ቻይና በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ለዓለም ጤና ድርጅት 500 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች፡፡
ይህም ቻይና ለዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት ውስጥ በቀዳሚነት እንድትቀመጥ ያደርጋታል።
አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ታደርገው የነበረው ድጋፍ በማቋረጡ ቻይና ትልቋ ለጋሽ ሀገር ሆናለችም ነው የተባለው።
ቻይና ይህንን ሀሳብ ያቀረበችው በጄኔቭ እየተካሄደ በነበረው አለም አቀፍ የጤና ጉባኤ ላይ ሲሆን ድጋፉ ቻይና ከሌሎች ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ያላትን አቋም የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት አቅዶት የነበረውን የ2026 በጀት በ21 በመቶ በመቀነስ ወደ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ያደረገ ሲሆን ይህም በዋናነት በትራምፕ አስተዳደር በተወሰደው እርምጃ ምክንያት የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ነው ተብሏል።
የቻይና ውሳኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷ ለመጨመር እያደረገቸው ካሉ ተግባራቶች እንደ አንዱ ሊወሰድ እንደሚችልም የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ አመልክቷል፡፡
አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት መገለሏን ተከትሎ ቻይና እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ በዓለም የጤና ሴክተር፣ አየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የላትን ተጽዕኖ እንደሚያሳድግላትም ተነግሯል።
(EBC)
