‹‹ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው ስሜት በጣም ከባድ ነበር›› መላከሰላም ተስፋሚካኤል አሰፋ (የጅማ፣ የየም እና የኮንታ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ)

Date:

መላከሰላም ተስፋሚካኤል አሰፋ ይባላሉ፡፡ የጅማ፣ የየም እና የኮንታ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በቅርቡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የኾኑት ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ስለደረሰባቸው እስር እና እንግልት ብሎም ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ በሀገረ ስብከታቸው ተፈጻሚ እንዳይኾን በእርሳቸው ላይ ስለደረሰው እገታ እና አንዳንድ የሕገወጡ ቡድን ደጋፊዎች በአካባቢው እያከናወኑት ስላለው እንቅስቃሴ ከግዮን መጽሔት ጋር ባደረጉት ተከታዩ ቆይታ ይናገራሉ፡፡ መልካም ንባብ! 

ግዮን፡- ራስዎን ለአንባቢያን ቢያስትዋውቁልን?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- መላከሰላም ተስፋሚካኤል አሰፋ እባላለሁ፡፡ የጅማ፣ የየም እና የኮንታ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ነኝ፡፡

ግዮን፡- ምን ያህል ዓመት በሥራ አስኬያጅነት አገለገሉ?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- በሥራ አስኪያጅነት አምስት ዓመት ከመንፈቅ በላይ ሠርቻለሁ፡፡

ግዮን፡- በቅርቡ በቤተክርስቲያን ላይ የተካሄደውን ኢቀኖናዊ ሲመት እንዴት አዩት? ግለሰቦቹንስ በቅርብ ያውቋቸዋል?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- ይህን ጉዳይ የፈፀሙ አባቶች በመጀመሪያ ከዋናው ሲኖዶስ ጋር አብረው የነበሩ ናቸው፡፡ የማናውቃቸው ሰዎች ሳይኾኑ በቤተክርስቲያኒቷ አገልግሎት የምናውቃቸው ናቸው፡፡ አሁን የተፈፀመው ነገር እንደ አንድ የቤተክርስቲያን ልጅ ስናየው የቤተክርስቲያን ሕግ ያልጠበቀ የቤተክርስቲያንን አንድነት የለየ ነው፡፡ ቀኖና ቤተክርስቲያንንም የጣሰ መኾኑን እንረዳለን፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያስተላለፈው መልዕክት ሁላችንንም የሚወክል ሃሳብ ነው፡፡ እኔም የምረዳው በዚህ መንገድ ነው፡፡

ግዮን፡- በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ላይ የምዕመኑ ተቀባይነት ምን ይመስላል? እንደ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኬያጅነትዎ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር የተሰማዎት ምን ነበር?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- ቅዱስ ሲኖዶስ የሁሉም የበላይ ነው፡፡ አባቶቻችን ያለውን ነገር አይተውና ገምግመው የወሰኑት ውሳኔ ሕዝቡ ተቀብሎታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ያለምንም ሥጋዌ እውቀት ከፖለቲካም ከዘርም በፀዳ መልኩ የተወሰነው ውሳኔ የሁላችንም ነው፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት የሚጠበቁ ተግባራትን የማስተገበርና የወረዱ መመሪያዎችን ማስቀጠል ግዴታችን ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች አሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ በአብላጫ የሚደግፉ አሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ የተወገዘውን ስብስብ ይደግፋሉ፡፡ የኾነው ኾኖ ግን የተፈጠረው አለመግባባት ከላይ የመጣውን ቤተክርስቲያን ለይቶ ማየት ካልተቻለና ዘመን ባመጣው የፖለቲካ ዘር ከተሄደ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተረስቶ ሌላ ችግር ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያንን ማዕከል አድርገን ከተነሳን ከሐዋሪያት የተቀበልንናት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ትተላለፍ የሚለውን ከተገነዘብን ሁላችንም በሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ይህ ባለመኾኑ ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ ጅማም ላይ ችግሮች ነበሩ፡፡ የኾነው ኾኖ ግን ቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ በሀገረ ስብከታችን ከፍተኛ ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡

ግዮን፡- የጅማ ደብረ ኤፍራታ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን ለማስመረቅ ወደ ጅማ በመጡት በብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ ላይ የተፈጸመው ነገር ምን ነበር?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡-  የደብረ ኤፍራታ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ምርቃት ግንቦት 2014 ዓ.ም ጀምሮ የተያዘ ፕግራም ነው፡፡ ከዚያ በፊት ጥር 2014 ጥር ይመረቃል ብለን ፕሮግራም ይዘን ነበር፡፡ ነገር ግን እለቱ ተቀይሮ ወደ ግንቦት 21 ተዛወረ፡፡ ነገር ግን ያልተሟሉ ጉዳዮች በመኖራቸው አሁን በጥር 2015 እንድትመረቅ ተደረገ፡፡ የረጅም ጊዜ ዝግጅት አድርገን ቀኑ ሲደርስም ለከተማ አስተዳደሩና ለሚመለከተው አካል ሁሉ አሳውቀን ተቀባይነት አግኝተን ነበር፡፡ ከኤርፖርት ጀምሮ እንግዶች እንዴት እንደሚገቡም ፕሮግራም ተሠርቶ ነበር፡፡ ከፍ ያለ ዝግጅት አድርገን ነበር፡፡ በበጀት ደረጃም ከፍተኛ ዝግጅት ነበር፡፡ ባለቀ ሰዓት ግን እንግዶች እንዳይገኙ የሚል መልዕክት ተላለፈልን፡፡ ይህን መመሪያ ለመለወጥ ብዙ ጥረት አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን አልኾልንም፡፡ እርሳቸውም ቢኾኑ ሀገረ ስብከታቸው ስለኾነ ልዩ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ በሐሳብ ደረጃ እርሳቸው ሕዝቡን እየመሩት ፕሮግራሙን እንዲካሄድ ተነጋግረን ነበር፡፡ ነገር ግን አስቆሙት፡፡ በፕሮግራሙ መሠረት እርሳቸው ሲመጡ እኔም አየር መንገድ ሄጄ ተቀብያቸዋለሁ፡፡ ይዘናቸው ልንገባ ስንል ከኤርፖርት እንድንወጣ አደረጉን፡፡ ከዚያ ይዘውን ጣቢያ ሄደን የአዛዡ ቢሮ እንዲያርፉ ተደረገ፡፡ ይህ ሲደረግ የደረሰን መረጃ ለአባታችን ጥበቃና ደህንነታቸው ሲባል እንደተደረገ ነበር፡፡ እርሳቸው ከተማ ውስጥ አንድ ነገር ቢደርስባቸው ለቤተክርስቲያንም ለሀገርም ችግር በመኾኑ ጥንቃቄ ይሻል የሚል ነገር ተናገሩ፡፡ በኋላም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደረጉ፡፡

ግዮን፡- ምዕመኑስ ጋ የተፈጠረው ስሜት ምን ነበር?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- እውነት ለመናገር ያን ቀን ለእኛ ትልቅ ፈተና ነበር የኾነብን፡፡ ብፁዕነታቸው ቅዳሜ ነበር የገቡት፡፡ ሕዝቡ ደግሞ የአባታችንን መቅረት አያውቅም ነበር፡፡ ለኮሚቴው ተናግረን ነው የአባቶችን መቅረት ያወቀው፡፡ ነገር ግን ለሰፊው ሕዝብ በተለይም ለወጣቱ ለማስረዳት በጣም ከባድ ነበር፡፡ የጊዜ እጥረት ነበር፡፡ የአባቶችን አለመምጣትና የእርሳቸውንም መቅረት ሲያውቅ ሕዝቡ የነበረው ስሜት ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህ ምዕመኑ በጣም ነበር ያዘነው፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው የጩኸት ስሜት በጣም ከባድ ነበር፡፡ ለማረጋጋትና ነገሮችን ለማስረዳት እስከሚከብደን ድረስ ነበር የኾነው፡፡ ለማንኛውም ሰው ከ10 ዓመት በላይ ሰርቶ ገንብቶ በዚህ ቀን ደስታዬን አያለሁ ብሎ የደስታ ቀኑ በዚህ ዓይነት መልኩ ሲኾን በጣም ያሳዝናል፡፡ ሕዝቡ በዚያ ልክ ነበር ስሜቱ፡፡ በዚህ ምክንያትም ሕዝቡ እሳቸውን በሌሉበት ቤተክርስቲያን አይመረቅም፣ አይባረክም ብሎ ሲጮህ ሌላ ነገር ከሚፈጠር ብለን ታቦቱን ወደ መቃኞው መለስን፡፡ እርሳቸው በሚገኙበት ሌላ ቀን ይመረቅ የሚል ውሳኔ ላይ እንድንደርስ ያደረገን የሕዝቡ ስሜት ነው፡፡ በጣም ነው ሕዝቡ ያዘነው እና ያለቀሰው፡፡

ግየን፡- ፕሮግራሙ ወደ መቼ ተቀየረ?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡-  አሁንም ጊዜውን መወሰን አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ስላሉብን ነው፡፡ በሌላ ወገንም ተመድበዋል የተባሉ አባቶች ስላሉ አስቸጋሪ ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ግን አባታችን አቡነ እስጢፋኖስ በሌሉበት አይመረቅም የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ከብጹዕነታቸው ጋር እየተማከርን በምናወጣው ፕሮግራም መሠረት ምርቃቱ የሚካሄድ ይኾናል፡፡

ግዮን፡- ከተወገዘው ስብስብ እናንተ ጋር የተመደቡት ግለሰብ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- እኛ ይኼን የሰማነው በወሬ ደረጃ ነው፡፡ በአካል ወደዚህ የመጣ የለም፡፡ ያን ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ግን እናውቃለን፡፡ ለመቀበል ዝግጅት የሚያደርጉና የሚሮጡ ሰዎች አሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ጅማን ማንም አይረግጥም ከአቡነ እስጢፋኖስ ውጪ ማንንም አንፈልግም የሚል ሌላ ከባድ ስሜት ውስጥ ያሉ ምዕመናንም አሉ፡፡ የኾነው ኾኖ የተመደበው ሰው በወሬ እንጂ በአካል አልደረሰም፡፡ በደብዳቤም አልተገለፀም፡፡ እኛም መደበኛ ሥራችንን እየሠራን ነው፡፡ መመሪያ እየተቀበልን እየተመካከርን በመሥራት ላይ ነው የምንገኘው፡፡

ግዮን፡- ጥር 22 ቀን በእርሶ ላይ ምን ነበር የተፈጠረው?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡-  ቅዳሜና እሁድን ከፍ ሲል በገለፅኩት ሥራ ላይ ነበር ያሳለፍኩት፡፡ በተለይ እሁድ እለት አስተርእዮ ማርያም ስለነበረች በስሜት ፈንቅሎ የመጣ ሕዝብ ነበር፡፡ ስለዚህ ያንን ሕዝብ አረጋግተን ወደ ቤት ማስገባት በጣም አድካሚ ሥራ ነበር፡፡ ወጣቱ ከቤተክርስቲያን ውጪ ቢወጣ የጸጥታ ኃይሎች ለማረጋጋት እርምጃ ሊወስዱ ስለሚችሉ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡ ወጣቱ ተከላከልኩ በሚል የጋለ ስሜት ላይ ነበር የሚገኘው፡፡ እኛም ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመነጋገር ነው ቀኑ ያለፈው፡፡ ከጸጥታ ኃይሉ ኃላፊዎችም ሕዝቡን “አረጋግተውልናል” በሚል ደውለው አመስግነውኛል፡፡ ነገር ግን እሁድ ማታ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ቤቴ በወታደሮች ተከቦ አደረ፡፡ ሰዎች ቤቴ መከበቡን ሲነግሩኝ አልገባኝም ነበር፡፡ በማግሥቱ ሰኞ ጉባኤ ስለነበረብኝ እዚያ እሄድ ነበር፡፡ ሹፌሬ እንዲወስደኝ ስጠብቀው ቀረብኝ፤ ምን ገጥሞት ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ በሌላ ተሸከርከካሪ ለመጠቀም ከቤት ስወጣ የጸጥታ ኃይሎች ይዘውኝ ሄዱ፡፡

ግዮን፡- የጸጥታ ኃይሎች ሲይዞት ምን ተነገሮት?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- ትፈለጋለሀ ብለው ነው በፓትሮል የወሰዱኝ፡፡ ከወሰዱኝ በኋላም የሀገረ ስብከቱን ንብረት ልታሸሽ ነው? ቤትህ ፀጉረ ልውጥ ሰው አሳድረሃል? የቤተክርስቲያኒቱን ንብረት ዘርፋችሁ ልትሄዱ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው የቀረቡት፡፡ በኋላም ቤቴን ፈትሸዋል፡፡

ግዮን፡- ምን ያህል ጊዜ በእገታ ቆዩ? የትስ ነበር የታሰሩት?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- የታሰርኩት የጅማ ከተማ ወረዳ 2 ፖሊስ ጣቢያ ነው፤ የቆየሁትም ለሁለትና ሦስት ሰዓት ያህል ነው፡፡

ግዮን፡- የሀገረ ስብከቱ ንብረት ታግዶ ነበር?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- ብጹዕ አባታችን በዚህ ረጅም ዓመት አገልግሎት ዘመናቸው ውስጥ ለገጠር ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚኾኑ መኪኖች ነበሯቸው፡፡ በተጨማሪም በጠቅላይ ቤተ ክህነትቱና የጅማ ሕዝብ በሠሩት ሥራ አክብሯቸው የሰጣቸው መኪናም ነበራቸው፡፡ በተለይ ይህ በስጦታ ያገኙት መኪና በራሳቸው ስም እንዲኾን ከሄዱም ይዘውት ከኖሩም የግል ንብረታቸው ኾኖ እንዲጠቀሙት ሕዝቡ ጠይቆና ለምኖ ነበር፡፡ እርሳቸው ግን “ቤተክርስቲያኗ የኔ ናት የኔ የምለው የግል ንብረት ሊኖረኝ አይገባም፡፡ ስለዚህ ለሀገረ ስብከቱ ይሁን” የሚል አቋም ስለነበራቸው መኪናው በሀገረ ስብከቱ ስም ሊብሬ ተሠራለት፡፡ ከዚህ መኪና ጋር ሀገረ ስብከቱ አምስት መኪኖች አሉት፡፡ እነዚህን መኪኖች ሊያሸሹ ነው በሚል ነው ኬላም ተዘግቶ እንዳያልፍ የተደረገው፡፡

ግዮን፡- የፀጥታ ኃይሎች ይህ እንዴት ሊፈጠር ይችላል ብለው አሰቡ? የፖለቲካ ወገንተኝነት ያለበት አካሄድ አይመስልም?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- እኛም የምናስበው በዚሁ አግባብ ነው፡፡ ከመንግሥት መዋቅር ጋር ለረጅም ዓመታት አብረን ነው ስንሠራ የነበረው፡፡ በጣም በብዙ ጉዳይ ያውቁናል፡፡ አባታችንን ሁሉም በመልካም ያውቃቸዋል፡፡ የደቡብ ምዕራብ ሪጅን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አባታችንን የሰላም አምባሳደር ብሎ ሾሟቸዋል፡፡

ግዮን፡- በእሳቸው 22 ዓመት የአገልግሎት ዘመን ቆይታ ውስጥ በሀገረ ስከቱ ውስጥ ምን ምን የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከትን ዳግም ፈጥረውታል ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም 22 ዓመታት ጅማ ሀገረ ስብከትን ከዜሮ አንስተው ነው ያቋቋሙት፡፡ በነበረው ሂደት ሀገረ ስብከቱ በበጀት ራሱን የማይችል የካህናት ደሞዝ መክፈል ያቃተው ሀገረ ስብከት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ቤተክርስቲያናት በበጀት መጥፋት ምክንያት ካህናት አጥተው የተዘጉ ነበሩ፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን ማስፋፋት በከተማ ሰባት የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት አሁን በጅማ ብቻ 20 እንዲኾኑ ተደርጓል፡፡ በገጠር አጠቃላይ 186 የነበሩ አብያተ ክርስቲያናትን አሁን ወደ 420 አድርሰውታል፡፡ ሌሎች በመሠራት ላይ ያሉም ብዙ ናቸው፡፡ በሕዝብ ቁጥር በአብያተክርስቲያናት መስፋፋት፣ በልማት፣ በማኅበራዊ ዘርፍ ሁሉ ትልቅ ተሳትፎ ያደረጉ አባት ናቸው፡፡ ስለዚህ አቡነ እስጢፋኖስ ሀገረ ስብከቱን ዳግም ፈጥረውታል ቢባል ስሕተት አይኾንም፡፡ በጀት በጠቅላይ ቤተክህነት ባለው መገምገሚያ እራሳቸውን የማይችሉ ከሚባሉ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ጅማ ሀገረ ስብከት አንዱ ነበር፡፡ አሁን ግን እራሱን ችሎ ለጠቅላይ ቤተክህነት ተጨማሪ የሚያስገባ ራሳቸውን ከቻሉ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ አንዱ ኾኗል፡፡

በሰው ኃይል፣ በካህናት፣ በሰባኪያን ቁጥር የአካባቢውን ልጆች በቋንቋው ተምረው ወንጌል አውቀው እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል፡፡ አበርጌ ገዳም ማለት በዓመት ከ60 እስ 70 ልጆች የሚመረቅበት ገዳም ነው፡፡ አሁን ራሱ ወደ 123 ተማሪዎች እየተማሩ ነው፡፡ እነዚህ 123 ተማሪዎች በሀገረ ስብከቱ ካሉ ወረዳዎች በየም ቋንቋ፣ በኦሮምኛ ቋንቋ፣ በከፊቾ ቋንቋ፣ በወላይትኛ ቋንቋ ማስተማርና መናገር የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ያለፉትን 22 ዓመታት በርካታ የሰው ኃይል አፍርተዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ካሉት 20 ወረዳዎች ውስጥ 16ቱን የኦሮሞ ልጆች ናቸው ሀገረ ስብከቱን በሥራ አስኪያጅነት የሚያገልግሉት፡፡

በእነዚህ ወረዳዎች ሥር ደግሞ ብዙ ሰባኪያን አሉ፡፡ አባታችን የተዘጉ ቤተክርስቲያናት እንዳይኖሩ ሀገረ ስብከቱም ተጠናክሮ እነዚህን ተግባራት እንዲከውን በማድረግ ትልቅ ሥራ አከናውነዋል፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ነው ጂፕላስ ሕንጻ አስገንብተው ያስመረቁት፡፡ ይህ ሕንፃ አሁን ላይ በወር 108 ካህናትን ደሞዝ ይከፍላል፡፡ ሁለተኛው ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ደግሞ አሁን በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሀገረ ስብከቱ በ22 ዓመታት ውስጥ የተሠራ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ በሁሉ ነገር እንዲጠናከርም በብዙ መልኩ ደግመዋል፡፡ በተለይ ከሠላም አንፃር እና ከሌሎች እምነቶች ጋር ባሉ መስተጋብሮች ዙሪያ አባታችን የሰላም አምባሳደር ኾነው ሠርተዋል፡፡ ሕዝቡ ቢጎዳ ችግር ቢገጥመው በትዕግስትና በኃላፊነት ለሀገር ሰላም በማሰብ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡

ግዮን፡- የተወገዘው ስብስብ ዋና ዓላማው ሕዝቡን በቋንቋ ማገልገል እንደኾነ ገልጾ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ደግሞ ሕዝቡን በቋንቋው እያገለገለች መኖር ከጀመረች መቆየቷ በተለያየ መንገድ ተገልጿል፡፡ ከዚህ አንፃር የተወጋዡ ስብስብ ፍላጎት ሥልጣን ይኾን?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- ሌላ ምሳሌ አያስፈልግም፡፡ እኔ የኦሮሞ ተወላጅ ነኝ፡፡ በእናቴም በአባቴም ኦሮሞ ነኝ፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የዚሁ የጅማ ልጅ ነኝ፡፡ ስለዚህ እኔ የኦሮሞ ተወላጅ የጅማ ልጅ ኾኜ በሥራ አስኪያጅነት እየሠራሁ ስለምገኝ ማሳያ መኾን እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም ከአካባቢው የተገኘሁ በቋንቋው ማስተማር፣ መናገር እና መቀደስ የምችል ነኝና፡፡

በዚህ በጅማ ብቻ ከ1000 በላይ ልጆች በቋንቋቸው እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ ሦስት ዓመት  መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይማሩና ስድስት ወር ደግሞ ስብከተ ወንጌል ተምረው  ተመርቀው በየአካባቢያቸው ይቀጠራሉ፡፡ ጅማ በሁሉም ወረዳዎች አብዛኛው ከአበርጊ ገዳም  የካህናት ማሠልጠኛ የወጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ማለት በቋንቋው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ይህን አስተናብሮና አደራጅቶ በበጀት አጠናክሮ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የቤተክርስቲያን የቋንቋ አገልግሎት ችግር የለም፡፡ እኔ በደንብ ስለማውቀው ይህን መናገር እችላለሁ፡፡ አሁን ነው ቋንቋ ቋንቋ መባል የተጀመረው፡፡ እርሳቸው ግን ከ15 ዓመት በፊት  ነው ይህን ፕሮጀክት  የጀመሩት፡፡ የበሻሻ ጉዳይ ሲመጣ ካህናቱ ጅማን ጥለው ፈርተው ሄደው ነበር፡፡ 1997 ዓ.ም ላይ “ከአካባቢው ልጆች ብናስተምር ችግር ቢመጣ ቁልፍ ጥለው አይሄዱም” ብለው የአካባቢውን ልጆች በጽኑ አቋም ማስተማር ጀመሩ፡፡ የፕሮቶኮል መኪናቸው እነዚህን ልጆች ለማሳደግ የሽሮ፣ የሽንኩርት፣ የቅቤ መጫኛ ነው፡፡

እናትም አባትም ኾነው በማስተማር ነው እነዚህን ልጆች ዛሬ ላይ የአድባራት አስተዳደር  ያደረጓቸው፡፡ ቤተክርስቲያን በዚያ ዙሪያ አልሠራችም ማለት እውነት ለመናገር ትክክል አይደለም፡፡ አሁን የተነሳው ሹመትና ተገንጣይነት የሥልጣን ጉዳይ እንጂ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በኦሮምኛ  የማይሰብክ ኾኖ አይደለም፡፡ ዛሬ ይህን ጉዳይ መታገያ ያደረጉ አባቶች በፊቱንም ሀገረ ስብከት ነበራቸው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥም አሉ፡፡ እስከትልቁ ኃላፊነት የደረሱ አባቶች ናቸው፡፡ እነርሱ በራሳቸው ሀገረ ስብከት ምን ሠሩ? ስለዚህ ጅማን ከእነርሱ ሀገረ ስበከት ጋር ማነጻጸር ያስለፈልጋል፡፡ አቡነ እስጢፋኖስ ኦሮሞ አይደሉም፡፡ ኦሮምኛ ቋንቋ አይናገሩም፤ እንደእርሳቸው ግን ለኦሮሞ ሕዝብ የደከመ ሕይወቱን ሰጥቶ የሠራ አባት የለም፡፡ ይህን የምለው እርሳቸውን ስለምንወዳቸው ሳይኾን ስለእውነታውና ሕዝቡ ሊመሰክር የሚችለው ማንም መጥቶ  በማየት በመረጃ ሊያረጋግጠው በሚችለው መልኩ ስለሠሩ ነው፡፡

ግዮን፡- ማስተላለፉ የሚፈልጉት መልእክት አለ?

መላከሰላም ተስፋሚካኤል፡- ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነው ውሳኔ አለ፡፡ የተወገዙት አባቶችም የራሳቸውን ውግዘት አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ ለቤተ ክርስቲያን አይበጅም፡፡ አባቶቻችን ችግሮችን በብስለት አይተው ነገሮችን መስመር ማስያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ምዕመናን መረበሽና መቸገር የለባቸውም፡፡ አባቶቻችን ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉት ቤተ ክርስቲያን አንድነቷ የተጠናከረ፣ ፍቅሯ የተገለጠ፣ የወቅቱን ፈተና ማሸነፍ የምትችል ቤተ ክርስቲያን እንድትኾን እንፈልጋለን፡፡ የተወገዙ አባቶችን ደግሞ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ወደ መዋቅሩ ገብተው ከአባቶች ጋር ተመካክረው በዋናው የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠራት ያለበት ነገር ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ እያነሱ እየተናገሩ እኛ ልጆቸው እንድንተገብረው ቢያወርዱልን እንደአንድ የቤተክርስቲያን ልጅ ትልቅ ምኞቴ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሕግና ደንብ አክብሮ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ያን ያላከበረ የእምነቱ ተከታይ ወንጀለኛ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ደግሞ የሕግ ምንጭ ናት፤ ልጆቿ ሕግ አክብረው መዋቅር ጠብቀው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ አባቶቻችንም በዚህ አግባብ እንዲተው ነገሮችን እንዲያስተካክሉ ቅዱስ ሲኖዶስ በከፈተው የይቅርታ በር  ተጠቅመው ምዕመናኑም ይቅርታ ጠይቀው ወደ መስመር ቢገቡ ብዬ በግሌ እመከራለሁ፡፡

መንግሥታችንን በተመለከተ ሀገር እየመራ የሚገኘው አካል እሱ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ አለበት፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገውን ነገር ተደራሽ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡ ከሚፈልገው ነገር ደግሞ አንዱ ኃይማኖት ነው፡፡ ስለዚህ ኃይማኖታዊ ጉዳይ መዋቅሮችን መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ለመዋቅሩ ፈተና የኾኑ ነገሮችን ሁሉ መንግሥት መፍታት ይኖርበታል፡፡ በውሳኔና አካሄዳችን ላይ ጣልቃ ሳይገባ ከሌሎች ጉዳዮች ላይ ግን ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ በመንግሥት በኩል የሚታዩ ነገሮችን መስተካከል አለባቸው፡፡ መንግሥት የቤተክርስቲያኒቱን መዋቅር ማክበር አለበት፡፡ ቤተክርስቲያን አንድ ኾና የራሷን ችግር እንድምትወጣ መታወቅ አለበት፡፡ ችግሩ የቤተክርስቲያን ችግር በመኾኑ እራሷ እንድትፈታው እድል መስጠት ይኖርባታል፡፡ አንዱን እስር ቤት አንዱ ማጀብ ለሕዝብም ለሀገርም የሚጠቅም አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን አንድነት ይጎዳል፡፡ ቤተክርስቲያን ሀገር ናት እየተባለ የሚነገረውን መንግሥት በተግባር ያሳየን ማለት እፈልጋለሁ፡፡

ከዚያ ውጭ ሁሉም በየደረጃው ያለ የመንግሥት መዋቅር ሕዝብ የሚፈልገውን እንዲመርጥ መተው አለበት፡፡ አሁን ያለው አካሄድ ደስ የሚል አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ፈተና ያለበት ሕይወት ስለኾነ እግዚአብሔር እስከፈቀደበት ጊዜ ድረስ በማስተዋል ዋጋ የሚያስከፍልም ከኾነ ልንቀበል ነው ወንበር ላይ የተቀመጥነው፡፡ በጥቅሉ የመንግሥት አካላት በማስተዋል እንዲሄዱ ከፍተኛው አካል መመሪያ ማስተላለፍ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሕዝቡም ለሀገር ሰላምና አንድነት ሲል ከስሜት በጸዳ መልኩ ነገሮችን በማስተዋል የአባቶችን መመሪያ እየዳመጠ መሄድ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በስሜት የሚኾን ነገር ጎጂ ነው፡፡ ሁሉም የቤተክርስቲያን ልጅ በመኾኑ በመነጋገርና በመናበብ በጸሎት ጭምር ታግዘን ችግሮቻችን መፍታት አለብን፡፡ ታሪካችን ውስጥ ጠባሳ እንዳያጋጥም ወንድሞቻችንን በዚህ ምክንያት እንዳናጣ በተቻለ አቅም በፍቅር በጸሎት በአንድነት ኾነን የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ሰላም ጠብቀን በቤታችን ውስጥ ይህንን ጊዜ መዝግበን ችግሮቻችን ፈተን ወደፊት ለሚመጣ ችግር ማጣቀሻ የሚኾን ጥሩ ታሪክ ጥለን ማለፍ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም እናመሠግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...