ከአማራ ክልል በአዲሱ የመሬት አዋጅ ላይ መግለጫ ተሰጠ

Date:


አዲሱን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ አስመልክቶ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የቢሮው ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ የመግለጫው አስፈላጊነት የገጠር መሬት ባለይዞታዎች አዋጁን አውቀው ተገቢውን ድጋፍ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ነው ብለዋል፡፡

‎የነበረውን አዋጅ ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ነባሩ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 252/2009 አሁን ካለው ነባራዊ ኹኔታ ጋር ያሉ ጉዳዮችን ባለመያዙ እና እንደ ሀገር የገጠር መሬት አጠቃቀምን ተመሳሳይ ለማድረግ በማስፈለጉ እንደኾነ ነው የገለጹት።

ለአዋጁ መሻሻል ከምክንያቶች መካከልም:-

‎👉 የአርሶ አደሮችን እና የከፊል አርብቶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት ጋር ማራመድ እንዲቻል እና በመሬት ይዞታው ላይ ያለውን የንብረት መብት ይበልጥ ለማጠናከር፣

‎👉 የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃን ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ለማደራጀት፣

‎👉 በመሬት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን ለመቀነስ፣

‎👉 የሴቶች፣ ሕጸናት እና ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ፣

‎👉 በተበታተነ መንገድ ያሉ አርሶ አደሮችን በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ ወደ አንድ ማዕከል ለማምጣት እና በገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሮችን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማድረግ እና

‎👉 የክልሉን መሬት በአግባቡ ማሥተዳደር የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል ኀላፊው።

“‎አዲሱ የመሬት አዋጅ ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የመለሰ ነው” ብለዋል፡፡

አዋጁ ይዟቸው ከመጡ መልካም ነገሮች መካከልም፦

‎መሬትን በባለቤትነት የመጠቀም መብት እና የሕግ ዋስትና ሽፋን ለአርሶ አደሮች ተሰጥቷል፡፡ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለልጆቻቸው እና ላመኑበት ለማንኛውም ሰው በስጦታ እንዲሰጡ ዕድል የሰጠ ነው ብለዋል።

‎ባለይዞታው በመሬቱ መጠቀም፣ ማከራየት፣ ለጋራ አራሽ መስጠት፣ ቋሚ ንብረትን በሽያጭ የማስተላለፍ፣ እና አሥተዳደራዊ ወሰን የማይገድበው የመለዋወጥ መብትን ሰጥቷል ነው ያሉት፡፡

‎አዋጁ የሴቶች፣ ሕጻናት እና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የጠቃሚነት መብት ከለላ የሰጠ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

‎አዋጁ የወጣቶችን እና አዲስ መሬት ጠያቂዎችን ጥያቄ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ከሦስተኛ ወገን ነጻ የኾነ መሬት አሥተዳደርን በማስፈን በፍትሐዊነት የሚያስተናግድ ነው ብለዋል፡፡

‎ዘላቂ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀምን በማስፈን መሬት መጠቀም የሚቻለው በአጠቃቀም ዕቅዱ መሠረት መኾኑን አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል ነው ያሉት፡፡

‎የመሬት አሥተዳደር ተቋማትን የሥራ ድርሻ ከላይ እስከ ታች ተጠያቂነትን ጭምር በግልጽ አስቀምጧል ብለዋል፡፡

‎የአሥተዳደር ሥርዓቱ ከማኅበረሰቡ ዕሴቶች ጋር እንዲስማማ ማድረግ በትልቁ ዕውቅና የሰጠ ነው፡፡ የአርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ለግብርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዋስትና እንዲኾን ያገዘ ነው ብለዋል፡፡

‎ለገጠር ኮሪደር ልማት እና የገጠር ሽግግር በ25 ዓመቱ ለታቀደው ዕቅድ መሳካት አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡

የገጠር መሬት የሚጠቀሙ ባለሀብቶች በረጅም ጊዜ ብድር እንዲያገኙ ዕድል ይዞ የመጣ መኾኑን ተናግረዋል። በክልሉ የብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ አሥተዳደር ለመገንባት አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

‎ከዚህ በፊት አርሶ አደሮች በማሳቸው ላይ ያለሙትን ቋሚ ንብረት የመሸጥ መብት አልነበረም። አሁን ግን ቤትን ጨምሮ ሌሎች ቋሚ ተክሎችን እንዲሸጡ የፈቀደ ነው ብለዋል፡፡ ለመንግሥት ሠራተኞች በውርስ እና በሥጦታ መሬት ማግኘት የሚችሉበትን መብት ያጎናጸፈ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡

‎የገጠር መሬት ባለይዞታው መሬቱን በአጠቃቀሙ መሠረት ካልተጠቀመ የሚወሰዱ እርምጃዎችንም  ያካተተ ነው፡፡ በአጠቃቀሙ መሠረት ካለሠራ ከምክር ጀምሮ መሬቱን እስከመጨረሻው ሊነጠቅ እንደሚችል ተቀምጧል ያሉት፡፡

‎ማንኛውም ሰው የግል፣ የወል ወይም የመንግሥት ይዞታን በሕገ ወጥ መንገድ የወረረ፣ ጉዳት ያደረሰ፣ ሕገ ወጥ ግንባታ የሠራ እና እንዲሠራ የፈቀደ እንዲሁም ሀሰተኛ የመሬት ማስረጃ ያቀረበ ከአንድ ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ25 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት በየደረጃው ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡

‎በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ዝቅተኛው የአርሶ አደሮች መሬት መጠን 0.25 ሄክታር ነው፡፡ ከዚህ መጠን በታች ከኾነ ለአንድ ሰው ብቻ በሥጦታ ወይም በውርስ ማስተላለፍ ይቻላል ነው ያሉት።

‎የአዋጁን ማስፈጸሚያ ደንብ የማዘጋጀት ሥራ መጀመሩን እና በቀጣይ መመሪያዎች እንደሚዘጋጁም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

አሚኮ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ...

የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የ5 በመቶ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና...

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ለኢራን ህዝብ – “እኛ ከእናንተ ጋር ነን”

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ፥ የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ...

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና...