በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመምህራንን ኑሮ የሚያሻሽል እና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ከዘመናዊው ትምህርት ጋር የሚያጣምር ፖሊሲ ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
የኢዜማ መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት የቀድሞው የፓርቲያቸው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሁኑ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴርን እየመሩ በመሆኑ በዘርፉ ጥሩ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ኢዜማ መንግስት ባለመሆኑ ምክንያት የጎደሉ ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የትምህርት አስተዳዳሪዎች የሚሾሙበት አሰራር ፖለቲካዊ መሆኑ የትምህርት ነጻነትን የሚጋፋ ነው ብለዋል።
ፓርቲያቸው በማኒፌስቶው ባካተተው የትምህርት ፖሊሲ የመምህራንን ብቃት እና የኑሮ ሁኔታ ማረጋገጥ፣ መሰረተ ልማትን ማሟላት እና የመጻሕፍት እጥረት ችግርን መፍታት ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፤ የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተጠባባቂ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበራ በቀለ በበኩላቸው፣ ፓርቲያቸው በሀገሪቱ ላለው የትምህርት ስርዓት አማራጭ መፍትሄ ይዞ መቅረቡን ተናግረዋል። አሁን ባለው የትምህርት አካሄድ ላይ ጥናት ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ አበራ፤ በሀገራችን ቋንቋዎች የተጻፉ በርካታ የሀገር በቀል የምርምር ዕውቀቶችን መጣላችን እንደ መሰረታዊ ችግር መለየቱን አብራርተዋል።
በመሆኑም እነዚህን እውቀቶች ከዘመናዊው ትምህርት ጋር ማጣመርና ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የልጆችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ትምህርት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው፣ ፓርቲያቸው ይህንን ያካተተ ፖሊሲ መቅረጹን አስታወቀዋል።
ፓርቲዎቹ የትምህርት ጥራትን ከሐገራዊ ነባር ዕውቀቶች ጋር ማጣመር እንደሚገባና ይዘዋቸው የመጧቸው አማራጮችም በጥቅም ላይ ከሚገኘው መርሃ-ትምህርት (ካሪኩለም) የተሻሉ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ፓርቲዎቹ ይህንን የገለጹት ለአሐዱ ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው።
