በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ ከ 42 ሺ በላይ ዜጎች በጎርፍ እና በግጭት ምክንያት ተፈናቅለዋል።
በጋምቤላ ክልል ያሉ የሰብአዊ ተራድኦ ድርጅቶችም የተደራሽነት ችግር አጋጥሟቸዋል ተብሏል።
የተራድኦ ድርጅቶቹ የሰብአዊ ድጋፍን በተቀናጀ መልኩ ለማሰራጨት ማስተባበር ላይ ክፍተት እንዳጋጠማቸው ሰምተናል።
የጋምቤላ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ዳይሬክተር ጃክ ጆይ እንደገለፁት ድርጅቶቹ በሚጠበቀዉ መጠን እየሰሩ አለመሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም እነዚህን የሰብአዊ ተራድኦ ድርጅቶች የሚያስተባብራቸዉ ተቋም የ ተመድ የሰብአዊ ማስተባበሪያ ኦቻ ሲሆን ቢሮዉ ጋምቤላ ከተማ ላይ አለመሆኑ አንዱ ምክንያት እንደሆነ አንስተዋል።
ቢሮዉ መገኛዉ አሶሳ ላይ በመሆኑ ተቋማቱን ለሰብአዊ ድጋፍ ለማስተባበር ባለመቻል ክፍተት እየፈጠረ ስለመሆኑ የጋምቤላ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ በክልሉ 42 ሺህ 374 ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ የጎርፍ እና የግጭት ተፈናቃዩች በክልሉ አሉ ብለዋል።
በክልሉ ካቢኔ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስትራቴጂክ ኘላን ቢፀድቅም ለተግባራዊነቱ በጀት የማፈላለግ ስራዉን የአለምአቀፍ ተቋማት ያደረጉት የ ፈንድ ገደብ እክል ፈጥሯል ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዩ ኤፍም
