቸውን፣ የተወለዱበትን ቀንና ዕድሜያቸውን መመዝገብ እንደሚያስችል የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ የሚገጠምላቸው ቴክኖሎጂ እንስሳት ቢጠፉና ያሉበት ቦታ ባይታወቅ በቀላሉ ተከታትሎ መረጃ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

በተሰበሰበው መረጃ መሠረት ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሲስተሙ የታቀፉ እንስሳትን እንደ መያዣ በመቀበል፣ የብድርና የመድን ዋስትና አገልግሎት ለመስጠት አመኔታ እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

በሌላው የዲጂታል ሶሉዩሽን ትምህርት ቤቶችን የሚያዘምንና የትምህርት አስተዳደር ሥርዓትን የሚያሻሻል መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

ይህም ከኬጂ እስከ ድኅረ ምረቃ ድረስ ላለው የትምህርት አገልግሎት የተለያዩ ጠቀሜታዎችን እንደሚሰጥ የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ የትምህርት ቤት አስተዳደርን፣ መምህራንና ወላጆችን፣ እንዲሁም ተማሪዎችን በዲጂታል ሥነ ምኅዳር ማስተሳሰር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ወላጆች በቀላሉ ባሉበት ሆነው የልጆቻቸውን የትምህርት ሁኔታ፣ የተሰጣቸውን የቤት ሥራና የቀሩበትን ቀን ጨምሮ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል እንደሚያስችል ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ከዚህ ባሻገር የኩባንያዎችን የቢዝነስ ሥራ ለማቀላጠፍ የሚያስችል ‹‹የአንድ ቢሮ ትስስርና ምርታማነት ሶሉዩሽን›› የሚል ቴክኖሎጂ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ብዙ የሥራ ፍሰቶችን ወደ አንድ ቋት በማምጣት በተለይ ለኢንተርፕራይዞች ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

 ኮር ባንኪንግ ሶሉዩሽን የተባለው ደግሞ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት አባላቶቻቸውን ወይም ደንበኞቻቸውን በተሻለ መንገድ እንዲያገለግሉ፣ የፋይናንስ አካታችነታቸውን እንዲያረጋግጡ በማድረግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ይረዳል ሲሉ አክለዋል፡፡