
ዓይናለም ደበበ
ካለፈው እትም የቀጠለ…
አልፎ ተርፎም ከሀሰተኛ ከሳሾች ዘንድ በቆሙ፣ ለሀገር ፍቅርና ለወገን ክብር አንዳች እንኳ ሐሳብ በሌላቸው፣ ተንኮላቸው እንዲሰምር እንደናዝራዊ ሰው የተጎሳቆሉ በሚመስሉ ‘የሃይማኖት ሰባኪያን’ ተመስገንና ጓደኞቹ ተወነጀሉ። እነኚህ ሰባኪያን እነ ተመስገን የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን በሌላ ለመቀየርና ለማጥፋት እንደተነሳሱ ያህል በማስመሰልም በየአደባባዩ ላይ ዘለፏቸው። ሰባኪያኑ ጨርሶውኑ ከሃይማኖት መርህ እና አስተምህሮት አፈንግጠው ለሃይማኖቱ ቀናኢ የሆነውን ምእመን ንቀው፣ በሀሰት ሲዳክሩ ውለው እያደሩ ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ክብር አጥብቀው የሚከራከሩትንና ህይወታቸውን ጭምር አሳልፈው የሰጡትን እነ ተመስገንን ያለ ኃፍረት ወነጀሉ። ከሕዝቡ ሊነጥሏቸው ላይ ወጡ ታች ወረዱ።
ከዚህም በኋላ ተመስገንና ጓደኞቹ ሕዝብ በተሰበሰበበት ማንኛውም አደባባይ ላይ ምንም አይነት ንግግር እንዳያደርጉ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ትእዛዝ ተከለከሉ። ከዛ ሁሉ ውርጅብኝ በኋላ ከንጉሠ ነገሥቱ የተላለፈው መልዕክት ለተመስገን እጅግ ፈታኝ ነበር። ቢሆንም ግን እውነተኛ ሀገር ወዳድ ምን ያህል መከራ ቢገጥመው በሀገሩ ተስፋ ሊቆርጥ አይቻለውምና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ መልካም ቀንን እያሰበ፣ ብሩህ ተስፋን እያለመ ረዥም ግዜን በመከራ አሳለፈ። ችግር ባለበት ሁሉ መፍትሔም ባንድነት ይኖራልና በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ላይ በእስልምና እምነት ተቋም ባለ መድረክ ላይ ስብከት ለማካሄድ ባለመከልከሉ ተመስገንና ጓደኞቹ ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም ሸሪፍ አፈንዲና ሙሚ ዮሱፍ የተባሉ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችን ፍቃድ በመጠየቅ ከየትኛውም የሃይማኖት መርህና አስተምህሮት ጋር ስለማይቃረነው ስለ ሀገር ፍቅርና አንድነት የጀመሩትን ስብከት ቀጠሉ። ከዚህም በኋላ የተዘጋው በር መከፈት ጀመረ።
“በእስላሞች ጀማ ያደረግነው የአንድነት ስብከት በከተማው በተወራ ግዜ ለከተማይቱ መልካም የመንቀሳቀስ መንፈስ ሰጠ። እንደሚድህ ትንሽ ህፃን ይወድቅና ይነሳ የነበረው አዘናችን ወደ አለቄታው በር ላይ ሊደርስ እንደቀረበ ለማወቅ የመንግሥት ትእዛዝ ነውና ከንግዲህ በፍርድና በፀሎት አደባባይ ስብከት እንዳታደርጉ ብለው በማስጠንቀቅ የነገሩን ዋና ዋና መኳንንቶችና የቤተ ክርስትያን ታላላቅ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ግዜ በኋላ ሀሳባቸው እንደተለወጠ አየን። በእርግጥ እንደተፀፀቱ ከነርሱ ጥቂቶቹ ከየፅሕፈት ቢሮዋቸው ነገሩን።” በማለትም ተመስገን በግለ ታሪኩ ላይ ተርኳል። ከዚህ በኋላ ጣልያን ለ40 ዓመት ያህል አድብታ ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር ዝግጅቷን አጠናቃ እንቅስቃሴዋን ስትጀምር ሁለት አይኑን ጨፍኖ እንቅልፉን ሲለጥጥ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በድንገት ባነነ። ከአርባ ዓመት በፊት በእምዬ ምኒልክ የአመራር ልህቀት ተፈጥሮ የነበረው አንድነት ግን በግዜው አልነበረም። የኢትዮጵያ መንግሥት ያለምንም ቁሳዊ ጥቅም በራስ ተነሳሽነት የሀገር ፍቅርንና አንድነትን ሲሰብኩ የነበሩ ግለሰቦችን ከሚያሳድዱት ጋራ እንዳልነበረ ሁሉ በጨነቀው ግዜ የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክር ማህበር ለማቋቋም በመሻት ለስራው ይሆናሉ የሚላቸውን ግለሰቦችን ማሰስ ያዘ። እንዲያም ሆኖ ግን ከመንግሥት ቢሮ ተሰግስገው ሀገርን ለሹመኛ በማሸርገድና በማሸብሸብ ብቻ ማገልገል የሚቻል የሚመስላቸውን ከንቱዎችን የሀገር ፍቅርንና አንድነትን እንዲያስተምሩ በማሰባሰቡ በግዜው የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ከተጨማሪ ስህተት ላይ ወደቀ። በዚህም የተነሳ የታለመው ውጤት ላይ ለመድረስ ባለመቻሉ ሹመኞች ጉዳዩን እንደገና መርምረው ስራውን ለተመስገንና ጓደኞቹ ለማስረከብ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከስምምነት ላይ ደረሱ። ቢሆንም ግን ግዜው ረፍዶ የጣልያን ጦር አይሎ አዲስ አበባ በመግባቱ ምክንያት ውጥኑ ሁሉ መና ሆኖ ቀረ።
በዶጋሊ፣ በአምባላጌ፣ በእንዳየሱስ እንዲሁም በአድዋ ላይ የኢትዮጵያውያንን ጡጫ ቀምሰው ተንገፍግፈው የተመለሱት ጣልያኖች ለበቀል አሰፍስፈው ነበርና ግዜ ቢሰጣቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ህፃን አዛውንት ሳይሉ እያሳደዱ በጥይት ቆሉት። ነፍሰጡር ህመምተኛ ሳይሉ ንፁሃንን አስረው በረሃብና በውሃ ጥም አቃጥለው ፈጁት። የሃይማኖት መሪ፣ የሀገር ሽማግሌ ሳይሉ ካሚዮን ላይ እንደ ጎማ የጭቃ መከለያ አስረው ከመሬት እየጎተቱ ክቡሩን የሰውን ልጅ አካል እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ገደሉ። ቅዱሳን ቦታዎችን ያለከልካይ በእሳት አጋዩ። ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ቦምብ እየወረወሩ ንፁሃንን በጅምላ ጨረሱ። ተመስገን ከበዛ መከራና ግፍ እንዲሁም ከጥይት እሩምታና ከቦምብ ፍንዳታ በፈጣሪ ቸርነት አምልጦ ቀሚስ ለብሶ ሻሽ ጠምጥሞ ከኩሬ ውሃ ልትቀዳ እንደወጣች ወይዘሮ እንስራ ተሸክሞ ለሊት በጨረቃ ብርሃን እያዘገመ ቀን እየተደበቀ የአባይን በረሃ አቋርጦ ጎጃም ከቤተሰቦቹ ዘንድ ቢደርስ አያቱና አራት ወንድሞቹ በፋሽስት ጣልያን ተገድለው፣ እናቱ መሪር ሀዘን ላይ ወድቀው አገኛቸው። እናቱን በዚህ ሁኔታ ያገኘውና ዘመዶቹን በሞት ያጣው ተመስገን ልቡ ተሰበረ። ሰው በመሆኑና በህይወት ቆይቶ እንዲህ ያለውን ሰቆቃ በማየቱ ፈጣሪውን አማረረ።
ተመስገን ከጣልያኖች ለመሰወር ከአዲስ አበባ ተነስቶ ከትውልድ ሀገሩ ደብረማርቆስ ከተማ ቢሄድም ጣልያኖች ግን ዱካውን እየተከታተሉ ይፈልጉት ነበርና ከሀዘንተኛ እናቱ ቤት ተሸሽጎ ለመቀመጥም ሳይችል ቀረ። በአጭር ግዜ ውስጥ ጣልያኖች በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ተንሰራፍተው ስለነበር ተመስገን በፋሽስቶች እየታደነ ከመኖር ህይወቱን ለማቆየት ወደሚችልበት ሱዳን ለማቅናት ተገደደ።
በስደት ህይወቱም እጅን አጣምሮ እየቆዘሙ ከመኖር በሱዳን የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ ትምህርት ሰጥቷል። በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ግለሰቦችና ተቋማት ጋራ ግኑኝነት በማድረግ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በማሳወቅ ፀረ-ፋሽስት ትግሉን አፋፍሟል።
ጃንሆይ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በጎበኙ ግዜ ተመስገን ተማሪዎቹን ‘የጥቁር አንበሳ’ የሚል መዝሙር አስጠንቶ በጃንሆይ የአቀባበል ስነስርዓት ላይ እንዲዘምሩ በማድረጉ ይሄን ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጀግንነት የሚያወሳውን መዝሙር እንግሊዞች አልወደዱም ነበርና ኢትዮጵያ ነፃ ስትወጣ ተመስገን ከጃንሆይ ጋራ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለስ እገዳ በመጣል የቁም እስረኛ ጭምር አድርገውት ነበር። ኋላ ግን በሱዳን የሚገኙ የኢትዮጵያና የኤርትራ ስደተኞች ተመስገን ሀገሩ የማይገባ ከሆነ እኛም አንገባም በማለታቸው እገዳው ሊነሳ ችሏል። ከዚያም በኋላ ሀገር ወደ ቀደመ ሰላሟ ስትመለስ ተመስገንም ከስደት ተመልሶ በልዩ ልዩ ስራዎቹ ሀገሩን አገልግሏል። “የኤርትራ ድምፅ” በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። በዚያን ግዜ ኤርትራ ገና ከጣልያኖች የቅኝ አገዛዝ አልተላቀቀችም ነበርና የሕዝቡን መከራ በመዘገብ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርጓል። በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተወዳጅ ፅሁፎችን ፅፏል። “የጉለሌው ሰካራም” የተሰኘውን አጭር የልቦለድ ታሪክ ለሕዝብ በማድረስ ፈር ቀዳጅ ሆኖ በኢትዮጵያ የስነፅሁፍ እድገት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ተመስገን ገብሬ ወ/ሮ ተከአ ገ/ሚካኤል ከተባለች የኤርትራ ተወላጅ ጋር በጋብቻ ተሳስሮ ሦስት ልጆችን ያፈራ ሲሆን ታህሳስ 15 ቀን 1941 ዓ.ም በ40 ዓመቱ ህይወቱ ሊያልፍ በቅቷል። ህይወቱ ያለፈውም በተመረዘ ምግብ እንደሆነም ይነገራል።
ተመስገን ለሀገሩ ጥቅም ደፋር፣ የሚያስበውን ነገር ከተግባር ለማዋል አንዳች የማይፈራ፣ ያመነበትን ነገር የሚናገርና የሚፅፍ፣ ነውረኞችንና ለሆዳቸው ያደሩ ግብዞችን አጥብቆ የሚኮንንና የሚቃረን፣ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት የሚሟገትና የሚዋደቅ፣ ዜጎች ስለ ሀገራቸው ታሪክ እንዲያውቁ ብሎም በሀገር ፍቅር ታንፀው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ቀንና ሌት የሚተጋ ነበር። ሀገራችን ኢትዮጵያ በአግባቡ ሳትገለገልባቸው ካጣቻቸው ብርቅዬ ልጆቿ መካከል አንዱ ተመስገን ገብሬ ነው። ዛሬ እንደ ባህል ምኒስትር ባለ ተቋም በቀላሉ ሊፈታ የሚችለውን እዚህ ግባ የማይባል ጉዳይ እንደ ችግር አንቀን፣ በአስተዳደር መዋቅር ላይ ሰንቅረን እንደ ሞኝ ይህን ሁሉ ዘመን ስናላዝን የኖርነው፣ ለመከራና ሰቆቃ እንዲሁም ለውርደት የተዳረግነው ትላንት ለተመስገን ገብሬና መሰሎቹ ‘አስተምህሮት’ የሰጠነው ግምት ትክክለኛ ባለመሆኑ ነው።
በቸር ያቆየን!