ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ነው፡፡ ሰብዓዊ ተግባራት ሰው ሰው በመሆኑ የሚያደርጋቸው ተግባራት ናቸው፡፡ ሰው በተፈጥሮው ሰብዓዊነት የሚሰማው ልዩ የፈጣሪ ፍጥረት ነው፡፡ ይኸውም፡- የሚሆነው ሰው መጀመሪያ ሲፈጠር የማስተዋልና የማመዛዘኝ ችሎታ እንዲኖረን የህሊናና የአዕምሮ ባለቤት እንዲሆን ተደርጎ የተፈጠረ በመሆኑ ነው፡፡
ሰብዓዊ ተግባራት በውስጡ መረዳዳትን፣ መተሳሰብን፣ መዋደድን፣ መከባበርን፣ መረዳዳትን ፣መገናዘብን፣ መፋቀርን፣ መደራረስ …. ወዘተ የሚከውን ተግባር የሚያከናውን ሆኖ መገኘትን ነው ታሳቢ የሚያደርገው፡፡ የሰብዓዊ ተግባራት መስፋፋት ለሀገር ሁለንተናዊ ተግባራት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
እነዚህ ተግባራት በሀገራት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሰው እርስ በራሱ ከተዋደደና ከተፋቀረ፣ በመዋደድና በመፋቀር ወስጥ አርስ በራሱ ከተከባበረ ከተሳሰበና ከተረዳዳ ሰላማዊ የሆነ ዕድገትና ብልጽግና ባለቤት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ይህም የጽንሰ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር መመልከት የምንችለውና የሚቻል መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ፈተናው ጠንከር ያለና ውስብስብ ሆኖ እንመለከታለን፡፡
ይህም ሰው በተግባር በነጠላም ይሁን በቡድን እራሱን ከመውደዱ ብዛት ከችግር፣ ከዕውቀት ማነስ፣ በዕድገት በመነጩና በሌሎችም ምክንያቶች ሳቢያ በብዛት እንደሚስተዋለው በተፈጥሮው የሚጠበቅበትን ሰብዓዊነት ተላብሶና አድርጎ በምግባሩ ሊገኝ እንዳልቻለ ምግባሩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ትክክለኛውንና ጠቃሚውን የሰብዓዊነት መመዘኛ ነጥቦች በምግባሩ በማሟላት ሰው ሊባል ይችል የነበረው ፍጡር ስለራሱ ብቻ የተለየ ጎጂና የማይጠቅም ፍቀር የማይኖረውና መላ እምነቱን በፈጣሪው ላይ በማሳረፍ ነገሮችን እያመዛዘነና በጎውን ከመጥሮው እየለየ ተቀባይነት የሚኖራቸውን ሥራዎች ብቻ ተግባራዊ የሚያደርግ መሆን ነበረበት፡፡ ይህም መሆን የሚገባው ሰው ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ጥልቅና ውስብስብ የሆኑ ነገሮችን መርምሮ በቀላሉ መረዳት የሚያስችል ሕሊናና አዕምሮ ተጎናጽፎ በመሆኑ ነው፡፡
ስለሆነም ሰው አውቆበት ቢሆን ኖሮ ሁኔታዎችን እያገናዘበ በፈጣሪም ሆነ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸውን ተግባራት የትኞቹ እንደሆኑ ሊረዳ የሚችልበት ችሎታ ስለተሰጠው በብዛት በምግባር በገለጠው ነበር፡፡
ዳሩ ግን ይህን ወደር የማይገኝለት የማሰብና የመመራመር ችሎታ ይዞ በጎ ተግባራትን እየሠራ መኖር ሲገባው በተቃራኒው ከምንም በላይ እራሱን በመውደድ ተሸንፎ ከመነሻውም በመሳሳት የጥፋትን ጎዳና በመምረጡ በለስን እንዳይነካ የሚደነግገውን ለሰው ልጅ የተሰጠውን የመጀመሪያ የፈጣሪ ሕግ ጥሶ ይኸውም ከማንኛውም ጊዜ በተለየ መልኩ አሁን በሚገኝበት ከፈሩ በወጣ የአኗኗር መስመር ላይ ተሰማርቶ ለመገኘት በቅቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ጥቂቶች ግን የተሻለ መልካምና በጎ የሆነ ተግባር አከናውነው ያለፉና በመስራት ላይ የሚገኙ እንዳሉ ዕሙን ነው፡፡
ሰው በሙሉው የሕይወት ዘመኑ በተሰጠው የማሰብ ችሎታው እየተጠቀመ ገቦ ሥራዎችን ብቻ እያከናወነ ማለፍ ይገባው ነበር፡፡ ይኸውም በአለማዊ ሕይወቱም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የተሻለ ስብዕናን እንዲላበስ የሚያስችለው ይሆናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በብዛት እንደሚስተዋለው ሰው በብዛት መላ አስተሳሰቡና መንፈሱ መጥፎ ድርጊቶችን በመፈፀም ዝንባሌ ላይ ማተኮራቸውንና ቀና ማሰብም ጨርሶ እንዳልሆነለት ሲመለከት ፈጣሪ እንደገና በጎና ክፉ ተግባራትንና አስተሳሰቦችን ለይተው የሚያሳዩ ሁለት ሕጎችን ለሰው ልጅ በመተዳደሪ ደንብነት ዳግመኛ እስከመስጠት ተገደደ፡፡ ከተሰጡት ሁለት ደንቦች ውስጥ አንዱ ክፍል በፈጣሪና በሰውም ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸው ተግባራትን ዘርዝሮ የሚያሳይና በግድም መተግበር የሚገባቸው መሆናቸውን የሚደነግግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የማይፈለጉ ተግባራትንና ሊወገዱ የሚገባቸውን አስተሳሰቦችና ሁኔታዎችን በግልጽ እያብራራ የሚያስረዳ ነው፡፡
በዚህም መሰረት በሕጎቹ የመጀመሪ ክፍያ ውስጥ የተጠቃለሉት አንቀጾች በአንዱ አምላክ ብቻ ማምለክና መመካት፣ ለወላጆችና ለሁሉም ሰው ከበሬታ መስጠት፣ በሁሉም ረገድ አዘውትሮ ታማኝ መሆን የታመሙና የተቸገሩ ሰዎችን ማጽናናትና መርዳት ለሃቅና ለእውነት መቆምና ለራስ የሚሹትን ሁሉ ለሌላ ደርሶ ለራስ እንዳገኙት አድርጎ መደሰት መቻል በሁሉም ሰው ዘንድ መከበር ያለባቸው ግዴታዎች መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ የሚካተቱት አንቀጾች ደግሞ የአመንዝራነትን አፀያፊነት፣ በሐሰት መመስከርና መማል ኃጥአት መሆናቸውን፣ የስርቆትና ዝርፊያ አስነዋሪነታቸውን የግድያና ቂም በቀልና አስከፊነት ሰግብግብነትና ንፋግነት የሚጠሉ ጠባያት መሆናቸውን የምቀኝነትና እንዲሁም ስድብና አሉባልታ በእጅጉ የተወገዙ ተግባራትነታቸውንና ሰዎችን ማጣላት ማጋጨትም መልካም ያልሆኑ ድርጊቶች መሆናቸውን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
ከፈጣሪ ተችረውት የነበሩት ተከታታይ ስጦታዎች ሲታሰቡ ሰው ከምንም በላይ እራሱን በመውደድና ከሚያውቃቸው ሁሉ በሁሉም ረገድ በልጦ በመገኘት ፍላጎት ግፊት ባይሸነፍ ኖሮ ዓለማችን በፍቅርና በመግባባት የተሞላች ልትሆን በቻለች ነበር፡፡ እናም ይህ ዕድል በዓለም ላይ ሰፍኖ ቢሆን ኖሮ ደግሞ በዚያው ልክ ሰውን መርዳትና ከችግር መገላገል፣ እገሌ ተዕገሌ ሳይባል ወገን የሆነ ሁሉ የሚጠቀምበትና ምቾትና ብልጽግናን ሊጎናፀፍ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸትና ለዚህም የሚያግዙ ዘዴዎችን ለመፍጠር መጣጣር የሰው ሁሉ የደስታውና የእርካታው ምንጮች ይሆኑ ነበር፡፡ በዚያውም የሁሉም ሰው ምኞትም የራሴን የቤተሰቤንና የዘመዶቼን ፍላጎት ካሟላሁ በኋላ የድካሜና የጥረቴ ፍሬና ውጤት ለሌሎች መዳረስ ይችል ዘንድ እኔስ በበኩሌ ምን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርብኝ ይሆና? የሚል ሊሆን ይችል እንደነበር መረዳቱ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡
ይህ ቢሆን ኖሮ ደግሞ የሰው ማንነቱ የሚለካው አሁን እንደሚደረገው ባለው ሃብትና ንብረቱ መጠን ሳይሆን መመዘኛው ለአገርና ለወገን የሚያስመዘግበው መልካም ሥራና ጠቃሚ ውጤት ይሆን ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ መንገድ ሁሉም ሰው የራሱን ጥቅም እየሰዋ ከራሱ ባሻገር ለሌላ በሚቸገርበትና በሚጠበብበት ዓለም ቅናት፣ ምቀኝነት፣ ሌብነት፣ ሃሜት፣ ጥላቻና መሰል እኩይ ተግባራት ሁሉ ጨርሶ ቦታ አይኖራቸውም ነበር፡፡ በዚያውም ልክ ዓለማችን ፍቅር፣ ፀጥታ፣ ምህረትና ይቅር ባይነት ሰላምና መተማመን የሰፈነበት ዓለም ዕውን ሆኗ ማየት በቻለ ነበር፡፡
አቅም በፈቀደ መጠን ለሁሉም በጎ ማድረግና ተቀባይነት የሚኖራቸውን መልካም ሥራዎች ብቻ ማከናወን የሚጠቅም መሆኑን ለመረዳት አንዳንድ ያለፉ ታሪኮችን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለማስረጃም ያህል በጥፋት ውሃ ጊዜ ያ ሁሉ ሕዝብና ፍጥረታት ሲያልቁ ኖህና ቤተሰቦቹ ሊተርፉ የቻሉት ሎጥና ቤተሰቡ ከሰዶምና ገሞራ ሰደድ ዕሳት ለማምለጥ የበቁት፣ ንጉሥ ዳዊት በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲነሱበት የነበሩትን ጠላቶች ድል እያደረገ ሲመልስ የነበረው አባታችን አብርሃምም የሰይጣንን ተንኮል እየደጋገመ ሲያከሽፍ የነበረውና ኢዮብም ያንን ሁሉ መከራ፣ ስቃይና ፈተና ሊወጣ የቻለው ሁሉም ሙሉ እምነታችውን በፈጣሪያቸው ላይ ብቻ በማድረጋቸውና ራሳቸውንም ለመልካም ሥራ አሳልፈውና ለዲሲፕሊንም በማስገዛታቸው ነበር፡፡
ነገር ግን የሰው ልጅ ይህንን ሁሉ እየደጋገመ ቢያይና ቢመለከትም ለራሱ ምቾትና ጥቅም ስለሚስገበገብ ሁሉን ለእኔ በሚል ስስት ሕጎችን እያዘወተረ ከመጣስ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ይሁንና በጎ የሚሠራው ለጋሱና ሩህሩሁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰነፍና ንፉጉም ቢሆኑ ኖረው ኖረው ሁሉም ከዚህ ዓለም እኩል ማለፋቸው አይቀርም፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው ታዲ አብዛኛው የሰው ልጅ የሚሞትበትን ዕለት ማወቅ ስለማይቻለው ብቻ ሁሉን ለእኔ እንዳለ ፣ እንደተስገበገበና ጨርሶ በቃን ማለትን ሳያውቅ እንዲያውም ሌላው ቀርቶ ያፈራውን ንብረትና ገንዘብ እንኳን ተጠቅሞበት ሳይጨርስ ሌላ ለመጨመር እንዲሁ ቀንና ሌሊት እንደዋተተና እንደማሰነ ሁሉንም ጥሎ የሚያልፍ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲያው የሰው አኗኗር እንዲህ ከሆነ ዘንዳ ባለውና መሆን በሚገባው መሐከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ መሞላት አልያም መጥበብ የሚችል ቢሆን እኛ ሰዎች ይበልጥ ተጠቃሚና ተረጂ እንሆናለን፡፡
