10 ፈጣን ጥያቄና መልሶች
1. ዕለተ ዕሁድን ከማን ጋር ታሳልፋለህ? – ከጓደኞቼ ጋር፤
2. ኮከብህ? – ኤሪስ፤
3. ከእግር ኳስ የማን ደጋፊ ነህ? – ማን. ዩናይትድ፤
4. ከሙያህ የመውጣት ሃሳብ አለህ? – በፍፁም፤ አይደረግም፤
5. የአንድ ቀን ሥልጣን ቢኖርህ? ወዲያውኑ በፈቃዴ ሥልጣን እለቃለሁ፤
6. ከፊልምና ቲያትር የቱ ይመችሃል? – ቲያትር፤
7. መጠጥ ትወዳለህ? – በስሱ፤
8. ከዓለማችን የምታደንቀው አንድ ሰው? -………….
9. ሞቶ ዳግም በተነሳ የምትለው ሰው? አለቤ፤
10. ሎተሪ ቆርጠህ ታውቃለህ? አላውቅም፡፡
ዘላለም ኩራባቸው ተወልዶ ያደገው በሃዋሣ ከተማ ነው፡፡ የሃይስኩል ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሜጋ አድቨርታይዚንግ በ“ፍሪላንሠርነት” ወደ ማስታወቂያ ሥራ የገባው ዘላለም የሠዎችን ድምፅ አስመስሎ በማቅረብ በእጅጉ አድናቆት አትርፏል፤ በአሁኑ ወቅት የራሱን ማስታወቂያ ድርጅት ከፍቶ በመሥራት ላይ የሚገኘው ዘላለም ከዕንቁ አንባቢያን ለቀረቡለትና እኛም በመሃል ላነሣንለት ጥያቄዎች የሠጠውን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ዕንቁ፡- ሠሞኑን ከአዲስ አበባ ርቀህ ሠንብተሃል፤ ምክንያቱ ምን ነበር?
ዘላለም፡- መጀመሪያ ወደ ድሬዳዋ ነበር የሄድኩት፤ በመቀጠል ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ላይ የማቀርበው ሥራ ስለነበረኝ ወደ መቀሌ ሄጃለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀሌን በመመልከቴ በጣም… በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ “ለካ መቀሌ እንዲህ ናት?” እስከምል ድረስም ተደምሜያለሁ፡፡ ጥሩ ጊዜ አሣልፌም መጥቻለሁ፡፡
የወንድሞችና እህቶችህ ብዛት የአንድ እግር ኳስ ቡድን እንደሚሞላ አውቃለሁ፤ እስቲ ስለ ቤተሠቦችህ አጫውተን፡፡
ልዑል ግርማ (ከሃዋሣ)
ዘላለም፡- ከአንድ እናት ከአንድ አባት… አሥራ አንድ ልጆች ነው የተወለድነው፡፡ 11ኛውና የመጨረሻው ልጅ እኔ ነኝ፡፡ እኛ ቤት ውስጥ ጨዋታ፣ ፍቅር፣ ደስታና ተግባቢነት ተዝቆ አያልቅም፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ቤተሠብ መውጣቴ በሕይወቴ ላይም ተፅዕኖ አለው፡፡
ትምህርት ቤት ውስጥ ምን ዓይነት ተማሪ ነበርክ?… የአሁኑ ሙያህን ትምህርት ቤት ሳለህ ትሞካክረው ነበር?
ሠዓዳ አሊ (ኢ-ሜይል)
ዘላለም፡- ትምህርት ቤት ውስጥ ከብዙዎቹ ጋር ነበር የምግባባው፡፡ በኪነጥበብ እንቅስቃሴዎች ላይም ቁጥር አንድ ተሣታፊ ነበርኩ፡፡ ከ9-12ኛ ክፍል በተማርኩበት ትምህርት ቤትም የሚኒ ሚዲያ አቅራቢና አዘጋጅ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች ላይ የጉልበቱን ሣይሆን የሞራል ማነቃቂያውን እኔ ነበር የምሠራው፡፡ በሀዋሣ ጥሩ የልጅነት ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡
ዕንቁ፡- ከሀዋሣ እንደመጣህ ነው “አለቤ ሾው” ፕሮግራም ላይ የቀረብከው?
ዘላለም፡- መጀመሪያ በሬዲዮ ነበር የቀረብኩት፡፡ ድሮ የኢቲቪ ሕብረ ትርዒት ወይም 120 ፕሮግራም ካየሁ በኋላ የሠዎቹን ድምፅ አስመስዬ በመድገም አቀርብ ነበር፡፡ ሠኞ ተማሪዎቹ እኔን ነበር የሚጠብቁኝ፡፡ በዚያ ውስጥ ነው ያደግኩት፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ የአካባቢዬን ሠዎች ድምፅ በማስመሠል መሥራት ቀጠልኩ፡፡ እያደገና እየሠፋ መጣና የሦስት ሠዎችን ድምፅ አስመስዬ በሬዲዮ ቀረብኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው “አለቤ ሾው” የቀረብኩት፡፡ አለቤ… በጣም… በጣም የምወደው ባለሙያ ነበር፡፡ ሁላችንም አጥተነዋል፡፡ …እኔ ዕድሜ ልኬን በአለቤ ስስቅ ነው የኖርኩት፡፡ እርሱ ያገኘኝ ቀን ደግሞ እየሳቀ ወደ እኔ ሲመጣ ገረመኝ፡፡ እየሣቀ መጥቶ በቲቪ አቀረበኝና ይኸው ዛሬም ድረስ መነጋገሪያ ሊሆን ችሏል፡፡
ዘላለም ከቤተሠቦቹ ልጆች ለእናቱ የተለየ ፍቅርና ቀረቤታ አለው ሲባል ሠምቻለሁ፡፡ አንተ ከሌሎቹ ተለይተህ የተጠቀስክበት ምክንያት ምንድነው?
እቴቱ ምናለ
ዘላለም፡- ለእናቴ የመጨረሻ ልጇ እኔ ነኝ፡፡ ልጅ ሆኜ አባቴ ስለሞተ ያለ አባት ነው ያሣደገችኝ፡፡ ለዚህም ነው የተለየ ቅርበት የፈጠርነው፡፡ እናታችን ብዙ ነገር ሆና ነው ሁላችንንም ያሣደገችን፡፡ እኔንና ቤተሰቦቼን ጨምሮ ልጆች እንድንሆን፣ ራሳችንን እንድንችል ያደረገችን፣ ቆንጆ ፍቅር የሠጠችን እናት አለችን፡፡ በዚያ ላይ በጨዋታ እናቴ ከእኔ ትበልጣለች እንጂ አታንስም፡፡
ዕንቁ፡- እናትህን በዚህ አጋጣሚ ምን ትላቸዋለህ?
ዘላለም፡- ምን እላለሁ?… እንዲያው ዝም ነው፡፡ በሆዴ ነው የምገልፅላት፡፡
ካንተ ሙያና ባሕርይ ጋር የሚመሳሰል ቀረቤታ ያላቸው ወንድሞች አሉህ?
ዮሐንስ ጌታነህ (ከቄራ)
ዘላለም፡- ሙያውን እንደ እኔ አድርገው ወደ ሚዲያ አላወጡትም እንጂ የእኛ ቤት ሁሉም ልጆች ተጫዋቾችና ተግባቢዎች ናቸው፡፡ ወደ ሚዲያው የወጣሁት እኔ ብቻ ልሁን እንጂ ብዙዎቹ ተሠጥኦ አላቸው፡፡
ዘላለም የራስህን ማስታወቂያ ድርጅት መቼና እንዴት ነው የከፈትከው?
ሃብታሙ ብርሃነ (አዲስ አበባ)
ዘላለም፡- የማስታወቂያ ድርጅቴ “ዘኩራ አድቨርታይዚንግ” ይባላል፡፡ ዘላለም ማስታወቂያ ድርጅት ማለት ነው፡፡ ከማስታወቂያዎቹ በተጨማሪ ጥናታዊና ዘጋቢ ፊልሞችን ይሠራል፡፡ በርካታ ክሊፖችና በቅርቡ ለዕይታ የሚበቁ ፊልሞችም በእኔ ስቱዲዮ ተሠርተዋል፡፡ በተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወረ የመዝናኛ ዝግጅቶችን እንዲሁም የታላላቅ ኩባንያዎችን ፕሮፋይልም ጭምር ይሠራል፡፡ የሀዋሣን 50ኛ ዓመት በተመለከተ እዚያ ጊዜያዊ ቢሮ ከፍተን ነበር፤ አሁን ግን ፕሮጀክቶችን ወስጄ እየሠራሁ ነው፡፡ ዋናው ቢሮአችን ባምቢስ ግሪክ ት/ቤት ፊትለፊት አፔክስ ሕንፃ 1ኛ ፎቅ ነው፡፡
ዘላለምን በተለየ የሚያስደስተው ምንድነው?
ሐሮን ሃድጉ (ከመገናኛ)
ዘላለም፡- በጣም የሚያስደስተኝና የምወደው ሙዚቃን ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን እሰማለሁ፡፡ ጭንቀት አልወድም፡፡ ከሰዎች ጋር ተግባብቶ በማዳመጥም በመናገርም አሪፍ ጊዜ ማሳለፍም ያስደስተኛል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየትም እርካታን ይሰጠኛል፡፡ በጎ አመለካከትና ነፃ አስተሳሰብ ይመቸኛል፡፡
ጓደኞችህ ቀልደኛ መሆንህን እና ጥሩ ኮሜዲያን ልትሆን እንደምትችልም ይመሰክራሉ፤ ይህን የሚሉት ደግሞ አብረሃቸው ስትሆን ጥርስ ስለማታስከድን ነው፡፡ ቀልዶቹ ከጓደኞችህ ጋር ስትሆን ብቻ ነው የሚመጣልህ? ካልሆነስ ከአስመስሎ ማቅረብ ሥራህ ባሻገር ወደኮሜዲያንነት ያልገባኸው ለምንድነው?
ትዕግስቱ ልጅዓለም (ከቦዲቲ)
ዘላለም፡- ብዙዎቹ ጓደኞቼ የኮሜዲ ተሰጥኦ እንዳለኝ ያውቃሉ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየፈጠርን የምናቀርባቸው ቀልዶች አሉ፡፡ በኮሜዲው ዘርፍ አንድ ቀን ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ይዤ እንደምቀርብ ፈፅሞ አልጠራጠርም፡፡ መሥራትም እችላለሁ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ስንጨዋወት በእኔ ደስተኞች ናቸው፡፡ ማንኛውንም ከወቅቱ ጋ የሚሄዱ ጨዋታዎች እንጫወታለን፡፡ እኔም ተሰጥኦው አለኝ ብዬ አምናለሁና ወደፊት በፕሮፌሽናልነት መምጣቴ አይቀርም፡፡
ዕንቁ፡- የኮሜዲ ሥራውን ብቻህን ለመሥራት ነው የምታስበው ወይስ አብረህ ለመሥራት ያሰብከው ሰው ይኖራል?
ዘላለም፡- በሀገራችን ብዙ ኮሜዲያኖች አሉ፡፡ ለምሳሌ መኮንን ላዕከን እኔ በጣም እወደዋለሁ፡፡ ክበበው ገዳ ደግሞ በጣም አሪፍ ኮሜዲያን ነው፡፡ ተስፋዬ ካሣ አንደኛና ምትክ አልባ ኮሜዲያን ነበር፡፡ እናም በግልም በጋራም የምሠራቸው ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
አሁን በምን ሥራ ላይ ተሰማርተህ ነው ያለኸው?
አበራሽ ገነቱ (ከይርጋጨፌ)
ዘላለም፡- በዋነኝነት ማስታወቂያ ነው የምሠራው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በሚዲያዎች ላይ እየተጋበዝኩ ድምፅ ማስመሰልን እሠራለሁ፡፡
ዕንቁ፡- ማስታወቂያዎችን በሌሎች ሰዎች ድምፅ አስመስለህ ትሠራለህ፤ አንዳንዴ ይህ ድምፅ የዘላለም ነው ወይስ የሌላ ሰው እስከማለት ያጠራጥራሉ፤ የሌሎች ማስታወቂያ ባለሙያዎችን ድምፅ አስመስለህ ማስታወቂያ መሥራቱን አልተውከውም?
ዘላለም፡- ብዙ ሰዎች ድምፃቸውን አስመስዬ በመናገሬ ቅር ይላቸዋል፡፡ አንዳንዴ በወዳጄ በሳምሶን ማሞ ድምፅ ነው እያስመሰልኩ የማቀርበው፡፡ ይህን ደግሞ ራሱ ነው የፈቀደልኝ፡፡
በሀዋሳ ከተማ የልጅነት እድሜያችንን አብረን አሳልፈናል፤ ከተማችንን ለማያውቁ ሰዎች ሀዋሳን እንዴት ትገልፃታለህ?
ነጋሽ ሌራሞ (ከሀዋሳ)
ዘላለም፡- ሀዋሳ የእኔ ብቻ አይደለችም፡፡ የማንም ከተማ ናት፡፡ ዛሬ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ ብሎ መኩራራት የቀረ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ሀዋሳ የኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ዋና ከተማ ናት ማለት እደፍራለሁ፡፡ ከየትም ቦታ የመጣ ሰው በነፃነት የሚንቀሳቀስበትና የሚተነፍስባት፣ አንዴ ከጎበኟት ደጋግመው የሚመላለሱባት የሁሉም ከተማ ናት፡፡ በመተሳሰብና በመፈቃቀር የሚኖርበት ቦታ ናት፡፡ አስተዳደጌ ሃዋሳ እንደመሆኑ በግልፅነት፣ በመዋደድ፣ በመተሳሰብ የሚኖርባት የአንድነት ከተማ መሆኗን መመስከር እችላለሁ፡፡ የፍቅር ከተማ ናት፡፡
በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ በመጣው የፊልም ቢዝነስ ውስጥ የመሥራት ሃሳብ አለህ? የሀገራችንን ፊልሞችንስ ትከታተላለህ?
ኃይሉ ወ/ገሪማ (ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ)
ዘላለም፡- በቅርቡ ሦስት ሰዎች የተለያዩ የፊልም ስክሪፕቶችን አምጥተውልኝ ነበር፡፡ እኔም ተደብቆ ያለ ችሎታ ካለኝ አውጥቼ የምሠራበት ጥሩ የሚባል ስክሪፕት ካገኘሁ ወደፊልም ለመግባት ሃሳቡ አለኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየታየ ያለው የፊልም እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳየው እድገት መልካም የሚባል ነው፡፡ የፊልሞችን ርዕስ መዘርዘር ባያስፈልግም በርካታዎችን ተመልክቻለሁ፡፡ ፊልሞቻችንን እያሳዩት ያለው ለውጥ እየተሻሻለ ቢሆንም አሁንም የተሻለ ቴክኒክና የተሻለ ታሪክ ይዘው መምጣት ከቻሉ ደግሞ እድገቱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ የካሜራና ሌሎች ዘመናዊነትን መከተልንም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ታሪካቸው ወደሀገራዊ ጉዳዮች ሊያተኩር ይገባል፡፡ በአንዳንዶቹ እንደታየው የሚሠሩት ፊልሞች ከነጮቹ ባይኮረጁና ድንግል የሆነ የራሳችንን ታሪክ ይዘው ቢነሱ የተሻለ ነገር ይታያል፡፡ ቀድሞ ባልተለመደ ሁኔታ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የተለያየ ሲዝንና ክፍል ያላቸው ድራማዎችን በማቅረቡ ከቀጠለ በፊልሙ ላይ ተጨማሪ መነቃቃት ይፈጥራል፡፡
ዕንቁ፡- “ሰው ለሰው” ድራማ ላይ “ምስጋና ለዘላለም ኩራባቸው” የተባለው በምን ተሳታፊነትህ ነው?
ዘላለም፡- ደራሲው መስፍን ጌታቸው ለእኔ በጣም ወዳጄ ነው፡፡ እና የድራማውን ቀረፃ በሀዋሳ ከተማ ማከናወን ፈልገው እኔን ያነጋግሩኛል፡፡ እኔም ስፖንሰሮችን አመቻችቼ ቀረፃውን እንዲያከናውኑ አደረግኩ፡፡ ጥሩ ጊዜ አሳልፈንም ሥራው ተሳክቷል፡፡ በቀጣይነትም የፕሮሞሽኑን ክፍል ስፖንሰር አፈላልገን ለመሥራት ተስማምተናል፡፡
በሚዲያዎች ላይ እንደሌሎች ማስታወቂያ አውሪዎች ምስልህ አይታይም? ከዚህ የራቅበት ምክንያቱ ምንድነው?
ሽጉ አየለ (ከአ.አበባ)
ዘላለም፡- አንድን ማስታወቂያ እኔ ስለሠራሁ የግድ የእኔ ምስል መታየት የለበትም፡፡ የኔ ገፅታ መታየት የሚያስፈልግበት ቦታ ላይ እገባለሁ፡፡ በሠራሁት ማስታወቂያ ላይ ሁሉ ግን የእኔ ምስል አያስፈልግም፡፡ በዚያ ላይ ቆጠብ ልበል ብዬም ነው፡፡
ትዳር መስርተሃል? ልጆስ አፍርተሃል? አጠቃላይ የቤተሰብ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዳማ ሮሪሳ (ከወልመራ)
ዘላለም፡- ስም፡- አቶ ዘላለም ኩራባቸው ወልዴ
የቤተሰብ ሁኔታ፡- ያላገባ (ወንደላጤ)
ጸሎት፡- በአሁኑ ወቅት የማልመታት፣ የማልፈታት ሚስት ይሰጠኝ ዘንድ አምላኬን በመማፀንና በጸሎት ላይ እገኛለሁ፡፡
ልጅ፡- ልጅ የገና ዳቦ አይደለ… ተጠፍጥፎ አይሠራ፣ ሚስትየው ከመጣች በኋላ ልጁ ይቀጥላል… እያለ… እያለ… ይቀጥላል፡፡ አሁን ገና ጨዋታ መጣ፡፡
ሰለሞን አስመላሽ በኢቲቪ 3 በሚያቀርበው አዲሱ “እስማማለሁ፤ አልስማማም” ፕሮግራም ከቀረቡት መሃል ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ያገኘኸው አንተ ነህ፡፡ ገንዘቡን የት አደረስከው? የጨዋታው መንፈስስ ምን ይመስል ነበር?
ቃሲም ታጁ (ከሻውል ደማ)
ዘላለም፡- በመጀመሪያ ሰለሞን ጋብዞኝ ወደፕሮግራሙ ገባሁ፡፡ የዕድሌን ቁጥር 11ን አነሳሁ፡፡ ይህን ቁጥር ያነሳሁበት ምክንያት ለቤተሰቤ 11ኛ ልጅ በመሆኔ ነው፡፡ ከዚያ ዘና ብዬ ስጫወት ሠባት ሺህ አምስት መቶ ብር አገኘሁ፡፡ ሰለሞንን አሁን በፖሊስ እያፈላለግኩት ነው፡፡ ምክያቱም ጉድ ሠርቶኛል፡፡ በይፋ 7,500 ብር ወስጄ 14,500 ብር እንዳወጣ አድርጎኛልና፡፡ በየገባሁበት ምግብ ቤትና ካፌ “ድርሻችንን” እያሉ እኮ ነው የተቀበሉኝ፡፡ ብዙ ሰዎች ደውለው ተቀባብለውኛል፡፡ ስለዚህ ከተቀበልኩት ያወጣሁት ስለበዛ በዕንቁ መጽሔት በኩል ለሰለሞን መልዕክቱ ይድረስልኝ፡፡ ፕሮግራሙ ቆንጆ ነው፡፡ ሰለሞን በጥረት እየሠራው ስለሆነ ወደፊትም ከፍተኛ መሻሻል እንደሚያደርግ አምናለሁ፡፡
ዕንቁ፡- አንተስ በኢቲቪ አዲስ ፕሮግራም የመጀመር ሃሳብ የለህም?
ዘላለም፡- አለኝ እንጂ፤ አንድ ዓመት ከሠራሁ በኋላ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራሜን ለሌላ ሰው የማያጫርትብኝ ከሆነ አዲስ የቲቪ ፕሮግራም የመሥራት ሃሳብ አለኝ፡፡ (የሞቀ… ሳቅ)
የብዙ ሰዎችን ድምፅ አስመስለህ በማቅረብህ የተነሳ የደረሰብህ መጥፎ አጋጣሚ የተፈጠረበት ጊዜ ነበር?
የሺዋስ ዓለማየሁ (ከፈረንሳይ ለጋሲዮን)
ዘላለም፡- መቼም ስም ለመጥቀስ አልገደድም፡፡ አንድ የገረመኝ ነገር ግን አለ፡፡ ብዙ ሰዎች ድምፃቸውን በሌላ ሰው አንደበት ሲሰሙ እንደሚደነግጡ ያስረዱኝ ሰዎች አሉ፡፡ ነፍሱን ይማረውና የጋዜጠኛ ደምሰው መርዕድን ድምፅ አስመስዬ በቲቪ ሳቀርብ ደምሰውም ደስ ብሎት አቅፎ አደነቀኝ፡፡ በጣም ከባዱ ድምፅ የእርሱን ማስመሰል ነበር፡፡ ከደምሰው ጋር ተዋውቀን ጥቂት እንደቆየን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ደምሰውን ለመቅበር እየሄድን ሳለ ከለቀስተኞቹ መሀል አንዷ ሴትዮ ጮክ ብለው “ደስ ይበልህ! ደፋኸው አይደል?” አሉኝ፡፡ ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ ደግሞ ሌላ ድምፁን የማስመስለው የሬዲዮ ፋና ጋዜጠኛ መታፈሪያ አበበ እሱም በሞት ተለየ፡፡ ከዚያ ካስመሰልኳቸው ውስጥ ግዛው ዳኜ ሞተ፡፡ አንድ ቀን ሽመልስ በቀለና ሠራዊት ፍቅሬ ቁጭ ብለው “…ይሄ ልጅ የሚያስመስላቸው ሰዎች እየሞቱ ነው፤ የእኛን አይችለውም አይደል?… ኧረ የእኛን ባልቻለው” ሲባባሉ ሰማኋቸው፡፡
አንዳንዱ ሰው ደግሞ የእርሱን ኮት ልታስወልቀው… በእርሱ ድምፅ ልትነግድ የመጣህ አድርጎ ስለሚያስበው ያስፈራራሃል፤ የሚደብረው ሰውም አለ፡፡ እኔ ደግሞ የሚደብራቸውን ሰዎች ድምፅ አልልላቸውም፡፡
ዕንቁ፡- አንድ ሰሞን የኃይሌ ገ/ሥላሴንና የደራርቱ ቱሉን ድምፅ ታስመስል ነበር፤ አትሌቶቹስ በዚህ ረገድ አቋማቸው እንዴት ነው?
ዘላለም፡- የእውነት ለመናገር ኃይሌንም ደራርቱንም አደንቃቸዋለሁ፡፡ ለኃይሌ ገ/ሥላሴ የሀዋሳ ሪዞርት ሆቴሉን ዶክመንተሪ ፊልም ሠርቼለታለሁ፡፡ እነርሱ ነፃ ናቸው፡፡ ድምፅ ማስመሰል የተለመደበት ማኅበረሰብ ጋር በቀላሉ የመግባትና የመውጣት ልምድ ስላላቸው የሚረዱት ይመስለኛል፡፡ አንዴ ግን ደራርቱ ሬዲዮ ፋና ላይ ቀርባ ሙዚቃ ስትመርጥ “ዘፈኑን በድምፅሽ ሞክሪው እስቲ” ይሏታል፡፡ እሷም “በኋላ የዘላለም መቀለጃ ልታደርጉኝ ነው” ብላ አለፈቻቸው፡፡
ዕንቁ፡- ለዛሬው ሥራህ መታወቂያ የሆነህ የታዋቂ ሰዎችን ድምፅ ማስመሰል መሆኑን ታምንበታለህ?
ዘላለም፡- አዎ! በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሰው ምንም ለመሆን የመጀመሪያ እርምጃው መታወቂያው ነው፡፡ አንድን ቁጥር ሳትጠራ 100 ላይ አትደርስም፡፡ ወደማስታወቂያ ሥራ ከመሻገሬ በፊት የድምፅ ማስመሰል ተሰጥኦዬ ታዋቂ አደረገኝ ማለት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች “ዘላለም ኩራባቸው” ስትላቸው “ይሄ ድምፅ የሚያስመስለው” የሚሉት ታዋቂነቴ በምን እንደመጣ ጠቋሚ ነው፡፡
በሀዋሳ ተወልደህ እንደማደግህ መጠን የከተማዋ 50ኛ ዓመት በዓል ሲከበር ምን አስተዋፅኦ አበርክተሃል?
ማቴዎስ ወ. (ከሆሳዕና)
ዘላለም፡- በዓሉ በደመቀ ሁኔታ ነው የተካሄደው፡፡ የሀዋሳ ከተማን ዶክመንተሪ ፊልም የሠራሁት እኔ ነኝ፡፡ የማስታወቂያ ሥራውንም ሠርቻለሁ፡፡ በከተማይቱ ታሪክ የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል መድረክ በማሠራት ኮንሰርት ያዘጋጀሁትም እኔ ነኝ፡፡ በዝግጅቱም በርካታ ታዋቂ የሃገራችን ሙዚቀኞችና ድምፃውያን ተሳትፈዋል፡፡
ዕንቁ፡- የመድረክ ፕሮግራሞችን ከመምራት የጠፋኸውስ ለምንድነው?
ዘላለም፡- የመድረክ ፕሮግራሞችን የመምራት ሥራ ላይ ብዙ ቆይቻለሁ፡፡ ቀስ በቀስ ግን ብዙ ሥራዎች ላይ ከመሳተፍ በአንዱ ላይ ወደመጠመድ ገባሁ፡፡ መድረክ የመምራት አጋጣሚው ሲገኝ የሚሠራ ነው፡፡ የምሠራቸው አንዳንድ መድረኮችም በቲቪ የማይቀርቡ ይሆኑና ሳይታዩ ይቀራሉ እንጂ ሙሉ በሙሉ ከመድረክ መምራት ጠፍቼ አይደለም፡፡ በተለያዩ የቴሌቶንና ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይም ሠርቻለሁ፡፡
የማስታወቂያ ሥራዎችህ እርካታ የሚያጎናፅፉህ ምን ውጤት ስታገኝባቸው ነው?
ኃይሉ ወ.አምላክ
ዘላለም፡- የሠራሁት ማስታወቂያ ሕዝቡ ጋር ደርሶ ጥሩ ግብረ መልስ /Feedback/ ሲገኝበት በጣም እርካታ ይሰጠኛል፡፡ ምሳሌ ልጥቀስ፤ አንድ ወዳጄ ባትሪ ድንጋይ ያስመጣል፡፡ ባትሪው ስላልተዋወቀ ተፅዕኖ ነበረበት፡፡ ወሰድኩ፣ ሠራሁት፣ ተዋወቀ፣ ወዲያውኑ አለቀ፤ በገበያው ተፈላጊነቱ ጨመረ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ መሥራት ነው እርካታን የሚያጎናፅፈኝ፡፡
ዕንቁ፡- የኩባንያዎችን ማስታወቂያ የምትሠራው በራስህ ነው ወይስ በአሠሪዎቹ ፍላጎት?
ዘላላም፡- በመጀመሪያ ደረጃ ኩባንያው የሚፈልገው ነጥብ አለ፤ “ዘላለም ይሄንን ነጥብ አጉላልኝ” ይላል፡፡ ከዚያ በኋላ ባለቤቱ እኔ ነኝ፡፡ መነሻ ያስፈልገኛል፡፡ ለምሳሌ ድርጅቱ ምርት መሸጥ ነው የሚፈልገው? ወይስ አዲስ ምርት እያመጣ መሆኑን ቀድሞ ማስታወቅ ነው የፈለገው?… የሚለው መነሻዬ ይሆነኝና ቀጣይ የማስታወቂያ ሥራው የእኔ ይሆናል፡፡
ዕንቁ፡- አንተ ማስታወቂያ ስትጀምር የነበረው እና የአሁኑ የማስታወቂያ አሠራር ለውጡ ምንድነው?
ዘላለም፡- ዕድገት አሳይቷል፤ ዕድገቱም የማስታወቂያ አስነጋሪዎችን ቁጥር ጨምሮታል፡፡ ምርታቸውንና ድርጅታቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አምነው የመጡ ደንበኞችን ቁጥር አበራክቷል፡፡ በማስታወቂያው ሂደት ግን ገና ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ብዙ ነገር ይቀረዋል፡፡
ዕንቁ፡- አሁን በሀገራችን የሚታዩ ማስታወቂያዎች ሊተዋወቅ የሚፈለገውን ምርት ከማስተዋወቅ ይልቅ አስተዋዋቂውን ሰውዬ ማጉላትና ድራማዊ ሂደቱ ላይ ያተኩራሉ የሚለውን አስተያየት እንዴት ትመለከተዋለህ?
ዘላለም፡- አንዴንዴ ማስታወቂያ ተናጋሪው ጎልቶ የሚታይበት ማስታወቂያ ይቀርባል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በሂደት የሚወገዱ ናቸው፡፡ አንድ ማስታወቂያ ዒላማው ምንድነው? መልዕክቱ ምንድነው? እንዴትና ለማን ይቀርባል? የሚለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምንጊዜም ማስታወቂያው እንደታየ ምርቱ ሊታወስ መቻል አለበት፡፡ አንዳንድ ማስታወቂያዎች ላይ የሰዎቹን ንግግር ታስታውስና ያስተዋወቁት ምርት ምን እንደሆነ ላይታወስ ይችላል፡፡ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮችን ማሻሻል ይገባናል፡፡
የማስታወቂያ ሥራ ባለሙያዎች ትግባባላችሁ? ማኅበር አላችሁ? በዋጋ የተነሳ እርስ በእርሳችሁ ችግር ትፈጥራላችሁ?
ስዩም ወልዴ (ኢ-ሜይል)
ዘላለም፡- ብዙ ባይሆኑም ዋጋ በጣም አውርደው ለመሥራት ማስታወቂያ አስነጋሪዎችን የሚጨቀጭቁ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ገበያውን መርተህ መዝለቅ የሚቻለው ዋጋ በማሳነስ ሳይሆን ጥሩ ይዘት ያለው ፕሮጀክት በመሥራት ብቻ ነው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በድምፅ ያስመሰልከው ማንን እንደነበር ታስታውሳለህ?
ራዊና ኃይሌ (ከአዲግራት – በስልክ)
ዘላለም፡- ብዙም የሚታወቅ ሰው አይደለም፤ የሀዋሳ ሰው ነው፤ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራሁት የሻምበል ግዛው ዳኜን ድምፅ ነበር፡፡ በጣም የማደንቀው ጋዜጠኛ ነበር፡፡
ዘላለም የዕረፍት ጊዜህን እንዴትና ምን በማድረግ ታሳልፋለህ?
ኬብሮን ተስፋ (ከኮልፌ)
ዘላለም፡- የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን በፍቅር እከታተላለሁ፤ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ፡፡… አንዳንዴ ለራሴ በክራር እዘፍናለሁ፡፡ ፕሮፌሽናል ባልሆንም በመጠኑ ክራር እመታለሁ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር እጫወታለሁ፡፡ ሙዚቃ አደምጣለሁ፡፡ እንደ ኡሙ ሳንጋሪ የመሳሰሉ የምዕራብ አፍሪካ ድምፃውያንን የሚያቀነቅኗቸውን ዜማዎች እከታተላለሁ፡፡
ዕንቁ፡- ከሀገራችን ድምፃውያንስ የማን አድናቂ ነህ?
ዘላለም፡- ብዙዎቹ ዘፋኞች ጓደኞቼ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ንጉሡን የሚነካብኝ የለም፡፡ ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠን የሚነካ ማንም አይኖርም፡፡ ከዚያ እያለ… እያለ… እያለ ይቀጥላል፡፡
ብዙዎቹ የውጪ ሰዎች ባሕር አቋርጠው በመምጣት የሀገራችንን የተለያዩ ቅርሶችና የቱሪስት መዳረሻዎች ይጎበኛሉ፤ የብዙዎቹ የእኛ አርቲስቶች ሕልም ግን አሜሪካና አውሮፓን ማየት ነው፡፡ አንተ ከሀገራችን የቱሪስት መስህቦች የትኞቹን ተመልክተሃል?
አስር አለቃ ስምኦን ወልዱ (ከምስራቅ ዕዝ)
ዘላለም፡- ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝቻለሁ፡፡ ጎንደር የሚገኘውን የንጉሥ ፋሲልና የበርካታ ነገሥታትን ቤተመንግሥትም ተመልክቻለሁ፡፡ በደቡብ ክልል የሚገኙ አብዛኞቹን የቱሪስት መስህቦች ተዟዙሬ አይቻለሁ፡፡ የአባይን ወንዝና የጢስ አባይ ፏፏቴን ተመልክቻለሁ፡፡ በዚህ በኩል እንኳ ሰነፍ አይደለሁም፡፡
እነዚህን ቦታዎች ስመለከት የተለያዩ ስሜቶች ነው ያደረብኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጢስ አባይን ስመለከት በጣም አፈርኩ፡፡ እስከዛሬ የት ነበርኩ አልኩ፡፡ ላሊበላ ገብቼ ግን ዝም ነው ያልኩት፡፡ ዝም… ዝም… ዝም፡፡ በኋላ ኢትዮጵያዊነቴ እየተሞላ መጣ መሰለኝ፡፡
ዕንቁ፡- አንተ ያደረብህ ስሜት ወጣቱ እንዲጋባበት ምን ምክር ትለግሳለህ?
ዘላለም፡- ወጣት የነብር ጣት ብዬ ነው የምጀምረው፡፡ አስተዋይ፣ ብልህ፣ የተማረና አንባቢ መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሀገርንና ወገንን በመልካምነት መጠበቅ፣ መተሳሰብ፣ መቻቻል፣ መደማመጥ ተገቢ ነው፡፡ የዛሬው ወጣት ሆይ ነገ የትም መድረስ ይቻላል፡፡
ዕንቁ፡- ዶክመንተሪ (ዘጋቢ) ፊልሞችህ ምን ላይ ያጠነጥናሉ?
ዘላለም፡- ብዙዎቹ ዘጋቢ ፊልሞቻችን ካምፓኒ ፕሮፋይሎች ናቸው፡፡ አንድ ኩባንያ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ፣ ወደፊት ምን ራዕይ አለው የሚለው ይዳሰስበታል፡፡ ታሪካዊ ጉዳዮችን ስንሠራ ለምሳሌ አንድ ከተማ መቼ ተቆረቆረች፣ የነበራት አደረጃጀት ምን ይመስላል፣ አሁን ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች፣ ወደፊት የት ትደርሳለች የሚለው ይቃኝበታል፡፡
በሕይወትህ በጣም ተከፋሁበት፣ በጣም ተደሰትኩበት የምትውን ቀን ልትነግረን ትችላለህ?
ታዬ ይድነቃቸው (ከባህር ዳር)
ዘላለም፡- አለ! ብዙ የሐዘን ጊዜያት አልፈዋል፡፡ እንዳልናገረው ይበጠብጠኛል፡፡ ሐዘንና ደስታ በማንም ሰው ሕይወት ተፈራራቂ ናቸው፡፡ ሰው ይደሰታል፤ ያዝናል፡፡ የሰው ልጅ ለማዘን ፈልጎ ባይሄድም መደሰትን ፈልጎ ግን ይደሰታል፡፡ እነዚህ የማይቀሩ ነገሮች ናቸው፡፡
መጽሐፍ ታነባለህ? ምን አይነት መጻሕፍትን ትመርጣለህ?
ዳዊት መልካሙ (ኢ.ሜይል)
ዘላለም፡- እኔ ባነበብኩት መጽሐፍ ላይ ያየሁትን ልሁን ባይ አይደለሁም፡፡ ከውስጡ የሚሆነኝን እቀበላለሁ፤ የሚያንፀኝን እወስዳለሁ፤ አይሆነኝም ያልኩትን ደግሞ እጥላለሁ፡፡ ከመደበኛነት ውጪ ያሉ ታሪኮችም ይመስጡኛል፡፡
ዕንቁ፡- ጥያቄዎቻቸውን ለላኩልህ፣ በአጠቃላይ ለአድናቂዎችህ የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖራል?
ዘላለም፡- አድናቂዎቼ አስባችሁ ጥያቄዎቻችሁን ስላቀረባችሁና ስለሰጣችሁኝ አስተያየት አመሰግናለሁ፤ እወዳችኋለሁ፤ አከብራችኋለሁ፡፡ ጥሩ ከማሰብ፣ ጥሩ ከመሆንና ጥሩ ከማድረግ በላይ ምንም የለም፡፡ ለወደፊቱም ጥሩ ነገር ይዤ ለመቅረብ እጥራለሁ፡፡ “ሁሉን ፈትኑ፤ መልካሙን ያዙ” ነውና፡፡ በአጠቃላይ አከብራችኋለሁ፡፡
