” የልደት በዓል ረቡዕ ወይም አርብ ቀን ቢሆን አይጾምም ፤ ይህም በፍትሐ ነገሥት ላይ የተደነገገ ነው”

Date:


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ህግጋት መሰረት ከአጽዋማት መካከል አንዱ በሆነው ረቡዕ እና አርብ እለት የልደት በዓል ቢውል ይጾማል ? ወይስ ፍስክ ነው ? (የጥሉላት ምግብ ስጋ፣ ቅቤ ፣ ወተት፣ እንቁላል … ይበላል ?) የሚሉ ጥያቄዎች በሰፊው ቀርበዋል።

በቤተክርስቲያኗ ህግጋት መሰረት አንዱ የጾም ጊዜ በሆነው ረቡዕና አርብ እለት የልደት በዓል ቢውል ይጾማል ? ወይስ ይበላል ? ለምን ? ሲል የጠየቃቸው የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት፣ ፍስክ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመሪ እቅድ መመሪያ ኃላፊ መላከሰላም ሰለሞን ቶልቻ እንዳሉት፣ የልደት በዓል ረቡዕ፣ አርብ እለት ቢውል ” በፍትሐ ነገሥት በተደነገገው ” መሰረት አይጾምም።

ጥምቀት ረቡዕ ወይም አርብ ቢውል ማክሰኞ ወይም ሐሙስ ተጹሞ (ገሃድ/ጋድ ይባላል) የበዓሉ እለት (ረቡዕ ወይም አርብ) የፍስክ እንደሚበላ ገልጸው፣ ” በዓለ ልደት ግን ገሃድ/ጋድ የለውም። ምክንያቱም በጾም ላይ ጾም የለም ” ብለዋል።

” በፍተሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 603 እንደተደነገገው የልደት በዓል ረቡዕ ወይም አርብ ቢውል የደስታ ቀን ስለሆነ አይጹሙት ይላል ” ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

ለምን እንደማይጾም ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም፣ ” ምክንያቱም በጌታ መወለድ ሰው እና መላዕክት፣ ምድራዊያንና ሰማያውያን የታረቁበት፤ የጥሉ ግድግዳ የፈረሰበት እለት ስለሆነ ነው ” ብለዋል።

የልደት በዓል ረቡዕ ወይም አርብ ቀን ቢሆን የማይጾመው፣ ” በፍትሐ ነገሥት ስለተቀመጠ፤ በቀኖና መፅሐፍት ላይ የተደነገገ ስለሆነ ነው ” ሲሉም አስረድተዋል።

” በሞት ጥላ መካከል ላለ ህዝብ ነጻነት እንደተሰበከ ሁሉ የልደት በዓል የደስታ ቀን በዓል ነው። የአበው የተስፋ ቃል፤ የነብያት ትንቢት የተፈጸመበት፤ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ቃልም የሚፈጸምበት የደስታ ቀን ነው ” ብለዋል።

” ይህ ቀን የሀዘን ቀን አይደለም፤ የደስታ ቀን ስለሆነ አበው በፍትሃ ነገስት እንዳስቀመጡት በዓለ ልደትን ረቡዕ፣ አርብ እለት ቢውል እንደማይጾም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና እና ስርዓት የተደነገገ ነው ” ሲሉ ገልጸዋል።

” ዮም ፍሰሃ ኮነ በእንተ ልደቱ ነው ለእግዚእነ፤ (በጌታ መወለድ ደስታ ሆነ) እያልን የምንዘምርበት ነው ” የሚሉት መጋቢሰላም ሰለሞን፣ ” በዚህ ቀን የፍስክ ምግብ ነው የምንበላው፤ አይጾምም። ገሃድ/ጋድን በተመለከተ የጥምቀት በዓል ረቡዕ፣ አርብ ቢውል ማክሰኞ ወይም ሐሙስ ይጾማል። ገሃድ ማለት ለውጥ ስለሆነ ” ብለዋል።

” የልደት በዓል በጾመ ድህነት (ረቡዕ እና አርብ) ላይ ከዋለ አይጾምም ” ብለው፣ ” ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን፣ በዓሉን በዋዜማው በቤተክርስቲያን አጥቢያ በመሄድ ምሽቱን በማህሌት፣ በስብከት፣ በጸሎት እንደሚተጉ፣ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ ቅዳሴ እንደሚገባ፤ ከዚያ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ በመፈሰክ በዓሉ እንደሚከበር ገልጸዋል።

ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጽሐፍትና ወመዘክር መምሪያ ኃላፊ የሆኑት በኩረ ትጉሃን ቀሲስ ምትኩ ከንቲባ በበኩላቸው፣ “ይበላል” ሲሉ መልሰዋል።

@tikvahethiopia

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ...

የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የ5 በመቶ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና...

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ለኢራን ህዝብ – “እኛ ከእናንተ ጋር ነን”

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ፥ የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ...

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና...