ብልጽግና ፓርቲ በአምሥት ቀናት ውስጥ ብቻ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ከ 37 ሺሕ 500 በላይ ሰዓታትን ማባከኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ፓርቲ(ኢዜማ) ማክሰኞ፣ ታህሳስ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
“በመንግሥት የሥራ ሰዓት እና ሃብት የፓርቲ ስብሰባ የማድረግ አባዜ መሠረታዊ የሕግ የበላይነት ድንጋጌዎች ተጥሰዋል፤ ዜጎችም ዕለታዊ አገልግሎት ተነፍገው የመልካም አሥተዳደር በደል ደርሶባቸዋል” ብሏል ኢዜማ።
“በአንድ ወረዳ ውስጥ በአማካይ እስከ 300 የመንግሥት ሠራተኞች እንዳሉ ፓርቲያችን ባደረገው የመረጃ ማጣራት ተገንዝቧል” ያለው የኢዜማ መግለጫ፤ በዚህም መሠረት ፓርቲያችን አዲስ አበባ በሚገኙ አስር ወረዳዎች ባደረገው ምልከታ ሠራተኞቹ በሥራ ሰዓታቸው ሊያሳልፉት ከሚገባው ከግማሽ በላይ የሆነውን የሥራ ሰዓት ለፓርቲ ስብሰባ መዋሉን መመልከቱን ገልጿል።
በዚህ መሠረት በእነዚህ ወረዳዎች በአማካይ 150 የሚሆኑት ሠራተኞች ከ 37,500 በላይ ሰዓታትን በዐምስት ቀናት ብቻ እንዳባከኑ ለመረዳት መቻሉን ኢዜማ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
“ይህ አይነት ስብሰባ በተለያዩ ደረጃዎች እንደሚደረጉ በገዢው ፓርቲ የተለያዩ የማኀበራዊ ትሥሥር ገጾችና ሚዲያዎች እየተገለጹ መሆኑን ወስደን ስሌቱን ከ5000 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ያሉባቸውን ተቋማት ከመረመርን ደግሞ የሚባክነው ሰዓት መጠን ብዙ መሆኑ እና አገልግሎት ማግኘት የሚገባው ማኅበረሰብ ምሬት ምን ያህል እንደሆነ መገመት አዳጋች አይደለም” ሲልም ኮንኗል።
“የመንግሥትን የሥራ ሰዓት ለፓርቲ ሥራ ማዋል ሳያንስ የተበደሉት የሥራ ሰዓታት እና የተጉላላው አገልግሎት ፈላጊው ማኅበረሰብ እንግልት አንፃር ስንመዝነው ጥፋቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል” ያለው ኢዜማ በመግለጫው፤ ዜጎች በአመለካከት የሚመስላቸውን የፖለቲካ ድርጅት የመደገፍ መብታቸው ላይ ምንም ዓይነት ብዥታ የሌለበት ቢሆንም በሕዝብ ግብር የሚተዳደሩ የመንግሥት ተቋማት የአንድ ድርጅት ተቀጥላ እንዲኾኑ ጫና ማድረግ ግን በሕግም ሆነ በሞራል ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስገንዝቧል።
“ብልጽግና ፓርቲ ትምህርት ያልወሰደው ከኢሕአዴግ ብቻ አይደለም፤ ከአምስት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ የምርጫ ወቅት መቃረብን ተከትሎ መንግሥታዊ መዋቅርን እና ሀብትን ባልተገባ መንገድ ለእራሱ ጥቅም በማዋል ሕገወጥ ስብሰባ ያደርግ የነበረ ሲሆን ከዚህ ተግባሩ ከመቆጠብ ይልቅ እንደውርስ ሃጢያት ይዞ መንጎዱን ያሳያል” ሲልም ብልጽግናን ከሷል።
“ይህም ብልጽግና ፓርቲ ለዴሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነትና ለዘላቂ የሕዝብ ጥቅም ደንታ እንደሌለው የሚያሳይ አሳፋሪ ድርጊት ነው” ያለው ኢዜማ፤ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ላለው ሕዝብ በአካባቢ ምርጫ ወኪሎችን ከመረጠ ከ 20 ዓመታት በላይ መቆጠራቸውንም አስታውሷል።
መሠረታዊ የፌደራሊዝም መገለጫ የኾነው የዜጎች በታችኛው መዋቅር የመወከል መብት ባልተጠበቀበት በዚህ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ የሚያደርገውን ተጨማሪ በደል ቆም ብሎ እንኳን ለማሰብ አለመቻሉ የበለጠ ድርጊቱን አሳፋሪ ያደርገዋል ሲልም ፓርቲው በመግለጫው ብልጽግናን ኮንኗል።
“አሁንም በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ እንዳሳወቅነው ሁሉ ፓርቲው ከዚህ እና መሰል ተግባሮቹ እንዲቆጠብ ጥሪ እናደርጋለን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህንን ጉድይ በአንክሮ በመከታተል ከዚህ ድርጊቱ እንዲያስቆም እንጠይቃለን” ሲልም ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዜጎች ከአገልግሎት ጋር የተገናኘ በደልን ከፍ ባለ ደረጃ በመከታተል ብልጽግናን ተጠያቂ እንዲያደርግም ኢዜማ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
ምንም እንኳን ኢዜማ ይህን ቢልም የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባዎቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን በተለያዩ አማራጮች ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡
