‹‹ፊደሎቻችንን ወረቀት ላይ ነድፌ ነው ኮምፒውተር ላይ ያስገባሁት››
‹‹እኔ እግዚአብሔርን በሃይማኖት ብቻ አልወስነውም››
‹‹የማንበቢያው መንገድ ተለያየ እንጂ የንባብ ባሕሉ አሁንም አለ››
ውድ አንባቢያን በቁጥር 199 ዕትማችን ከሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ባለሙያው ኢንጂነር ፍሥሐ አጥላው ጋር ስለትውልድ እና ዕድገታቸው፣ ከሀገር ስለወጡበት ሁኔታ፣ አሜሪካን ሀገር ከሔዱ በኋላ ስለገጠማቸው ሕይወት እና ስለትምህርታቸው መጠነኛ ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው የኹለተኛ ክፍል ቆይታችን ደግሞ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሶፍትዌር ዕድገት ስለነበራቸው ጥልቅ ሙያዊ አበርክቶ እና የኢትዮጵያ ፊደልን ወደ ኮምፒውተር ፕሮግራም ለማካተት በግላቸው የደከሙበትን ርቀት፣ ይኽንን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ቤት መጥተው ለመንግሥትና ለተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ሲያስተዋውቁ ስለነበረው ምላሽ፣ ስለመንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ ስለግብረ ሰናይ አገልግሎታቸውና ስለሌሎችም ጉዳዮች የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- የኢትዮጵያ ፊደል በሶፍትዌር እንዲኖር ለማድረግ ያነሳሳዎት ምን ይሆን? የኑሜሪካል ኮንትሮል ፕሮግራመር ሆነው አሜሪካን አገር መስራትዎ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት ነበረ? አሜሪካን አገር የሰሩባቸው ተቋሞችና እርስዎስ ምን ምን ይሰሩ እንደነበር ባጭሩ ቢገልፁልን?
ኢ/ር ፍሥሓ፡- ለመረጥኳቸው የትምህርት ዓይነቶችና በትርፍ ጊዜዬም ለምሰራቸው ከአካዳሚ ውጭ ለሆኑ ድርጊቶች ተፅእኖ ያሳደሩብኝ ብዙ ነገሮች ነበሩ። ይህም በልጅነቴ ብዙ የአማርኛም የእንግሊዝኛም መጻሕፍትንና ጋዜጦችን የማንበብ ልዩ ፍቅር ነበረኝ፤ ገና ዘጠነኛ ክፍል ሆኜ ከክፍል ባልደረቦቼ ጋር ተመርጠን ከእንግሊዝኛ አስተማሪያችን ከወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው ጋር አዲስ አበባ ተደርጎ የነበረውን የኣሜሪካን ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን መጎብኘቴ (በዛን ጊዜ የተነሳው ቪድዮ እስከ አሁን YOUTUBE ላይ “Fesseha Atlaw, USA” በሚል ርዕስ ይገኛል) ይህን የመሳሰሉ ብዙ አጋጣሚዎች ላይ ስለቴክኖሎጂ የነበረኝ ዝንባሌና ምኞት በተቻልኝ ሁሉ ለመሳተፍ ጉጉት ስለነበረኝ እግዚአብሔርም ይህን አሳክቶልኝ እድለኛ መሆኔ ነበር።
የመጀመሪያውን የአማርኛ ሶፍትዌር መሥራቴ ከሮቦት ፕሮግራመርነቴ ጋር አይገናኝም፡፡ ምክንያቱም እኔ ስሠራበት የነበረው ካምፓኒ በትልልቅ መሣሪያዎች የብረት አንዳንዴም የፕላስቲክ የአውሮፕላን መለዋወጫ እቃዎችን በብዛት ለመፈብረክ የሚያስችል ፕሮግራም ነበር የምፅፈው፡፡ ይህም ከአማርኛ ሶፍትዌር መሥራቴ ከዚህ ጋር አይገናኝም፡፡
ከዚህ ቀጥሎም አታሪ (ATARI) የተባለው የመጀመሪያዎቹን የኮምፒውተር ጌም ከሰራው ኩባንያ ለ3 ዓመት ከሰራሁ በኋላ ወደ ሂውሊት ፓካርድ (Hewlett Packard-HP) ኩባንያ ገብቼ ከጁንየር ዴቬሎፕሜንት ኢንጂኔር እስከ ኢንጂኔርንግ ሳይንቲስትና ኢንጂኔሪንግ ማናጀር ከ20 ዓመታት በላይ ስሰራ ቆይቻለሁ።
ሂውሊት ፓካርድ (HP) ዋናው መስሪያ ቤት (Head Quarters) በነበርኩበት ጊዜ በመጀመሪያ የፓወር ሲስቴም ኮምፖኔንት፤ የPower Systems Components ኢንጂኔር ነበርኩ፡፡ ከተለያዩ አሜሪካ ስቴትስና ልዩ ልዩ አገራት (ሜክሲኮ፣ ጀርመኒ፣ ጃፓን፣ ጣልያን፣ እንግሊዝ፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖር፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ ኮርያና ሌሎችም) በየዓመቱ የሚዘጋጅ “Power Systems Engineering Design Symposium” አዘጋጅና ሊቀ መንበር ሆኜ ለ7 ዓመት አግልግያለሁ። ይህም በHP የምናደርገው ፈር ቀዳጅ የሆነው ዓለም አቀፍ ስብሰባ፤ ለሌሎች ኩባንያዎች ተምሳሌት ነበር፡፡ ስለዚህም በዓለም የታወቁ የኢንጂኔሪንግ ጋዜጦች (ለምሳሌ “Electronic Engineering Times; Novermber 23, 1992 Anatomy of a USER –HP” በሚል ርእስ) እኔን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ዘግቦታል። በ1994 ዓለም አቀፍ የሆነ በብዙ ሺህ ኢንጂኔሮችና ሳይንቲስቶች የተካፈሉበት ትልቅ ሰብሰባ ላይ በተባባሪ ሊቀ መንብርነት (CO Chairman) ለመሆን ተጠይቄ አገልግያለሁ። ይህም ዓለም አቀፍ የሆነው “PCIM (Power Control Intelligent Motion (PCIM)” የተባለው መፅሔት “Power System Compatibility for Digital Designers” በሚል ርዕስ ማርች 1994 እትሙ ላይ በሰፊው ዘግቦታል።
በቅርብ ጊዜ ደግሞ “Medtronic” በሚባል ኩባንኛ በ“Bio Medical Engineering” ለሰው አካል መለዋወጫ በሚሰራ ኩባንያ ውስጥ ነው የሰራሁት። በዚህም ኩባንያ ካስገኘናቸው መለዋወጫ ምርቶች፣ የልብ ባንቧ ቫልብ (Heart Valve)፣ ሰው ወራሽ ኩላሊት (Artificial 3D printed kidneys)፣ ልዩ ልዩ የውጭ አካላት (አፍንጫ፣ ጆሮ፣ ጣት፣… የመሳሰሉት ናቸው) ምንም እንኳ እኔ የምሰራው ትንሽ ሥራ ከሁሉም ተደምሮ ቢሆንም በመንገድ ላይ ወይም ባንዳንድ ቦታ “MEDTRONIC” የሚል ሸሚዝ ወይንም ኮፍያ አድርጌ ሲያዩኝ ሁሉም የኔ ሥራ ብቻ እንደሆነ ተንደርድረው የሚያቅፉኝና የሚያመሰግኑኝ በርካታ አሜሪካውያን አጋጥመውኛል፡፡ እንደውም አንድ ሴት “ልቤ ውስጥ ገብተኻል” ብላ መጥታ እንባ እየተናነቃት ብዙ ሰው በተሰበሰብብት እንዳመሰገነችኝ አልረሳውም። ይህች ሴት የልብ ዋና ባንቧ ስለጠበበ ወደሞት እየተጓዘች እኛ የምንሰራው ከ Nitnol ከተባለ ብረት stent ተገጥሞላት ሕይወቷ ስለተረፈ ነው።
ግዮን፡- በጣም የሚገርምና የሚያኮራ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ሴሚናሮች ሌሎች የአፍሪካና ኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎች ወይንም አቅራቢዎች በብዛት ምን ያህል ነበሩ?
ኢ/ር ፍሥሓ፡- አሁን ባለንበት ጊዜ በተለያዩ የአሜሪካን ስቴቶችና ልዩ ልዩ አገራት ብዙ የሚያመረቃ የቴክኒካል ሥራዎችን የሚሰሩ፣ የሚያኮሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን አውቃለሁ። ሆኖም በዚያን ጊዜ እኔ በነበርኩብት አካባቢና ስብሰባዎች የነበሩ ኢትዮጵያውያን አልነበሩም፡፡ እንደውም የጥቁር መልክ ያለው አፍሪካዊ ወይም ጥቁር አሜሪካዊ ተሰብሳቢ የማየው ከመቶ አንድ እንኳን አይሞላም ነበር።
በአሁኑ ጊዜ ግን በየስብሰባውና በየሴሚናሮች ቁጥራቸው ከፍ ያለ ጥቁሮችና አፍሪካውያን በቴክኖሎጅው መስክ እየተሰማሩ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ወጣቶችን በዓለም ዙሪያ በጣም በተራቀቁና በጠለቁ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ላይ በሚያስደንቅ ሁኔታ እየተሳተፉ ሳይ እጅግ ደስ ይለኛል። በተለይም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በአማርኛም ሆነ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚሰሩ ወጣት ኢንጂነሮችን ማየቴ ያን ጊዜ ከ40 ዓመታት በፊት በዳዴ ያስጀመርነው አሁን ከየትኛውም የዓለም ቋንቋ በማይተናነስ ክንፍ አውጥቶ ሲበር እያየን ነው። እኔም እንዳቅሜ በተቻለኝ ሁሉ “በርቱ” እያልኩ ነው።
ይህንን ለመደገፍ በእኔና በቤተስቤ ስም ያቋቋምኩት የበጎ አድራጎት ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከምንረዳችው እንቅስቃሴዎች አንዱ በፊደላችን የሚሰሩ መተግብሪያዎችና ሶፍቴዌሮች የሚሰሩ ወጣቶችን በየዓመቱ በማወዳደር መጠነኛ የገንዘብና የቁሳቁስ ሽልማት እንሰጣለን።
ግዮን፡- ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እንደምንሰማው (ከዛሬ 35 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ በቮይስ ኦፍ አሜሪካ እና የመሳሰሉት ጭምር) የአማርኛ ፊደላትን ከኮምፒውተር ለማዛመድ እርስዎ የመጀመርያው ሰው እንደሆኑ ተዘግቧል፡፡ አሁን እንደሚነግሩን ግን ዋነኛ ሥራዎ ከቋንቋ ሶፍትዌር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ነበር፡፡ ታዲያ ለምንና እንዴት ይህን ያማርኛ ሶፍትዌር ሊሰሩ በቁ?
ኢ/ር ፍሥሓ፡- ትክክል ነው ብዙዎቹ አሜሪካን ውስጥ ተቀጥሬ የስራሁባችው ተቋማት ከቋንቋ ሶፍትዌር ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራችውም፡፡ የኤሌክትሮኒክ ኮምፖነንትስ እና ሲስተምስ ላይ ነበር የምሰራው፡፡ ሆኖም ከልጅነቴ ጀምሮ ገና 10 ዓመት ሳይሞላኝ የአማርኛ ግጥምና ድርሰቶችን እወድ ነበር፡፡ የተቻለኝም ያህል ለመፃፍ እሞክር ነበር። በ12 ዓመቴ ላይ የፃፍኩት የልብወለድ ታሪክና ግጥሞችም ታትመው እንደወጡ በዚያን ጊዜ በጳውሎስ ኞኞ አዘጋጅነት የሚታተመው ተወዳጁ የመንግሥት ዕለታዊ “የኢትዮጵያ ድምፅ” የሚሰኘው ጋዜጣ ዘግቦታል። ይኸውም 7ኛ ክፍል እያለሁ የደረስኩትና ፕሮዲውስ ያደረግሁት ቴያትር አገር ፍቅር ቴያትር ለመታየት በመብቃቱ “የ15 ዓመት ሕፃን ቲያትር ደራሲ” በሚል ርዕስ ነበር።
አሜሪካን አገር 3ኛ ዲግሪየን ካገኘሁ በኋላ በተማርኩበት ትምህርት ልምምድ ለማድረግ የሥራ ፈቃድ ተሰጥቶኝ ሥራ ጀመርኩ፡፡ የ18 ወራት የልልምድ ጊዜዬ ሲያልቅ የምሰራበት መሥሪያ ቤት የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሰጠኝ ለአሜሪካ መንግሥት አመልክተውልኝ የአሜሪካን የመኖሪያ ፈቃድ ተሰጥቶኝ ሥራዬን ቀጠልኩ። በዚህን ጊዜ ነው የአማርኛ ጽሑፎችን እንደገና መጫጫር የጀመርኩት። ሆኖም በእንግሊዝኛ ለሥራም ሆነ በግሌ የምጠቀምበት የግል ኮምፒውተር ቢሮዬ ነበረኝ። አማርኛ ግን ለመጻፍ የማይታሰብ ነበር፡፡ አማርኛ ቀርቶ ጃፓንኛና ቻይንኛ ወይም ዐረብኛ (Non-Latin) የመሳሰሉትን ማስተናገድ የሚችል አልነበረም። ጽሑፎቼን በእጄ መፃፍ ሲሰለቸኝ ቤተሰቦቼን የአማርኛ ጽሑፍ መሣሪያ (ታይፕ ራይተር) ከኢትዮጵያ ላኩልኝ ብዬ ጠይቅሁ፡፡ እነሱንም ሽሮ፣ በርበሬ፣ ጋዜጣና የአማርኛ መጻሕፍት እንልክልሃልን፡፡ የአማርኛ ታይፕ ራተር ግን ከኢትዮጵያ ማውጣት ትልቅ ወንጀል ነው ተብሎ ስለተደነገገ አንልክልህም አሉኝ። በወቅቱ በኢትዮጵያ ማንኛውም የአማርኛ ጽሑፍ ሥራ ይከናወን የነበረው በዚህ መሣሪያ ነበር፡፡ እነ ኢሕአፓ፤ ሻዕቢያ፤ ህወሓትን የመሳሰሉት ፓርቲዎችም የተለያዩ በራሪ ወረቀቶችንና ጽሑፎችን ያዘጋጁ የነበረው በዚህ የጽሑፍ መሣሪያ ነበርና፡፡ የደርግ መንግሥት የጦር መሣሪያን ያህል ይፈራውና ይቆጣጠረው ነበር። ስለዚህ በሕግ ደረጃም መሣሪያውን ከሀገር ይዞ የሚወጣ ግለሰብ ከተገኘ እስከሞት ድረስ ሊቀጣ ይችላል ይባል ነበር፡፡ እዚህ ላይ ፈረንጆች “ብዕር ከሰይፍ ይልቅ ይጠነክራል” (The PEN is mightier than the sword) የሚሉትን አባባል ያስታውሰኛል።
የአማርኛው ታይፕ ራይተር የምንለውን በመጀመሪያ የፈጠሩት ኢንጅነር አያና ብሩ የተባሉ ትውልድና እድገታቸው በወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ የሆኑ ምሁር ነበሩ። ኢንጅነር አያና ኦሊቬቲ (OLIVETI) ከተባለ የጣሊያን ካምፓኒ ጋር ለ40 ዓመታት ያህል ሰርተው ነው ይህንን የአማርኛ ታይፕራይተር ግኝትን እውን ማድረግ የቻሉት! የኢትዮጵያን ፊደለ ምስል (SCRIPT) ለትውልድ ያስተዋወቁ በመሆናቸው የዘመናዊ ታይፖግራፊ አባት (The Father of Modern Ethiopic Typography) ተብለው ይታወቃሉ።
እኔም ታይፕ ራይተሩ የሚፈበርከውን ጣሊያን ሀገር ላለው ኢሊቬቲ ለተባለው ኩባንያ ለመግዛት እንዴት እንደሚቻል እንዲነግሩኝ በመሥሪያ ቤቴ ስም ፃፍኩላቸው፡፡ ኩባንያውም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ልዩ ውል እንዳለውና ሊሸጥልኝ እንደማይችል ነገረኝ፡፡ ከዚያ በእንግሊዘኛ የምሠራበትን ኮምፒውተር መመርመር ጀመርኩ፡፡ ታይፕራይተር በማጣቴ የአማርኛ ሶፍትዌር ለመሥራት አነሳሳኝ፡፡ ይህ ወቅት በፈረንጆቹ 1982 አካባቢ ነበረ።
እኔ የምሰራበት “HP 150” የተባለ ኮምፒውተር ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህ ኮምፒውተር የሚጠቀመው የINTEL 8088 ማይክሮ ፕሮሴሰር ቢሆንም በሌሎች ከተሰሩ የዴስክ ኮምፒተሮች በሶፍት ዌርም በሃርድዌርም የሚያመሳስል ነገር አልነበረውም። ከHPም ወጥቶ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ጥቅም ላይ አልዋለም ነበር። ለነገሩ በዚያን ጊዜ ሁሉም ኮምፒውተር ፈብራኪዎች የየራሳቸው ዲዛይን ስለነበራቸው በሃርድዌርም በሶፍትዌር አይግባቡም ነበር። ወይንም ኮምፒውተሮቹ አንድ ወጥ የሆነ ሁሉን የሚያግባባ ስታንዳርድ አልነበራቸውም። ለምሳሌ “ማውስ” አሁን ሁሉም ኮምፒውተር ላይ የምንጠቀመው ጭራ ያለው አይጥ የሚመስል አዲስ የኮምፒውተር ክፍል አድርገን ነበር የምናየው። (“ማውስ” የሚለው ስሙም ከዛ እንደተወረሰ ብዙዎች አያውቁም) ዊንዶውስ የተባለውን የኮምፒውተር ተጠቃሚ መግባቢያ (Computer Ueer Interface) ማይክሮ ሶፍት ያስተዋወቀው በኋላ ነበር፡፡ ስለዚህ የምንጠቀመው ዶስ (DOS – Disk operating system) ፕሮግራሞችን መስመር በመስመር እየሰራን ነበር፡፡
አማርኛን ኮምፒውተር ውስጥ ለማስገባት ከወሰንኩ በኋላ የትኛውን ኮምፒውተር ልጠቀም የሚለው ትልቅ ጥያቄን ፈጥሮብኝ ነበር። ምክንያቱም ባንዱ ላይ የተሰራው ፕሮግራም ሌላው ላይ አይሰራምና። ያን ጊዜ የነበሩት ዋና ዋና የዴስክ ኮምፒውተሮች (IBM; Comaque; HP; Toshiba; Apple 2C; Atari; Commodore ይባሉ ነበር) የIBM standard ይሆናል ብዬ ስለገምትሁ አንድ የIBM ኮምፒውተር በወር $750 ከነማተሚያው ተከራይቼ ሥራዬን ጀመርኩ። የገመትኩትም ትክክል ሆኖ ከጥቂት ዓመታት በኋላ IBM ከከማይክሮሶፍት ጋር ተባብሮ የወደፊቱን ስታንዳርድ መሠረተ፡፡
ከዚያም በተከራየሁት በአዲሱ ኮምፒውተሬ ላይ ልዩ ልዩ ነገርን መሞከርና ኤክስፐርመንት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ የኢትዮጵያን ፊደላት በወረቀት ላይ ነድፌ አንድ ባንድ በኮምፒውተሩ ላይ ማስገባት ጀመርኩ (አንድ አንድ ፊደሎች በነበረው ውስን ሰንጠረዥ ውስጥ ለማስገባት አስቸጋሪዎች ነበር፡፡ ከእነዚህም “ጬ” አንዱ ነበር፡፡ ለነገሩ ሰባቱም የ”ጨ” ዘር ፊደላት በጣም አስቸጋሪዎች ነበሩ፡፡ “በ” ከሁሉም ብዙ ቦታ የሚወስድና 8 በ8 (8X8 Ascii) በነበረ ሰንጠረዥ ማካተት ከባድ ነበር) እያንዳንዱ ፊደል መቀረጽ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ፊደል ብቻ ሳይሆን የቻይና፣ የዐረብኛ፣ የጃፓንና የሌሎች ሀገሮች ቋንቋዎችም ቦታ አልነበራቸውም። የመጀመሪያዎቹ ኮምፒውተሮች በላቲን ፊደል (በእንግሊዝና በመሳሰሉት) ያለተፃፈን ጽሑፍ አይረዱትም ነበር፡፡ ስለዚህም ቴክኖሎጂው ጥሎን እንዳይሄድ አማርኛን በላቲን ቢፃፍ ይሻላል የሚሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በቴክኖሎጅው ምክንያት እንዳይደበዝዝና እንዳይጠፋ በማሰብ ነበር፤ አልፈርድባቸውም። እኔ ግን “አይቻልም” ወይም ከባድ ነው ሲሉኝ የባሰ የመጠንከርና እልኸኝነት ስላለብኝ መቻል አለበት ብዬ በትጋት በነበረኝ ትርፍ ጊዜ ሁሉ መሞከሬን ቀጠልኩ፡፡ በእግዚአብሔር እርዳታና በብዙዎች አበረታችነት ውጥኔ ተሳክቶክልኝ የኢትዮጵያን ፊደላት በኮምፒውጸር ማሳየትና በማተሚያም አትሜ ማሳየት ጀመርኩ። ምንም እንኳን ልፋቴ ለግል ጽሑፎቼ ቢሆንም ወሬው ወዲያው ተሰራጨና ብዙ ሰዎች እነርሱም መሥራት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡ አንዳንዶችም ያገኟቸው ውጤቶች እንደነበሩ ተረዳሁ፡፡ እኔ ግን በቶሎ መጠቀም ለሚፈልጉ ሁሉ የገንዘብ አቅም ላላቸው እያስከፈልሁ፣ ለሌላችው ደግም በአነስተኛ ዋጋ እንዲሁም በነፃ እየላክሁ በተጠቃሚ እጅ ገብቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለ “የአማርኛ የድርሰት ማቀነባበሪያ” የታሪክ መጀመሪያ ተባለ።
በዚያን ጊዜ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከብዙ አገራት በመቶ የሚቆጠሩ ደብዳቤዎች ይፃፉልኝ ጀመር። ብዙዎቹ ደብዳቤዎች እስካሁን ድረስ በእጄ ይገኛሉ። ደብዳቤውን የሚፅፉልኝ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ማኅበራዊ ድርጅቶች፤ የመንግሥት ተቋሞች፤ የግል ኩባንያዋችንም ጭምር ነበሩ፡፡ ከብዙ ጥቂቶችሁን ለመጥቀስ፦ ለምሳሌ የዋሽንግቶን፣ የቦስቶን፣ የዳላስ፣ የሎስ አንጀለስ ኢትዮጵያን ተራድዖ ድርጅቶች፤ ከመንግሥት መስሪያ ቤቶችም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ የጡረታ ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ ሕዝብ ደህንነት፣ የውጭ ድርጅቶች፣ ዩኒሴፍ፣ ወርልድ ፉድ ፕሮግራም፣ ዩኔስኮና የተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፤ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትና ወንጌላዊ ድርጅቶች፤ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችም ይገኙባቸዋል።
ግዮን፡- የዛሬ 30 ዓመት አካባቢ ሶፍትዌሩን ከጨረሱ በኋላ በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ተጋብዝው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር ሰምተናል፡፡ ከብዙ ዓመታት የአሜሪካን ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ያጋጠመዎት ነገር ምን ይመስል ነበር?
ኢ/ር ፍሥሓ፡- ሶፍትዌሩን መጀመርያ እንዳወጣሁት ትልቅ ዜናና መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ፊደላችንን በኮምፒውተር ስክሪን ላይ ማየት ብርቅዬ ነገር ነበር። እኔም ከሥራዬ ውጪ ባለው ጊዜዬ ሁሉ በተለያዩ ከተማዎች እየዞርኩ ኢትዮጵያውያን ሰብሰብ በሚሉባቸው ቦታዎች ማሳየትና ገለፃ ማደረግ እወድ ነበር። በኳስ ሜዳ ዓመታዊ ውድድሮች፣ በአብያተክርስቲያናት፣ በኮሚኒቲ ማዕከላት፣ በዩኒቨርስቲዎች፣ ወዘተ…።
አንድ ወቅት ካሊፎርንያ በሚገኘው ስታንፎርድ ዩንቨርሲቲ በአምባሳደር ካሣ ከበደ የሚመራ “ሕዝብ ለሕዝብ” የሚባል ቡድን ለኢትዮጵያውያን አሰባስቦ ለማነጋገር ከኢትዮጵያ መጥቶ ነበር፡፡ እኔም በስብሰባው መጨረሻ የሠራሁትን የአማርኛ ሶፍትዌር ኮምፒውተር ለእንግዶቹ እንዳሳይ ተጠይቄ ሳሳያቸው ምን ያህል እንደተደነቁና እንዳመሰገኑኝ ምን ጊዜም አልረሳውም። አምባሳደር ካሣም “ኢትዮጵያ ብናስጠራህ መጥተህ ታሳያለህ?” ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔም “በደስታ” ብዬ መለስኩላቸው። “ጥሪ እንዲደርስህ አደርጋለሁ” ብለውኝ ሄዱ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን፤ ዶክተር አበበ ሙሉነህ፤ (የዚያን ጊዜ ኮሚሽነር) የግብዣ ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ ጥሪውም “ስለሰራኸው ኮምፒውተር ዜና ደርሶን ደስ ብሎናል፤ መጥተህ የኛንም ተቋም ጎብኝልን፤ አንተም ስለ ሰራኸው ገላፃ አድርግልን” የሚል ነበር።
በፈረንጆቹ 1988 ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከገባሁ በኋላ በኢትዮጵያ ሬዲዮም በቴሌቪዥንም ቃለ መጠይቅ ተደረገልኝ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ፣ በጡረታ ሚኒስቴር፣ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በንግድ ሚኒስቴር፣ በቡናና ሻይ መስሪያ ቤት፣ በሕዝብ ደህንነት ጽሕፈት ቤት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች ትልልቅ ተቋማት ውስጥ እየተገኘሁ ማብራሪያ ሰጠሁ፡፡ ኮምፒውተሩም ሲሰራ አሳየሁ፡፡ አንዳንዶቹንም ፀሓፊዎች እንዲሞክሩት አደረግሁ፡፡ በወቅቱ ትልቅ ዜና ኾነ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ መኪና ከነሹፌሩ እየተላከልኝ ስዞር ቤተሰቦቼን በአግባቡ ሳልጠይቃቸው ወደ ሥራዬ መመለሻ ጊዜው ደርሶ ወደ አሜሪካን ተመለስኩ፡፡
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ያዘጋጁልኝን ውይይትና ፕሮግራሙንም ካሳየኋቸው በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ለሰፊው ሕዝብ ገለፃ ማድረጌን ቀጠልኩ። አንድ ቀን ብዙ ሰው በተሰበበበት በሂልተን ሆቴል አዳራሽ ገለፃ ሳደርግና ኮምፒውተሩን ሳሳይ አንድ ስድስት የሚሆኑ የኮማንዶ ልብስ የለበሱ መሳሪያ የያዙ ወታደሮች ገብተው ሕዝቡን ከአዳራሹ ካስወጡ በኋላ እነሱ ጥግ ጥግ ይዘው ቆሙ፡፡ ከዚያም አምባሳደር ካሣ ከውጭ በችኮላ ወደኔ መጥተው “ይህንን ማየት የሚፈልግ ሰው ይመጣል ጠብቅ” አሉኝ፡፡
የወታደሮቹን መሳሪያ አቀባብለው መቆምና የአምባሳደሩ ትዕዛዝ መሰል ሹክታ፣ ጥርጣሬና ፍርሕት አሳደረብኝ፡፡ ምክንያቱም በአሜሪካን አገር ኢትዮጵያ ውስጥ በዚያን ጊዜ የሚደረገውን ግድያና ጭፍጨፋ ተቃዋሚ ነበርኩ። በነበርኩበት ዩኒቨርሲቲና ባገኘሁት መድረክ ሁሉ የኢትዮጵያን የደርግ መንግሥት አወግዝ ነበር። ፖለቲከኛ ሆኜ ሳይሆን የወጣቶች መጨፍጨፍ አንገብግቦኝ ነው። መንግሥት ይፈልገኛል የሚል ሥጋትም በውስጤ አድሮብኝ ነበር፡፡ በአምባሳደር ካሣ በኩል ጥሪ ባይደርሰኝ ኖሮ ኢትዮጵያ መመለስ አደጋ ላይ ይጥለኛል ብዬ አስብ ስለነበር ኢትዮጵያ አልመለስም ነበር። ግብዣው ሲደርሰኝ ከብዙ ጊዜ የውጭ ቆይታ በኋላ በዚያውም የናፈቅኋቸውን ቤተሰቦቼን ለመጎብኝት መልካም አጋጣሚ ሆኖ ስላገኘሁት በድፍረት ነው አገሬ የተመለስኩት።
አዳራሹ ውስጥ ያለው ሕዝብ ከወጣ በኋላ ወታደሮቹ እና እኔ ቀርተን አዳራሹ ባዶ ኾነ፡፡ ከአንድ 20 ደቂቃ ቆይታ በኋላ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም 15 በሚኾኑ ሰዎች ታጅበው በዋናው በር ሲገቡ አየኋቸው። እኔም ጠርጥሬ ስለነበር ልቤ ትር ትር እያለ ኮምፒውተሩ ላይ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” የሚል በቀይ በትልቁ ጽፌ የኮምፒውተሩን ስክሪን ወደበሩ አዙሬ ጠበቅኋቸው። ጽሑፉን ገና ከሩቁ አይተው ፈገግ ሲሉ አየኋቸው፡፡ ያን ጊዜ እኔም ትንሽ ተንፈስ አልኩ። “የእንግሊዘኛ ኮምፒውተር ምንነት ገና ሳይገባን እንዴት በአማርኛ ልትሰሩት ቻላችሁ?” ብለው ጥያቄያቸውን ጀመሩ፡፡ “የሚረዳህ አለ? ኩባንያ ወይም ድርጅትህ ማን ነው?” የሚሉ ዐይነት ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቁኝ። እኔም በተቻለኝ መጠን ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡ አንድ ጽሑፍ ከኮምፒውተሩ አትሜ ሳሳያቸው “ይሄን የመሰለ ጥርት ያለ ጽሑፍ የሚያትም መሳርያ የሰራው ካምፓኒ ማን ይባላል?” ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔም የጽሑፉ ምንጭ ሀርድዌሩ ሳይኾን ሶፍትዌሩ መኾኑን ተናገርኩ፡፡ “እኮ ምን ማለትህ ነው?” ብለው አፋጠጡኝ፡፡ እኔም “ለምሳሌ የእርሶ ንግግር ተቀድቶ በካሴት በተለያዩ የካሴት ማጫዎቻ ሶኒ ወይንም ፊሊፕስ ውስጥ ሲገባ ያው የሚወጣው የርሶ ንግግር ነው። አሁን የርስዎ ንግግር እንደ ሶፍት ዌር ቢቆጠር፤ ማጫዎቻው ደግሞ ሃርድዌር ነው ማለት ነው፡፡ በየትኛውም ማጫወቻ ንግግሩን ያደምጡታል። ይኼም ፕሪንተር ሀርድ ዌር ነው ማለት ነው” ብዬ አስረዳሁ።
ከዚያም የደህንነት ኃላፊው ኮሎኔል ተስፋዬ ዘንድ ተጠርቼ ሄድኩ፡፡ አባቴ እኔ ይዤህ እሄዳልሁ ብሎ ይዞኝ ሄደ። እቢሯቸውም ውስጥ ብቻዬን አነጋገሩኝ፤ አመሰገኑኝ። ኮምፒውተር ሌላ ለመንግሥት የሚጠቅም መረጃ መስብሰብ ያስችለናል ወይ? ብለው ጠየቁኝ፡፡ በድርጅቱ ሥር የሚገኙትንም የቴክኒካል ሰዎች አስጠርተው አንድ 3 ሰዓት ያህል የወሰደ አጠር ያለ ሥልጠና እንድሰጥ ተደረገ። በተቻለኝ ጥያቄዎቻቸውን የሰራሁት ሶፍትዌር ምን እና እንዴት እንደሚሰራ መለስኩላቸው። የመረጃ መሰብሰብና ሌላም ፖለቲካ ነክ ነገሮች ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አረጋገጥሁላቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን አባቴ ውጭ ይጠብቀኝ ነበር።
ግዮን፡- በዚሁ አጋጣሚ በሀገራችን ያለውን የንባብ ባሕል እንዴት ያዩታል? መንግሥትስ በዚህ ዙሪያ ምን መሥራት አለበት ይላሉ?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- አሁንም ባለንበት ዘመን በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የማንበብ ፍላጎት እንዳላችው በየማኅበራዊ ሚዲያ በሚደርሱኝ ደብዳቤዎችና አማርኛ መፅሕፍትን ዲጂታይዝ አድርጌ በነፃ ከማካፍልበት ድረገፅ ተፈላጊነት መረዳት ችያለሁ፡፡ በጣም ደስ የሚል የአማርኛ መጻሕፍትን የማነበብ ፅኑ ፍላጎት እንዳለ ነው የሚያሳየኝ። እኔ በልጅነቴ የተለያዩ የአማርኛም አቅሜ እስከፈቀደልኝ ደግሞ የእንግሊዝኛ መጻሕፍቶችን አነብ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤቴ ውጭ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው ወመዘክር፣ አሜሪካን ላይብረሪ፣ የራሽያና የእንግሊዝ ላይብሬሪዎች ነበር፡፡ እነዚህ ተቋሞች እስካሁን አዲስ አበባ ላይ ይኑሩ አይኑሩ አላውቅም። ብዙዎች የማነበብ ፍላጎት ያላቸው የሚያነቡት እንዳይቸገሩ በማለት የተለያዩ መጻሕፍቶችን አርካይቭ እያደረኩ ለብዙዎች እንዲያነቡ በነፃ አካፍላለሁ፡፡ የኦንላይን መጻሕፍት ቤቱን ከጀመርኩ ከአምስት ዓመት በላይ ኾኗል፡፡ መጀመሪያ ላይ የራሴ “አምሐሪክ ቡክ” (Amharicbooks.org) የሚባል ነበር፡፡ በኋላ ግን ሁሉም በቀላሉ ማግኘት በሚችለው መልኩ የኢትዮጵያን ቅርስ ለማቆየት በርካታ የቀድሞ መጻሕፍትን ጭኜበታለው፡፡ በዚህም በርካታ ሰዎች እንደሚያነቡ ይነግሩኛል፤ አመስግነውኛልም፡፡ በ80 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላት እናቴ አሜሪካን እኔን ልትጠይቅ መጥታ የጧት ፀሎቷን ካደረሰች በኋላ መጽሐፍቶቼን ከየመደርደሪያው እያወረደች ስታነብ ትውላለች፤ በስልኳም ላይ የተለያዩ የአማርኛ መጻሕፍትን ስታነብ “በኔ ይሆን እንዴ የወጣችው?” እያልኩ እቀልዳለሁ።
ድሮ የማንበብ ሁኔታ አማራጭ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ዘመኑ የዲጂታል በመኾኑ ትውልዱ የግድ ወረቀት ላይ ብቻ የተፃፈን ብቻ ማንበብ አይደለም፡፡ አንዳንዶች አሁንም ዲጂታል መጻሕፍትን አንብቡ ስላቸው የሚፈልጉት በመጽሐፍ መልኩ ታትሞ የሚወጣውን እንደሆነ ይነግሩኛል፡፡ በጥቅሉ ግን የማንበቢያው መንገድ ተለያይቷል (በኮምፒውተርና በስልክም) እንጂ የንባብ ባሕሉ አሁንም አለ፡፡ አሁን ላይ ደግሞ “ተራኪ” እና የመሳሰሉ መጻሕፍቶችን በድምፅ (Audio Books) የሚተርኩ በርካታ መተግበሪያዎች ወጣት ኢንጂነሮች እየሰሩ ሳይ ብዙ ተስፋ ይሰጠኛል። ስለዚህ የንባብ ባሕል የራሱን የዘመን ቅርጽ በመያዙ እንጂ ደካማ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እዚህ አሜሪካን ሀገርም አንዳንድ መጻሕፍት ቤቶች እየተዘጉ ነው፡፡ ይህ የኾነው ሰው ስለማያነብ ሳይኾን የንባብ መንገዱ ስለተቀየረ ነው፡፡ ለነገሩ እኔም በድምፅ የሚሰሙ (ኦዲዮ ቡክ) መጻሕፍቶችን ማንበብ ይቀለኛል፡፡
ግዮን፡- መጽሐፍ ያላቸው ሰዎች አትመው መሸጥ ይፈልጋሉ፡፡ ሰው በነፃ በዲጂታል መልክ የሚያገኘው ከኾነ ጸሐፊው እና በእዚያ ዙሪያ ያሉ መጻሕፍት ነጋዴዎች እና መሰል አካላት ላይ ተጽእኖ አያሳድርም?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- እኔ አርካይቭ ላይ ያነበቡ ሰዎች “መጽሐፉን የት እንግዛው” ብለው የጠየቁኝ ሰዎች አሉ፡፡ የመጽሐፍ ፍቅር ያለው ሰው ገዝቶ በመደርደሪያው ማስቀመጥ ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የአክሊሉ ሀብተወልድ “ማስታወሻ” የሚለውን መጽሐፍ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬስ ነው ያሳተመው፡፡ መጽሐፉን ከሦስት ዓመት በፊት ገዝቼው በዲጂታል አትሜ ለማቅረብ አታሚዎቹን (Addis Ababa University Press) ሳማክራቸው በጣም ደስተኛ እንደሚኾኑ ነው የነገሩኝ፡፡ ብዙዎቹ ፀሐፊዎችና አሳታሚዎች እንደማስታወቂያ ነው ያዩት። እኔ ደግሞ የሰው መጽሐፍ ወደ ዲጂታል ስለቀየርኩ ገንዘብ አላገኝበትም ከፍላችሁ አንብቡ የማለት ፍላጎትም መብትም የለኝም፡፡ ስለዚህ በገበያ ላይ የሚገኙ መፅሐፍት ግለሰቦች ከኮምፒውተር አውርደው አትመው ለመሸጥ እንዳይሞክሩ (ኮፒ እና ፕሪንት እንዳይኾን) አንባቢው ስልኩና ኮምፒውተሩ ላይ ብቻ እንዲያነብ እንጂ ገልብጦ ለማተም እንዳይቻል አድርጌዋለሁ።
ግዮን፡- ወደ ዲጂታል የቀየሯው መጻሕፍቶች በባለቤቶቹ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- አዎ ፍቃድ እጠይቃለሁ፡፡ ብዙዎቹ ግን የድሮ የታሪክ መጻሕፍቶች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን አርካይቬ ላይ ያሉ መጻሕፍቶች ባለቤቶቹ ወይንም ባለመብቶቹ “አንሳው እየሸጥነው ነው” ካሉኝ አነሳዋለው፡፡ በዋናነት ትኩረት የማደርገው የቆዩና የጠፉ በቀላሉ የማይገኙ የታሪክ መጻሕፍቶች ላይ እንጂ በቅርብ የታተሙት ላይ አይደለም፡፡ የኾነ ወቅት ላይ ወመዘክር ያሉ ጥቂት የማይባሉ መጽሐፎች “አያስፈልጉም” ተብለው ተጥለው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ነው እኔ መጻሕፍቶቹን ለማቆየት በማሰብ በታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍትን በዚህ መልኩ ዲጂታይዝድ አድርጌ አቀረብኳቸው፡፡
ግዮን፡- እርሶ የሰሩት የአማርኛ ሶፍትዌር አገራችን ላይ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በሀገራችን ብዙ መጻሕፍቶችና መጽሔቶች ይታተሙ እንደ ነበር እናውቃለን፡፡ ይህ ሊኾን የቻለው ምን ዓይነት የአሠራር ሂደት በመከተል ነበር?
ኢንጂነር ፍሥሓ፡- መጀመሪያ እንደሚታወቀው በብራና፤ በመቃ እና በብዕር በእጅ ነበር የሚፃፈው፡፡ በኋላ ግን ለቢሮ የሚያገለግል የአማርኛ የጽሕፈት መኪና (ታይፕራይተር) የሚባል የወለጋ ተወላጅ በኾነው በአቶ አያና ብሩ ዲዛይን ተደርጎ ጥቅም ላይ ሊውል ቻለ። ጽሑፎቹም ፊደሉ በብረት ተቅርፆ፤ መፃፊያው አንድ በአንድ በጣት ሲነካ ፊደሉን አንስቶ ወረቀቱ ላይ የሚያትምበት ሂደት ነው የነበረው፡፡
ማተሚያ ቤቶችም ለማተም በትንንሽ ብረቶች የተቀረጹ ፊደሎችን በለቃሚዎች (አዎ ሥራቸው ፊደል ለቃሚ የነበሩ ሠራተኞች ነበሩ) የሚደረግ አሠራርን ነበር የሚጠቀሙት፡፡ ጋዜጦችና መጻሕፍቶች በዚህ መልኩ ነበር እየተለቀሙ የሚሠሩት፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ ሴንትራል ማተሚያ ቤት፣ አሥመራ ማተሚያ ቤትና ሌሎች ማተሚያ ቤቶችም ይኽንኑ መንገድ ነበር የሚከተሉት፡፡ እኔ ልጅ ሆኜ ከትምህርት ቤታችን ተወስደን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትን የመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር፡፡ በትንንሽ ብረት ላይ የተቀረፁ ጉብ ጉብ ያሉ ፊደሎች፤ በየጆንያው ተቆልለው ሳይ በጣም ነው የተደነቅሁት፡፡ “ፍ” “ሥ” “ሓ” የሚሉትን ፊደላት ፈልጌ ከሦስት የተለያዩ ከረጢቶች አገኘኋቸውና “ልውሰዳቸው?” ብዬ ጠይቄ አይሆንም የተባልኩትን አስታውሳለሁ። በዚህ ወቅትም ፊደሎች በምን መልኩ ታትመው ጋዜጣና መፅሐፍ እንደሚታተሙ ለማየት ችያለሁ፡፡
ከ30 ዓመታት በኋላ፤ የኢትዮጵያን ምሰለ ፊደላት በሥዕሎቹ በዓለም የታወቀው አርቲስት ወሰኔ ኮስሮፍ የተባለው ጓደኛዬ አዲስ አበባ ኢክዚቢሽን ለማሳየት እያንዳንዱን ፊደሎቻችንን ከሰው ቁመት በላይ በሆኑ ሐውልቶች ቀርፆ ለማጓጓዝ የነበረበትን ችግር ሲነግረኝ፤ በጣም በመገረም “ፊደሎች ሲጫኑ” የሚለው የፃፍኩት ግጥም በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ሆኗል። የእያንዳንዱንም ምስለ ፊደል በልዩ መረዳት እንዳየው ረድቶኛል።
ግዮን፡- የአማርኛን ኮምፒውተር ፕሮግራም ሶፍትዌር በመሥራት የመጀመሪያው ሰው እንደ ሆኑ ይታወቃል፡፡ ግን የሶፍትዌር ባለቤትነት ማግኘት ያልፈለጉት ለምንድነው? ሶፍትዌሩንስ ወደ ኮምፒውተር ለማስገባት ፓተንት አለነበረውም?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- የአማርኛ ሶፍትዌር ሲባል ፤ እኔ በዚያን ጊዜ የሰራሁት “የአማርኛ የድርሰት ማቀነባበርያ” (Amharic Word Processor) ይህም ማለት የተሰራውን የእንግሊዝኛ ድርሰት ማቀነባበርያ የኢትዮጵያ ፊደላት እንዲገባበት ማድረግ ነበር። ያ ሂደት አሁን ሲታሰብ በቀላሉ መሥራት ይቻላል፡፡ በዚያን ጊዜ ግን አስችጋሪ ነበር፡፡ ዊንዶውስ፤ ማውስና የመሳሰሉ ብዙ የሶፍትዌር መገልገያዎች ገና አልተፈጠሩም ነበር፡፡ ፊደላችንን አንድ በአንድ በእጄ እየቀረፅሁ ነው ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲካተት ያደረግሁት። ቀደም ብዬ እንደተናገርሁት ድርሰት ማቀነባበሪያውን የሰራሁት ለራሴ ድርሰቴን ለመፃፍ ስለነበር የመሸጥ ሃሳብም አልነበረኝ፡፡ በመጀመሪያ ሥራውን ሰምተው ለጠየቁኝ ሁሉ በነፃ በደስታ ለተወሰነ ጊዜ ስልክ ነበር። ነገር ግን ፈላጊዎች እየበዙ ሲሄዱ ዳሸን ኢንጂኔርንግ የሚባል ድርጅት አቋቁሜ አቅም ላላቸው በክፍያ፣ ለተማሪዎች፣ ለቀሳውስት፣ ለወንጌል አስተማሪዎች፣ ለጡረተኛ አረጋውያን በትልቅ ቅናሽ ወይንም በነፃ ማከፋፈል ጀመርኩ፡፡ ስለዚህ ሲጀመር “ባለቤትነት መታወቂያ” ወይንም “ፓተንት” በብዛት ለሰው ሊዳረስ ለምፈለግው ግኝት አግባብ ነው ብዬ አላየሁትም። እኔ በዚያን ጊዜ ለኤችፒ (Hewlett Packard/HP) ጥሩ ሥራ በትልቅ ደሞዝ እሰራ ነበር፡፡ የአማርኛውን ፕሮግራም የሰራሁት በትርፍ ጊዜዬ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥም የተመሰገነ ይሁን የገንዘብ ችግር አልነበረብኝም። ስለዚህ መብት ማስጠበቅ ለሽያጭ ማቅረብ የሚለውን አስቤውም አላውቅም ነበር።
ደግሞም ብዙ ሰዎች “ተማርን” የሚሉትንም ጨምሮ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ምስለ ፊደል “የኔ ነው የሚባል” እንዳይደለ አይረዱትም። ፊደልን ለቅሞ ኮምፒውተር ውስጥ በእንግሊዝኛው ፈንታ ማስገባት ልዩ አዲስ ጥበብ አልነበረም፡፡ እርግጥ በልዩ ልዩ ቅርፅ እያስዋቡ ፊደችላችንን የሚያስውቡ አርቲስቶች “ይህ የኔ የፈጠርኩት ቅረፀ ፊደል ነው” ብለው የባለቤትነት መታወቂያ ቢጠይቁ አግባብ ነው። ሌሎች ደግሞ ኦፐሬቲንግ ሲስትም በአማርኛ ሰርተው (ሳይተረጉሙ ማለት ነው) የሚያቀርቡ “ፓተንት” ወይንም ግኝቱ የራሴ ነው ቢሉ ትክክል ናቸው። ግን አሁን “ፓተንት” አለን እያሉ ሰውን ለማሳመን የሚሞክሩ አልፎ አልፎ አሉ፡፡ እነሱ የአማርኛ ወይንም የኢትዮፒክ ፓተንት የሚሉት፣ አንድ ሰው ታይፕ ሲያደርግ “ሀ” “ለ” “ሰ” ኪቦርዱ ላይ ምን መስሎ ይስፈር የሚለው ነው። አንዳንዶች ለምሳሌ “ሀ” ለመፃፍ “He” ሲጠቀሙ ሌሎች ደግሞ “Ha”; “Hv” “H” ይሄ እንግዲህ እያንዳንዱ የአፃፃፍ ዘዴ “ልዩ” ተብሎ በአሜሪካን ባለቤትነት ሲጠየቅበት ፓተንት ይሰጠዋል ማለት ነው። እስካሁን በአሜሪካን አገር ፓተንት ቢሮ ከሃያ በላይ የተለያዩ የአማርኛ ኪቦርድ አፃፃፍ ዘዴዎች ቀርበው ለዘዴዎቹ “ፓተንት” አግኝተዋል።
ይህም ማለት የኪቦርዱን ሰንጠረዥ (Keyboarding) ሌላ ሰው ያላሰበው ወይም ካለውን ትንሽ ለወጥ አድርጎ በማቅረብ ነው ፓተንቱ የተገኘው ማለት ነው። ለምሳሌ እኔ ያን ጊዜ ስሠራ በአማርኛ ታይፕ ራይተር ላይ ያለውን እንዳለ ቁጭ አድርጌ ነው የሰራሁት፡፡ ምክንያቱም ያኔ የነበሩ ጸሐፍያን የሚያውቁትና የተለማመዱት በዚያ መልኩ ያለውን ስለኾነ ለእነርሱም እንዲቀላቸው ብዬ ታይፕራይቱንም ተከትዬ ሠርቼዋለሁ፡፡ ይህን ሌሎች ሰዎች መጥተው ሊቀይሩት ይችላሉ፡ አሻሽለው ቀይረውትማል። ይህንንም በአሜሪካ የፓተንት ዝርዝር on-line ማግኘት ይቻላል። ይህንን አይነት “አዲስ” ዘዴ ለመፍጠር ከሁለት ቀን በላይ አይፈጅም። ለዚህም ዘዴ መፍጠሪያ ዮኩሌሌ (https://software.sil.org/ukelele/) የተባለና ሌሎችም ብዙ ብዙ ሶፍትዌሮች በነፃ ይገኛሉ። በዚህ መንገድ ሄደው “ፓተንት” አለን የሚሉ ሰዎች መብታቸው ስለሆነ ምንም ተቃውሞ የለኝም። ከዚህ ሌላ ግን “የኢትዮጵያን ፊደል በኮምፒውተር ለመጠቀም አትችሉም፤ መብቱ የኔ ነው” ለሚሉና ሌሎች ፊደላችንን ተጠቅመው ልዩ ልዩ መተግበርያዎችን እንዳይፈጥሩ ተስፋ ለሚያስቆርጡ ሰዎች “የኢትዮጵያ ፊደል” የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በዩኒኮድ (UNICODE) ተመዝግበው ለማንም የኮምፒውተር ተጠቃሚ በነፃ ለማገልገል ተዘጋጅተዋል፤ ማንም የተለየ መብት የለውም እያልኩ ከማስረዳት አልቆጠብም።
“UNICODE” የተባለው ይህ ድርጅት ከ30 ዓመት በፊት ለዚሁ ጉዳይ የተቋቋመ፤ በዓለም ያሉትን ቋንቋዎችን ሁሉ አካትቶ ቦታ ቦታ የወሰነላቸው፤ ሁሉም የኮምፒውተር ፈብራኪዎች የሚሳተፉበት ተቋም ነው። እኔም በመጀመሪያ HPን እና ዳሸን ኢንጂኔርንግን፤ ወክዬ አንዱ መስራች አባል ነኝ። እስከመጨረሻው የፊደላችን ስም ኢትዮፒክ ተብሎ በኮምፒውተር ዓለም እንዲሰየም ሌሎች ኢትዮጵያውያንን አሰባስቤ የማስረጃ ደብዳቤ ላለሁበት ኮሚቴ በመፃፍ በብዙ መረባበርብ በሙሉ ድምፅ የፊደላችን የዩኒኮድ ስሙ ኢትዮፒክ (ETHIOPIC) እንዲሆን ተወስኖ እስከ ዛሬ በዚሁ ይታወቃል። አዳዲስ ኮምፒውተሮች ሲፈበረኩ ይህንን የኢትዮፒክ ፊደላት አካተው ስለሆነ፤ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም ኮምፒውተር ላይ በፊደላችን ለመጠቀም እንደ ድሮው “ዳውንሎድ” ወይንም መግዛት አስፈላጊ አይደለም።
እርግጥ የዛሬ 30 ዓመት እኔ ዳሸን ኢንጂኔርንግ በተባለው በግሌ ተቋም በተጠቃሚ እጅ ገብቶ መገልገያ ለመሆን የመጀመሪያው የአማርኛ ድርሰት ማቀነባበሪያ ቢሆንም በዚያኑ ጊዜ አካባቢ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌሎች ብዙ ጥረት የሚያደርጉ እንደነበሩ መዘንጋት የለበትም፡፡ በተቻለኝ ሁሉ ስለዚህ ጉዳይ ስናገርና ስሜ ሲጠራ እኔ ደግሞ እነዚህን ሰዎች ከመዘከር አልቆጠብም ። ከእነሱም መሃል ይጥና ፍርድ ይወቅ፣ ዳንኤል አድማሴ፣ ፈቃድ መስፍን ስለሺ፣ አባስ ዓለምነህ፣ የማነ ርእሶም የሚባሉ ይገኙባቸዋል።
————————–
ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን ከኢንጂነር ፍሥሐ አጥላው ጋር ደረግነው ቆይታ በዚህ አልጠናቀቀም፡፡ ስለግብረ ሰናይ አገልግሎታቸውና ስለሌሎችም ጉዳዮች ያደረግነውን የመጨረሻውን ክፍል ቆይታ በቀጣይ ዕትም ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡