የግብር ሥርዓት ለአንድ አገር ዕድገትም ሆነ የመልካም አስተዳዳር ሥርዓትን ዕውን መኾን ወሳኝ ነው፡፡ ግብር የሠራና ገቢ ያገኘ ማንኛውም ሰው ባገኘው ልክ የሚከፍልበት፣ የሌለውም በዜግነቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት የአገር እሴት ነው፡፡ ግብር ‹‹ያለው ለሌለው›› የሚያስከፍልበት ፍልስፍና ነው፡፡ ግብርና ታክስ መክፈል ማለት የሕዝብንና የአገርን ደኅንነትና ሰላም ማስጠበቅም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም አገርና ሕዝብን ከፍ ወደ አለ ሥልጣን ማድረስ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ዕውን ሊሆን የሚችለው ግን ፍትሐዊ የግብር ሥርዓትና ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ አከፋፈል በመዘርጋቱ ብቻ ሳይሆን፣ በግብር መክፈል ስም ከሥራ መፈናቀል፣ ስደትና እንግልት ሲቆም ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን እየታየ ያለው የተለጠጠውን የመንግሥት የልማት ዕቅድና ፍላጎት ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ለማሟላት፣ መንግሥት ከብድርና ከዕርዳታ ከሚያገኘው በላይ ከዜጋው ገቢ ለመሰብሰብ ከመፈለጉ የተነሳ የተፈጠረ ይመሥላል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀን ገቢ ግምት ስም በርካቶች ከሥራ ወጥተዋል፡፡ የመንግሥት ዕዳ በመፍራትና በመሸሽ ከአገር የተሰደዱትም ጥቂት አይደሉም፡፡ አንዳንድ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ (በተለይ በአገልግሎት ሰጪ መስክ) ወገኖችም ሠርተህ ያላገኘኸውን ገንዘብ እንድትከፍል ከመገደድ ልመናና ሴተኛ አዳሪነት ወይም በምሬት መሰደድና መሸሽ በእጅጉ ይሻላል ብለው ኑሯዋቸውን ቀይረዋል፡፡ አስደንጋጩ ነገር ደግሞ በአንድ ዓይነት ሥራና ቦታ ወይም በተቀራራቢ የወጪና የገቢ መስክ አንዱ ግብር ብቻ ሳይሆን ቅጣትና ወለድ እየተጫነበት ሲገፈግፍ፣ ሌላው በኢ-ፍትሐዊነትና በማናለብኝነት በሕዝብ ሀብት የግል ኪሱን ሲያደልብ መመልከት፣ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ በተለይ እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ መጠጥ ቤቶችና በመሳሰሉት የግል ድርጅቶች ላይ የሚጣለው ግብርም ሆነ እንዲሰበስብ የሚፈለገው ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) የተጋነነ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡
በተቃራኒው በዐሥርና 20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የመኪናና ልዩ ልዩ ማሽነሪዎች መለዋወጫ የሚያስመጣ ሰው ግን ካፒታሉ ከ50 ሺሕ ብር ባይበልጥም (በአሠራሩ ክፍተትና በአድሎአዊነቱ መዘዝ) የሚናገረው የለም፡፡ በመቶ ሺዎች ብር ለሚፈጽመው ሽያጭም ደረሰኝ ቆረጠ አልቆረጠ አተኩሮ የሚያስተውለው የለም፡፡ እንዲያውም በገቢዎች መሥሪያ ቤት እየሠሩ ደመወዝና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም ያመቻቸላቸው ጥገኛ ሠራተኞች አማካይነት መረጃና ድጋፍ ስለሚደረግለት እያጭበረበረ በብልፅግና ይኖራል፡፡
መንግሥት እንዲህ ያለ የሕገ ወጥ ንግድ ተግባር የሚፈጸምበትን መርካቶና አካባቢዋ ላይ በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው የደረሰኝ የንግድ ሥርዓት ሀገራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ የሚኾነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ መርካቶ በአፍሪካ ትልቁ የኢኮኖሚ አቅም ነው። ለከተማችን ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገርም ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው ላቅ ያለ ነው። መርካቶ ትልቁ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት በመሆኑ በአግባቡ ከተመራ ያለውን አስተዋፅዖ ያህል በአግባቡ ካልተያዘ ደግሞ የንግድ ስርዓቱን ያዘባል። አብዛኛው ግብይት የሚፈፀምበት መርካቶ ህጋዊ የግብይት ስርዓት ካልያዝ በመላ ሀገሪቱ በሚሰራጩ ምርቶች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
ግብር የአንድ ሀገር መንግስት ለሚያከናውናቸው የልማት አሻራዎች መሰረት ነው፡፡ ይሄ አዲስ ነገር አይደለም። የነበረና የሚኖር ነው። የሚሰበስበው ግብር በትክክልም ለልማት እየዋለ ነው የሚለው ጥናት የሚጠይቅ ቢኾንም፣ ፍትሓዊ አሠራሮች ለማንበር የሚደረግ ጥረትን ማበረታታት ግን ጠቃሚ ነው፡፡ ይኽም ኾኖ ዜጎች በተሰማሩበት የንግድ ሥራ ላይ ተገቢውን ግብር ለመክፈል በመንግሥት በኩል ምቹ የኾነ አሠራር በመዘርጋት ረገድ እዚህም እዚያም የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸውን ደግሞ ጠቁሞ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ በየወሩ የገቢ ግብር ለመክፈል ከሚያጋጥማቸው መጉላላት ጀምሮ፣ ለቦታው የማይመጥኑ ሰራተኞች የሚፈጥሩት ችግር ግብር ከፋዩን የንግድ ማኅበረሰብ እያማረረ መኾኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በመኾኑም መንግሥት ኢ ፍትሓዊ የሚመስሉ አሠራሮችን መልክ ለማስያዝ እየሔደበት ካለው ርቀት ጎን ለጎን እንዲህ ያሉ አሠራሮችንም ማረቅ ይገባዋል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 220 ታህሳስ 12 2017 ዓ.ም
