ሁሉንም ህዋሶቻችንን ከሀጢያት እና ከመጥፎ ተግባር ከምንከለክልበት ግዜ ውስጥ አንዱ የጾም ወቅት ነው፡፡ ጾም ልቅ የሆነ በዓይን የሚታየውን የስጋችንን ፍላጎት ሲያጠፋልን በጥልቁ ውስጥ ያለውን የነፍስን ጉድፍ ደግሞ በማንጻት ነገ ለሚጠብቀን ዘላለማዊ ሕይወት መወጣጫ መሳላል በመሆን ያገለግላል፡፡ መጥፎ ስሜት እየተሰማን መልካም መልካሙን እንድናስብ የሚያደርገን ጾም ነው፡፡ ጾም ከእንስሳዊ ባሕሪ አሊያም ከደመነፍሳዊ ያልተቀመረ የሕይወት አኗኗር አውጥቶ የሰው ልጅ መላዕክቶችን መስሎ የሚኖርበት ሕገ ሥርዓት ነው፡፡
ፈጣሪ ሥጋ ለብሶ የዓለምን ሕዝብ ለማዳን ከሰማያተ ሰማያት ወርዶ የእኛን መከራ ተቀብሎ 40 ቀን እና 40 መዓልት ጾሞ የጾምን ትሩፋት ለእኛ ልጆቹ ከማስተማሩ በፊት ሥርዓቱን ገና በጠዋቱ ለአዳም እና ሄዋን አስተምሯቸው ነበር፡፡ አዳም እና ሄዋን ገና በገነት ሳሉ ይህን እጸበለስ አትብሉ ብሎ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ያ ትዕዛዝ ጾም እንደነበር ምን ያህሎቻችን አስተውለነው እናውቃለን፡፡ የጾሙን ትዕዛዝ ሽረው ዕጸ በለሱን ከበሉ በኃላ ከምን ዐይነት ከፍታ ወርደው ገሀነማዊ ምድር ላይ እንደኖሩ አሁንም እሳቱ ላይ እንዳለን ወደፊትም ፈራጁ እስኪመጣ እሳቱ እንደሚቀጥል የሚታወቅ ነው፡፡ ይህን ማለፍ የሚቻለው በጾም እና በጸሎት ብቻ ነው፡፡
“ጾም” ጸሎት እና እንባ ታክሎበት ፈጣሪን የምንለምንበት የጽድቅ ሥርዓት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሀዲስ ኪዳን ስለ ፆም ብዙ ተብሏል፡፡
ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን፡- መጽ ኢያሱ 7፥6-9፣ መጽ አስ 4፥16፣ ትን ዮናስ 1፣ መጽ ሳሙኤል 12፥17፣ ዘዳግም 9፥9-18፣ ትን ኢዩኤል 1፥14፣ መዝ 34(35)፥13፣ ትን ዳንኤል 10፥2፣ መዝ 108፥2፡፡
በበሀዲስ ኪዳንም ስናይ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥራው ሁሉ መጀመሪያ ያደረገው ጾምን ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ የሚቀጥሉትን በሀዲስ ኪዳን ቅዱስ መጸሐፍ ስለጾም የተጻፉትን ምዕራፍ እና ቁጥሮችን እንመልከት፡- ማቴ 6፥16፣ ሉቃ 6፥21፣ ማር 2፥20፣ ሐዋ 13፥3 እነዚህን የመጸሐፍ ቅዱስ ቃሎች መሠረት በማድረግ ነው፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓመት ውስጥ ሰባት (7) አጽዋማትን አውጃ በሕጉ መሠረት ማንኛውም አቅሙ የሚፈቅድ የእምነቱ ተከታይ ጾሙን እንዲጾም ምታዘው፡፡፣ እነሱም፡-
1. ዐቢይ ጾም 5. ጾመ ድኅነት
2. ጾመ ሀዋሪያት 6. ጾመ ነነዌ
3. ጾመ ስብከት /ጾመ ነብያት/ 7. ጾመ ገሀድ
4. ጾመ ፍስለታ
ከተዘረዘሩት አጽዋማት ውስጥ ወቅቱ የዐቢይ ጾም ነውና ስለ ዐቢይ ጾም ጥቂት ላንሳ፡፡
ዐብይ የሚለው ቃል ‹‹አበየ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም (ከፍ አለ) እንደማለት ነው፡፡ ይህ በክርስትና እምነት ተከታዩ ክፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው ጾም ይህን ክብር ያገኘው በምክንያት ነው፡-
1. ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጾመው ጾም በመሆኑ፡፡
2. የቀኑ ብዛት ከሌሎቹ አጽዋማት ስለሚበልጥ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው 40 ቀንና 40 መአልት ነው፡፡ እኛ የምንጾመው ግን 55 ቀን ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በመሀል ያሉ 15 ቅዳሜ እና እሁዶች ስለማይጾሙ ነው፡፡ 55-15—40
3. ሌላው እና ዋነኛው በጾሙ ወቅት ጌታችን ታላላቅ የሳጥናኤል ፈተናዎችን እንዲሁም ሦስቱ ርዕሰ ሀጢያት ትዕቢት፣ ስስት እና ፍቅረ ንዋይ የሚባሉትን የዘመኑ ደም አፍሳሽ ጉዳዮችን በድል በመወጣቱ ይህ ጾም “ዐብይ” (ታላቅ) ተብሏል፡፡ ማቴ 4፥3-11
ዐቢያ ጾም ተጨማሪ ስሞች አሉት
ጾመ ሁዳዴ፡- ሁዳዴ ማለት ሰፊ/ትልቅ እርሻ ማለት ነው፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘው ብዙ ቀን ስለሚጾም ነው፡፡
የካሳ ጾም፡- በሰው ስሌት ለ5500 ዓመት በፈጣሪ ቀመር ደግሞ ለ5 ቀን ተኩል የሰው ልጅ በዲያቢሎስ ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ ይህን ግዞት ክርስቶስ ደሙን በመክፈል መላው የዓለምን ሕዝብ ነጻ ስላወጣው የካሣ ጾም ተባለ፡፡
የዐቢይ ጾም ስምንቱም ሳምንታት የራሱ የሆነ መጠሪያ አለው፡-
1ኛ ሳምንት፡- ዘወረደ 5ኛ ሳምንት፡- ደብረ ዘይት
2ኛ ›› ፡- ቅድስት 6ኛ ›› ፡- ገብርሔር
3ኛ ›› ፡- ምኩራብ 7ኛ ›› ፡- ኒቆዲሞስ
4ኛ ›› ፡- መጻጉእ 8ኛ ›› ፡- ሆሳዕና
በመጨረሻም ይህን ብዬ ላብቃ፡፡ ሀገራችን ላይ እየሆኑ ያሉት ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶችም ሆነ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ይህ ጾም ጥሩ ሰዓት ላይ የመጣ ነውና ሁሉም የሃይማኖቱ ተከታዮች አቅማችን በፈቀደ እንዲጾሙ እመክራለሁ፡፡
