ዳራዊ መረጃ
ዘመናችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ማኅበራዊ ተሳትፏችንን በብዙ መልኩ የቀየዱበት ነው፡፡ መካኒካዊ፣ ኤሌክትሪካዊ፣ ኢንዱስትሪያዊ፣ የሕክምና እና የሥነ ተግባቦት አጽቆች የሰው ልጅን ሕይወት በማቅለል ረገድ ተስተካካይ አይገኝላቸውም፡፡ ዓለም በአንድ ድምጽ ተገዢ የኾነላቸው እነኚህ የቴክኖሎጂ በረከቶች ቀስ በቀስ ነባርና አዳዲስ አሠራሮችን በራሳቸው ንጣፍ (Platform) ሥር እስከመተካት ደርሰዋል፡፡ በተለይ “ኢንተርኔት” የተባለው መረብ አብዛኛውን የዓለማችን ሕብረተሰብ ካጠመደ በኋላ ለበርካታ በጎና በጎ ያልኾኑ ተጽዕኖዎች ምክንያት ሲኾን መታዘብ ተችሏል፡፡ የሰው ልጅ የአዕምሮ ልቀትና የፈጠራ ከፍታ ግዙፍ ማሳያ እንደኾነ የሚነገርለት የአይሲቲ ዘርፍም፣ ከጠፈር ሳተላይት እስከ ምድር ማብለያ ለአያሌ ግኝቶች መሠረት መኾኑ ቴክኖሎጂ በሥነ ፍጥረት ሀቲት ውስጥ አዳዲስ ባለሚናነትን እንዲላበስ አድርጎታል፡፡
ኢትዮጵያም ከጊዜ ወደጊዜ የዚህ ሹረት አንድ አካል ወደመኾን መጥታለች፡፡ የኢንተርኔት ተደራሽነቷን ከማስፋቷ ጎን ለጎን ሳተላይቶችን ወደ ሕዋ እስከማምጠቅ ሙከራ ማድረጓ ወደንፍቀ ክበቡ ለመግባት በእጅጉ እየተንደረደረች ለመኾኗ አብነት ነው፡፡ ዳሩ ግን ሀገሪቱ ከምትገኝበት ቀጠና እና ማኅበረሰባዊ ንቃት አንጻር ሥነ ተግባቦት (Communication) ላይ የተቸከለው ቴክኖሎጂን የመጠቀም አዲስ ልማድ የሚያስደንቅ ውጤት አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ቴክኖሎጂያችን ከሥነ ተግባቦት ግኝት ተሻግሮ መካኒካዊ፣ ኤሌክትሪካዊ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማገዝ በሚረዳው የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ያለው ሚና እስከዚህም መኾን “ከሥጋው ይቅርብኝ ከመረቁ አርጉልኝ” ኾኗል ቢባል አያስተዛዝብም፡፡ ይኽ ቅደም ተከተሉን የሳተ አካሄድ ዜጎች ለነገሮች ያላቸውን መድሎት በእጅጉ አንሻፎታል፡፡ በዚህም ሳቢያ በሀገራችን ቴክኖሎጂ ያጎረፈው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተናጋሪን እንጂ ተግባሪን መፍጠር አልቻለም ፤ አውሪን እንጂ ሰሪን የሚያበረታታ ኾኖ አልተገኘም፡፡
ማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ምንድነው?
ማኅበራዊ መገናኛ/ሚዲያ ማለት ማናቸውም እርስ በርስ የሚያሳትፍ ድረ-ገጽ ላይ የተመሠረተ ተንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂ ማለት ነው። የጋራ ማኅበራዊ መገናኛ አውታር/ሚዲያ መድረኮች በርካታ ሲኾኑ ከእነዚህ መካከል በስፋት የሚታወቁት የሚከተሉት ናቸው፡፡
- Blogs (WordPress, Blogger, Tumblr, etc.)
- የማኅበራዊ አውታረ-መረብ ገፆች ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ሊንክደን፣ ወ.ዘ.ተ (Facebook, Twitter, LinkedIn, etc.)
- ፎቶ፣ የተቀረጸ ድምፅ እና ቪዲዮ መላላኪያ ገፆች ዩቲዩብ፣ ቪሚኦ፣ ፍሊከር፣ እንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ሳውንድክላውድ፣ ወ.ዘ.ተ (YouTube, Vimeo, Flickr, Instagram, Snapchat, SoundCloud, etc.)
- ማኅበራዊ ቡክማርኪንግ ገፆች ፒንተረስት፣ ረዲት፣ ወ.ዘ.ተ (Pinterest, Reddit, etc.)
- እንደ Wikis አመቺ፣ በግልጽ አርትዕ ሊደረግ የሚችል ይዘት፣ እንደ Wikipedia ዓይነት (collaborative, openly editable content, such as Wikipedia)
ሌሎች የተለመዱ የኤሌክትሮኒክ መገናኛ መሣሪያዎች የሚያካትቱት ደግሞ፦ እንደ ኦንላይን መድረኮች፣ የመልዕክት አፕስ (መተግበሪያ)፣ እንዲሁም የቴክስት መልክቶች ናቸው። እነዚህ መገልገያዎች የማኅበራዊ ሚዲያ/መገናኛ አካል ባይኾኑም በእነርሱም ላይ ተመሣሳይ ሕግ ተግባራዊ እንደሚደረግ መገንዘብ አስፈላጊ ነው።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፏችን
በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያን አሁን በምናየው መልኩ ለአንድ ዓላማ በስፋት የመጠቀም ምክንያቱ አንድና አንድ ነው ቢባል ማጋነን አይኾንም፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሲታፈን ማናቸውንም አማራጮች ለዛ ዓላማ መጠቀም አይቀሬ ጉዳይ ይኾናል፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ለንባብ ትበቃ የነበረችው አዲስ ጉዳይ መጽሔት፣ በወቅቱ በመንግሥት በኩል አለቅጥ ታፍኖ የነበረው ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ማኅበራዊው ሚዲያ ያለገደብ መቸሩን ተከትሎ ወደፊት ስለሚያስከትለው ተላውጦ ትንቢት የሚመስል የፊቸር መጣጥፍ አስነብባ ነበር፡፡ መጽሔቷ በአጭር ዓረፍተ ነገር የገለጸችው ሀቅ “መጪው ጊዜ ምርጫ መጣ ፕሬስ ውጣ” የሚለው ብኂል መገራት ወደማይችልበት ደረጃ እንደሚደርስ ነበር፡፡ የኾነውም በትክክል ይኸው ነበር፡፡ ፌስቡክን ማዕከል ባደረገው የትግል መረብ በሥልጣን የነበረውን አገዛዝ የሚይዘው የሚጨብጠው ማሳጣት ተችሏል፡፡ አዳዲስ አንቂዎችና አታጋዮች እንዲፈጠሩም ምክንያት ኾኗል፡፡
የኢትዮጵያውያን (ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ) የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ግን በአዳዲስ ተላውጦዎች እየታጀበ ለመምጣት ብዙ አልፈጀበትም፡፡ ከወግ፣ ከሥርዓት፣ ከዕምነትና ከልማድ ያፈነገጡ መልዕክቶች በመብት እና ነጻነት ሥም ሲዥጎደጎዱ መቆየታቸው በገቢር አያሌዎችን በጭካኔ ለመግደልና ለማፈናቀል አግዟል፡፡ በዚህም ሳቢያ ለበርካታ ጊዜያት የኢንተርኔት መዘጋቶች ሊያጋጥሙ ችለዋል፡፡ ኾኖም ክስተቶቹ ብዙም አስተማሪ ሊኾኑ አልቻሉም፡፡ የየማኅበራዊ ትስስር ገጾቹ ባለቤቶች የጥላቻ ንግግርን አስመልክተው እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ የሚመሩበት ደንብ እና ሕግ የሌላቸው መኾን ለማንበብ የሚዘገንኑ፣ ለመስማት የሚሸክኩ፣ ለመመልከት የሚያስፈሩ ሃሳቦች ያለገደብ በተደጋጋሚ እንዲሰራጩ ምክንያት ኾኖ ቆይቷል፡፡
በጥቅሉ ስንመለከተው የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ኢኮኖሚያዊ አማራጭን ለመፍጠር፣ የቢዝነስ ዕድሎችን ለመክፈት እንዲሁም ጤናማ ሕብረተሰባዊ ግንኙነቶችን ለመፍጠርና ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ የዋሉበት አጋጣሚ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሳሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ላይ በመጠኑም ቢኾን ቴክኖሎጂውን እንዳደጉት ሀገሮች ሕይወትን የተሻለ ለማድረግ እየተጠቀሙበት የመጡ ተቋማትንና ግለሰቦችን ማየት እየተለመደ ቢኾንም አመርቂ ነው ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡
የበይነ መረብ ግንባር
በዓለማችን እየገነገነ የመጣው የሉላዊነት (Globalization) ሃሳብ ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት የመቀየር ውጥኑ እየተሳካ ይመስላል፡፡ በተለይ ዜጎች የሕይወትና የኑሮ እንቅስቃያቸውን በበይነ መረብ ሥር እያደረጉ መምጣታቸው ትልቅ ማሳያ ኾኖ ሊታይ ይችላል፡፡ እዚህ ጋር ስውር ባይኾንም በወጉ ልብ ያልተባለ አንድ ነገር መኖሩ ግን ሀቅ ነው፡፡ ይኽውም በሥመ ሉላዊነት እየተደረገ ያለው መሰባሰብ ማንን በማን ላይ ጥገኛ አድርጓል የሚለው ጥያቄ ጥልቅ ትኳሬን ይሻል፡፡ ይኽን ጥያቄ ስናነሳ ያለጥርጥር የምናገኘው መልስ አንድና አንድ ነው፡፡ በተለይ የሦስተኛው ዓለም ሀገራትን እነኚህ የበይነ መረብ ንጣፎች የምዕራቡ ዓለም ደባል አድርገዋቸዋል ቢባል አንዳችም ስህተት የለውም፡፡ ከሃሳቦቹ ባለቤቶች ጀምሮ ፍቃድና ቁጥጥሩ በአንድም ኾነ በተዘዋዋሪ መንገድ በእነኚህ ልጨኛ (ሊበራል) ሀገሮች ሥር መኾን ለብዙ ዳፋ አጋልጧል፡፡ መዘዙ በቶሎ እንደማይለቅም በተግባር ታይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ማኅበረ ፖለቲካዋን መረጋጋት በመንሳት ረገድ ይኽ ቴክኖሎጂ የማይናቅ ሚና እንደነበረው ክፍ ብለን አትተናል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ኹኔታም ኾነ በመጪው ጊዜያት ግን ኹናቴን በመጠቀም ጥበብ (Art of possibility) አንዳች ስልት ካልቀየሰች ነገሮች ይበልጥ ሊወሳሰቡ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡ በተለይ ከሳምንታት በፊት በ geopolitics.com ላይ ይፋ በኾነው የባስማ (C2FC) ሕቡዕ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ፍርሰት ጀርባ እጃቸውን የዘረጉ ምዕራባውያን ሀገራትና ቡድኖች እነኚህን ማኅበራዊ የትስስር ገጾች በመጠቀም ረገድ የሚሰሩት ሸፍጥ አስፈሪና አስደንጋጭ መኾን ለመፍትሔው ካሁኑ የሚያባጅ ነው፡፡
ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በግልጽ መረዳት እንደሚችለው ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የውክልና ጦርነት አንዱ ዐውደ ግንባር እነኚህ የበይነ መረብ ንጣፎች እንደኾኑ ነው፡፡ በተለይም ፌስቡክንና ቲውተርን ማዕከል ያደረጉት ግንባሮች በበዙ መልኩ ኢትዮጵያ ነጥብ እንድትጥል ሲሰራባቸው ቆይቷል፡፡ ከታሪካዊና ነባራዊ ጠላቶቻችን ጋር ያበሩ የሀገር ልጆችን በመጠቀም የሀሰተኛ መረጃዎችን በእነኚህ መድረኮች በስፋት በማስተጋባት ዓለም የመሬቱን ሳይኾን የመረቡን “እውነት” ብሎ በመቀበል ለመግለጫና ለውሳኔ እንዲሽቀዳደም ያልተሰራ ሥራ የለም፡፡ ከፍ ባለው አንቀጽ የጠቀስነው C2FC የተባለው ስውር ቡድን ስለኢትዮጵያና ስለ ሀቋ የሚሟገቱ ፌስቡከሮችን ከማገድና አካውንታቸውን ከመጥለፍ አንስቶ፣ በአንዳችም ኹኔታ ለተዓማኒነት ዋቢ የማይኾኑ ግለሰቦችን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎች ዘንድ በምንጭነት እና በተንታኝነት እንዲቀርቡ እስከመጠቆም ደረስ የበይነ መረብ ቴክኖሎጂው ኢትዮጵያ በሰፊ ልዩነት የምትሸነፍበት ዐውደ ግንባር እንዲኾን ሳያሰልስ ሰርቷል፡፡
ይኽም ኾኖ በተገኘው ዕድልና አማራጭ የሀገራቸውን የማይነጥፍ ሀቅ ዓለም ጆሮ እንዲሰጠው ያለመታከት የሚተጉ ዜጎች መኖራቸው አልቀረም፡፡ በተለይ ከወራት በፊት ከሀገር ውጪ የሚገኙ በርካታ የህወሓት ደጋፊዎች በርካታ የቲውተር አካውንቶችን በመክፈት በኢትዮጵያ እየኾነ ስላለው፣ ዓለም ተቃራኒውን እንዲረዳ የሄዱበት የዘመቻ ርቀት ነገሩን ኹሉ “በጠመንጃ ያገኘኸውን በወሬ ትፈታለህ” (Victory at gunpoint is defeated by propaganda) የሚለውን ሃሳብ ሥጋ እንዲለብስ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በነቃው የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊ ዘንድ ዓለም ወድዶ ሳይኾን ተገድዶ የኢትዮጵያን እውነት እንዲያደምጥ ተከታታይ የቲዊተር ዘመቻዎችን ማድረግ አስገዳጅ ተግባር ወደመኾን መጥቷል፡፡ ቴክኖሎጂው በእነሱ አዛዥ ናዛዥነት የተቀየደ መኾን ዘላቂ መፍትሔ የሚያሻው መኾኑ እንደተጠበቀ ኾኖ ኢትዮጵያውያኑ ምን ያህል የዓለምን የሀሰት ክንብንብ ለመግለጥ እንደጣሩ የዚህ ሳምንት ተሳትፏቸውን በዋቢነት በማንሳት ብቻ እንመልከት፡፡
የቲዊተር ተሳትፎዎች
ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ ለኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ብዙም ተወዳጅነት በሌለው፣ ዓለም ግን በስፋት በሚገለገልበት የቲዊተር ዐውድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ድምጽ ለመኾን ተከታታይ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡ በውጤቱም በሀገራችን በዕርዳታ ስም ሽብርተኛውን ድርጅት የሚደግፉ ተቋማትና ግለሰቦችን የሚቃወሙ የትዊተር ዘመቻዎች ተደርገው አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮችና ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተዛባ አቋም እንዲፈትሹ እያስገደዳቸው መሆኑ ተገለጹዋል።
በዓባይ ወንዝና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛ እና የትዊተር ዘመቻው ተሳታፊ የኾነው እስሌማን አባይ ሰሞኑን ለአንድ ጋዜጣ በሰጠው ቃል፣ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ወዳጆች በእርዳታ ሰበብ የአሸባሪውን ህወሓት ወንጀል ለመደገፍ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ተቋማት ድርጊት በመቃወም የትዊተር ዘመቻዎች ማካሄዳቸው ከፍተኛ ተፅእኖ በመፍጠርና የኢትዮጵያን ድምፅ ለዓለም በማሰማት ዓለምአቀፍ ተደማጭነት የማግኘት አቅም እየተፈጠረ መምጣቱን አመላክቷል፡፡ ከቀናት በፊት ‹‹@DrTedrosResign›› በሚለው መልዕክት በአንድ ምሽት ዘመቻ ብቻ ከ144 ሺህ በላይ ትዊት ተደርጓል፡፡ ‹‹TplfTerroristGroup›› የሚልም በሳምንቱ ከ375 ሺህ በላይ ትዊት መደረጉን አስታውቋል። በዘመቻውም 3ነ ጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ተደራሽ መሆን መቻሉን ጠቁሟል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት እየጨመረ መምጣቱን ያመላከተው እስሌማን፣ ከቀናት በፊት “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አይወግንም። በአራቱ መርሆቻችን ሰብዓዊነት፣ ገለልተኝነት፣ አለማዳላትና ራስን የቻለ በሆነ መንገድ ሰብዓዊ ተግባር እየሰራን ነው፣ በዚህ መንገድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያለምንም አድሎ የምናደርገውን እርዳታ የምንቀጥል ይሆናል ሲል ያወጣው መግለጫ የዚሁ እውነታ አንዱ ማሳያ ነው›› ብሏል፡፡
ባለፉት ቀናት የተደረጉት የትዊተር ዘመቻዎች ‹‹StopWeaponizingAid›› እና ሌሎች ዋነኛ አጀንዳዎች የተቀረፀለት፣ በቀጥታ የሳማንታ ፓወርን ቢሮን የሚመለከትና ከ631 ሚሊዮን በላይ ተደራሽ ያገኘው እንደነበር ያስታወሰው ጋዜጠኛ እስሌማን፣ በቀጣዩ ቀን ሳማንታ ፓወር ‹‹የህወሓት ትንኮሳ ኢትዮጵያን ከመጉዳት ያለፈ ትርፍ አያመጣም›› የሚል መልዕክት ማጋራታችንም ዘመቻው ተፅእኖ እያመጣ ስለመምጣቱ ሌላው ማሳያ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ‹‹ጥንቃቄው፣ ጥርጣሬው የዲፕሎማሲ ብልሃትና ትግሉ መቀጠል እንዳለበት ሳንዘነጋ የሴትዮዋ የአቋም ለውጥ በጦር ሜዳውና በዲጂታሉ ፍልሚያዎቹ የተገኙ ድሎችን ተከትሎ የተፈጠረ ስለመሆኑ አጠራጣሪ አይሆንም›› ብሏል፡፡ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተዛባ አቋም እንዲፈትሹና እንዲያስተካክሉ የሚጠይቀው የትዊተር ዘመቻው ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጿል፡፡
አዲስ ንጣፍ (Platform) የመፍጠር አማራጮች
ከፍ ብለን ለመመልከት እንደሞከርነው ቴክኖሎጂውና የቴክኖሎጂው ባለቤቶች የአንድ አስተሳሰብ ተጋሪዎች መኾን፣ በጎውን አስበው ተጠቃሚ ለኾኑት የአፍሪካ ሀገራት ሌላ የማንበርከኪያ (ቅኝ የመግዣ) መሣሪያ ኾኖ መጥቷል፡፡ የቴክኖሎጂዎቹን ውጥኖች ገና ከመነሻው የተረዱት አንዳንድ የምሥራቅ እና መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ግን ለዜጎቻቸው አማራጭ መንገድ በመፈለግ እንዲህ ካለው ተጽእኖ መዳን ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ አዲስ መንገድ መፈለግ ይኖርባታል የሚለውም ቀላል የማይባሉ ሰዎች አስተያየት ወደመኾን መጥቷል፡፡ ከቀናት በፊት ታዲያ በኢትዮጵያ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) በኩል የተሰማው ዜና ለዚህ ፍላጎት ቅሩብ ምላሽን የያዘ ነበር፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ፌስቡክንና ትዊተርን በሀገራዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የመተካት እቅድ እንዳላት አስታወቀዋል፡፡
አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ እንደኾኑ በማስታወስም “ኢትዮጵያዊ የሆኑ እና እውነትን የያዙ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰራጩ እና ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ መልእክቶች ካሉ ፌስቡክ በአስቸኳይ እንዲጠፉ እያደረገ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ እውነታና ይዘት ያላቸው፣ ለሀገር ግንባታ የሚውል፣ አንድነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን የሚሰብኩ ይዘቶችን የሚያሰራጩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ገጾች እየተዘጉ መሆናቸውንም በመጥቀስ ፌስቡክ ከዚህ ቀደም ‘ከኢንሳ ጋር ይሰራሉ’ እና ‘የመንግሥት ደጋፊ ናቸው’ በሚል የተለያዩ ገጾችን ዘግቻለሁ ማለቱን አስታውሰዋል፡፡ “ገጾቹ የምንም ይሁኑ የማን ትክክለኛ መረጃ እስከያዙ ድረስ መዘጋታቸው ተገቢ እና ፍትሃዊ አይደለም” በማለትም አሁን ላይ ተቋማቱ እየወሰዱት ያለው ተግባር “የዘመቻ መልክ ያለው ነው” ብለዋል።
በትክክል እንደሚታወቀውም አፍራሽ ዓላማ ያነገቡ ጽሑፎችና “መረጃዎች” ያለማንም ከልካይ ምንም ማስጠንቀቂያ እንደፈለጉ ሲያሰራጩ የቴክኖሎጂዎቹ ባለቤቶች ደስተኞች ይመስላሉ። ዴሞክራሲን አስፍነናል፤ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ እኛ ነን በሚሉ ሀገራት የለሙ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ሰዎች ሀሳባቸውን መግለጽ መብትን የሚከለክሉ ከሆነ ሌላ ችግር እንዳለ ማሳያ በመኾኑ፣ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከሁለቱ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለመስራት ሙከራ ማድረጉ የሚበረታታ ነው።
እንደ ዶ/ር ሹመቴ ዕምነት ታዲያ “የሚያዋጣን ነገር የራሳችን የሆነ ፌስቡክን እና ትዊተርን ሊተካ የሚችል እንዲሁም ቢያንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም የሚስያችል የማህበራዊ ትስስር ገጽ መፍጠር” በመኾኑ ይኽንን በተግባር ለማዋል እየተሰራ ነው። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የለሙ የተግባቦት (የኮሙዩኒኬሽን) ፕላትፎርሞች ወደ ሙከራ ለመግባት በመንደርደር ላይ መኾናቸውም ተጨማሪ ተስፋ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ለስብሰባ የሚሆኑ፣ የኮሙዩኒኬሽን እንዲሁም የመረጃ መለዋወጫ መተግበሪያዎች አሁን ላይ የለሙ እና በሙከራ ደረጃ እየተሰራባቸው እንደሚገኝ፣ አስፈላጊው መሠረት ልማት ተሟልቶላቸው በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚለቀቁም በዶ/ር ሹመቴ በኩል መገለጹ አስደሳች ነው፡፡
መደምደሚያ
ሀሳባችንን በምቋጭበት አንቀጽ ታዲያ አንድ ጉዳይ ላይ አጽንዖት ሰጥተን ለማለፍ እንገደዳለን፡፡ ይኸውም መንግሥት እነኚህን የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ሀገር ውስጥ በለሙ ሌሎች መተግበሪያዎች ሲተካ ወደተለመደው ሃሳብን የማፈን አካሄድ እንዳይመለስ ነው፡፡ አፍሪካውያን ሀገራትና መንግሥታት በዚህ ረገድ ዕምነት በስፋት የሚጣልባቸው አለመኾኑ ነገሩ የተስፋችንን ያህል በሥጋትም እንድንቀየድ ምክንያት ይኾነናል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከበይነ መረብ በላይ ናት!
