
“ትግራይ ለጦርነት እየተዘጋጀች ነው ” በሚል ስለሚሰራጨው መረጃ የክልሉ ጊዜያዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ረዳኢ ሓለፎም ” ይህ ውሸት ነው ፤ 24 ሰዓት ሙሉ ክልሉ እየሰራ ያለው ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ነው ፤ ጉዟችን ሁሉ ለሰላም ነው። ሰላሙ እንዲጠከር ስለምንፈልግ ነው ታጣቂ ኃይሉን እየቀነስን ያለነው ፤ ከአሁን ቀደም ከትግራይ በኩል ማውረድ የነበረብንን ትጥቅ በየጊዜው እያስረከብን መጥተናል በተፈራረምነው የሰላም ስምምነት ከትግራይ የሚጠበቁትን እያደረግን ነው ቀረ የሚባል ነገር ያለ አይመስለኝም ፤ በቀጣይነትም ይህን አጠናክረን ወደ ተሟላ ሰላም ለመሄድ የትግራይ በሮች ክፍት ናቸው። ጊዜያዊ አስተዳደሩ 24 ሰዓት እየሰራ ያለው ሰላሙን ለማፅናት ነው፤ ዘላቂ እንዲሆን ነው።”
አቶ ረዳኢ ሓለፎም
ትግራይ ቲቪ፣ ነሐሴ 6 ቀን 2015 ዓ.ም
“ሠራዊቱ ለሚነዙ የሃሰት ወሬዎች ጆሮ ሳይሰጥ ግዳጁን በታላቅ ተጋድሎና ጀግንነት እየተወጣ ነው። በየደረጃው የሚገኝ አመራር በየጊዜው የሚመራውን ሰራዊት አቅም የሚያሳድጉ ተግባራትን በማከናወንና ዝግጁነትን በማረጋገጥ አሸናፊነትን መገንባት ይኖርበታል፡፡ በስልጠና የተደገፉ አቅሞችን መፍጠር ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጡ ትንኮሳዎችን መመከትና ማሸነፍ የሚችል ሁሉን አቀፍ አስተማማኝ ዝግጁነት ይፈጥራል። በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን አቅም የማሳደግ አስፈላጊነቱን በመገንዘብ በዕዛችን ሁሉም ክፍሎች ስር ላሉ ምክትል መቶ አዛዦች የታቀደ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ የሀገራችንን ህልውና የሚፈታተኑ ሃይሎች ተደራጅተው ሠራዊቱ ላይ ጥቃት ቢከፍቱም ሰራዊቱ ለሚነዙ የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎች ጆሮ ሳይሰጥ በጥንካሬ እየመከተ የፀረ ሠላም ሃይሎችን ፍላጎት ማምከን ችሏል።”
ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሠረት፣ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ
ኢዜአ፣ ነሐሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም
“የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአሜሪካ ለወዳጅነት ጨዋታ አምርቶ ባደረጋቸዉ ጨዋታዎች በአሜሪካ ክለቦች መልማዮች እይታ ዉስጥ የገቡ ተጫዋቾች ዝርዝር ታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ሽመልስ በቀለ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ቢኒያም በላይ ፣ አቤል ያለው ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ረመዳን የሱፍ እና ማርከስ ቬላዶ-ፀጋዬ በልዩ ሁኔታ በመልማዮች እይታ ዉስጥ ገብተዉ ምልከታ ሲደረግባቸዉ ነበር። ከተጠቀሱት ተጫዋቾች ውስጥ ጋቶች ፓኖም እና አቤል ያለው ከዲሲ ዩናይትድ በተጨማሪ በሌላ አንድ ክለብ መልማዮች ተፈልገው ነበር፡፡ አቤል በክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውል ስላለው ጥያቄው ወደ ክለቡ እንዲሄድ አድርገን ውል የሌለው ጋቶች ፓኖም እዛው ቀርቶ ዕድሉን እንዲሞክር አድርገናል።”
አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ
ሀትሪክ፣ ነሐሴ 6 ቀን 2015 ዓ.ም
“መከፋፈሉ ላይ ብዙ ተቃውሞ የለኝም፡፡ አንድነቱ ራሱ በአንድ ጀንበር በአፈሙዝ ነው የተፈጠረው፡፡ ለ30 ዓመታት ቆይቶም ቢሆን በመከፋፈሉ ብዙ ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ ክልሎቹ ሲደራጁ ግን የሚደራጁበት ቀመር ነው በጥንቃቄ መሆን ያለበት፡፡ የሕዝቡ የልማት ጥያቄ ምንድነው? ከሕዝቡ ፍላጎት በተጨማሪ የየአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ያማከለ ልማትን ለማስፋፋት ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ የሰላም፣ የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪ፣ የአይሲቲና ሌላም ዓይነት ልማቶችን ማዕከል ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ አሁን በደቡብ አካባቢ እየተፈጠሩ ባሉ አዳዲስ አደረጃጀቶች እየታየ አይደለም፡፡ ያው የቀደመው የተለመደው ጎሳን ማዕከል ያደረገ የመዋቅር ክፍፍል ነው የሚታየው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ነው መቅረት ያለበት፡፡ የብሔር ክፍፍሉ ከ30 ዓመታት በላይ የተሞከረና እንደ አገር ከግጭትና መቆራቆዝ ውጪ አንዳችም ውጤት ያላገኘንበት መንገድ ነው፡፡ ደቡብ ክልል መከፋፈሉ ጠንካራ ክልልን ማፍረስ ነበር የሚለው አመክንዮ በሁለት ጎኑ ሊታይ የሚችል ነው፡፡”
አቶ ታረቀኝ፣ የሕግ ባለሙያ
ሪፖርተር፣ ነሐሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም
“ምርት ገበያ በበጀት ዓመቱ 24 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 257 ሺህ ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ምርቶችን አገበያይቷል፡፡ ግብይት ከተፈጸመባቸው 257 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምርቶች መካከል 75 ሺህ ሜትሪክ ቶኑ የአኩሪ አተር ምርት ነው። 62 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሰሊጥ እንዲሁም 57 ሺህ ሜትሪክ ቶኑ የቡና ምርቶች ግብይቱ የተፈጸመ ሲሆን፤ ቀሪውን የግብይት መጠን ሌሎች ምርቶች ይይዛሉ፡፡ ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓቱንና አገልግሎቱን በማሻሻል አርሶ አደሩን፣ አቅራቢው፣ የሕብረት ሥራ ማህበራትንና ላኪዎችን በማገልገል ላይ ነው፡፡ አገሪቱ ከውጭ ምንዛሬ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ዘመናዊ የንግድ ግብይት ሥርዓት በባህሪው ተለዋዋጭ በመሆኑ በጊዜው አዳዲስ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ምርት ገበያ የዓለም ገበያን ከግምት ውስጥ ያስገባ የአሰራር ማሻሻያና ለውጦችን አድርጓል።”
ነፃነት ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ
ኢፕድ፣ ነሐሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም
“ጽህፈት ቤቱ እያከናወናቸው ያሉ የግንባታ ሥራዎች ውል በታሰረላቸው የጊዜና የገንዘብ መጠን በእቅዳቸው መሠረት የተከናወኑ መሆናቸውንና 90 በመቶ ያህሉም በእቅድ መሠረት የተፈጸመ ነው:: በእስካሁኑ ሥራዎቹም አቅዶ የመፈጸም አቅም መፍጠር ተችሏል:: ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ በእቅዱ መሠረት ካከናወናቸው የግንባታ ሥራዎችም የታላቁ ቤተመንግሥት የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) እና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ህንፃ (የህንፃ ኮምፕሌክስ)፣ አብርኆት ቤተ መፃሕፍት፣ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት፣ በኮልፌና አያት አካባቢዎች የተከናወኑት የገበያ ማዕከላት ግንባታዎች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ክላስተር ለአብነት ይጠቀሳሉ::”
ኢንጂነር ምሬሳ ልኪሳ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ጽህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ
አዲስ ዘመን፣ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም
“የአማራ ክልል በርካታ ተፈጥሮአዊ፣ ባሕላዊ እና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ባለቤት ነው፡፡ እንደ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና የማእድን ዘርፎችም የእድገት ምንጭ ኾኖ እያገለገለ ይገኛል፤ የሥራ እድል በመፍጠርም ከፍተኛ ድርሻ ያለው ዘርፍ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግ በሠራው የማስተዋወቅ ሥራ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር እና ከጎብኝዎች የሚገኘው ገቢ እድገት ቢያሳይም በኮሮና ወረርሽኝ እና በሰሜኑ ጦርነት ዘርፉ መቀዛቀዝ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጅ ባለፉት ሰባት ወራት ዘርፉን ለማነቃቃት በተሠራው ሥራ 14 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል፡፡ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢም ማግኘት ተችሏል፡፡ ይሁን እንጅ አሁንም በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ አለመረጋጋት ለቱሪዝሙ ጥገኛ የኾኑ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ቆመዋል፤ ለዘርፉ መዳከምም ምክንያት ኾኗል፡፡ ዘርፉን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል፡፡”
አባይ መንግሥቴ፣ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ
አሚኮ፣ ነሐሴ 07 ቀን 2015 ዓ.ም
“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በከተማዋ በርካታ ፓርኮች እየተገነቡ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ፓርኮች ውስጥ አንዱ የሆነው በ36 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ የሚገኘው እንዲሁም 6 የግንባታ ሂደቶች እና የፒኮክ መናፈሻ የመጀመርያው የግንባታ ሂደት ተጠናቋል፡፡ በተመሳሳይ ከተማ አስተዳደሩ ከሚያስተዳድራቸው 11 ፓርኮች ውስጥ የከንቲባ ወልደጻድቅ ጎሹ ፤አምባሳደር እና አፍሪካ ፓርኮች የከተማዋን ደረጃ በጠበቀ መልኩ ግንባታቸው ተከናውኗል፡፡ ሌሎች የከተማዋን ፓርኮች ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከ1.5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የብሄረጽጌ መናፈሻን ዓለም ዐቀፍ ደረጃን ያሟላ እና ለዲፕሎማቶች የመዝናኛ አማራጭ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡”
አቶ ዘመኑ ደሳለኝ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ ነሐሴ 07 ቀን 2015 ዓ.ም