Home በዓላት የቡሄ ትውስታ ዳዊት ከበደ ወየሳ

የቡሄ ትውስታ ዳዊት ከበደ ወየሳ

የቡሄ ትውስታ ዳዊት ከበደ ወየሳ

የቡሄው ሚስጥር የተነገረን በኋላ ላይ ነው። በልጅነት ወቅት… ጅራፍ መስራት እና ማጮህ፤ ቡሄ መጨፈር እና ሙልሙል መሰብሰብ፤ ችቦ መስራት እና ማብራት… እነዚህ ሁሉ በነሃሴ ወር የምንተገብራቸው የልጅነት ስራዎች ናቸው። በኋላ ላይ “ጅራፉ የክርስቶስን ግርፋት፤ ችቦው የክርስቶስ ብርሃነ መለኮት መገለጥን ያሳያል።” እስከምንባል ድረስ፤ ቡሄን የኛ ሰፈር ልጆች የጀመሩት ይመስለኝ ሁሉ ነበር። እናም ለጅራፉም፣ ለችቦውም፣ ለሙልሙሉም፣ ሃይማኖታዊ ትንታኔ ሳይሰጥበት በፊት ነበር የምናውቀው። ከድፍረት አይቆጠርብኝ እንጂ፤ በስተበኋላ ላይ ሆያ ሆዬ ከኦርቶዶክስ እምነት ጋር መያያዙ አብረውን ይጨፍሩ የነበሩ የፕሮቴስታንት እና የ’እስልምና እምነት ተከታይ ጓደኞቼን፤ “እንደዛ ነበር እንዴ?” እንዲሉ ስለማልፈልግ… ከሃይማኖት ጋር መያያዙን ከሚደግፉት ውስጥ አይደለሁም። ቡሄ ለኔ… የልጆች ጨዋታ ነበር፤ አሁንም እንደዚያ ነው ብዬ ባስብ ነጻነት ይሰጠኛል። እውነትም ደሞ… በዚያን ጊዜ… አዲስ አበባ ተወልዶ፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያደገም ቢሆን፤ “ሆያ ሆዬን” በልጅነት ሲጨፍር፤ ጅራፍ ሲያጮህና ችቦ ሲያበራ ሃይማኖታዊ ትርጉሙን ተከትሎ፤ የጅራፍ ልጥ የጎነጎነ፤ የከሴ ችቦ የሰበሰበ ልጅ  አላውቅም። ስለዚህ ዛሬ ስለቡሄ ሳወጋቹህ በልጅነት ያሳለፍነውን የቡሄውን ባህላዊ ጨዋታ እንጂ፤ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ለማስተማር እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።

የቄራ ልጅ ነኝ፤ ለጨርቆስም እቀርባለሁ። በሁለቱ ሰፈሮች መካከል “ኬላ በር” የሚባል መንደር አለ። ድሮ የአዲስ አበባ ኬላ እዚያ ላይ ነበር። እኔ የዚያ ሰፈር ልጅ ነኝ። ድሮ ሰፈራችንን ደመቅ አድርጎ የሚያሳየው የቴሌ ፎቅ ገና አልተሰራም ነበር። ለምን ስራ እንደታጨ ባላውቅም ዙሪያውን በግማሽ ሜትር ግንብ ታጥሮ፤ ባለቤት የሌለው ሜዳ ሆኖ፤ በበጋ ኳስ የምንጫወትበት፤ ክረምት ሲመጣ ደሞ፤ ቡድን ሰርተን… ጭቃ እያድቦለቦልን የምንወራወርበት ስፍራ ነበር። ሆኖም የሃምሌ ዝናብ ወዲያው ወዲያው ስለሚመጣ፤ ነሃሴን መናፈቃችን አይቀርም።

ነሃሴ ደግሞ… የአህያ ሆድ የመሰለው ሰማይ ወገግ የሚልበት ወይም ነሃስ የሚመስልበት ወር ነው። በዚያ የክረምት ወር ከብቶች ወተት በብዙ የሚሰጡበት፤ እርጎ የሚጠጣበት፣ ቂቤ የሚነጠርበት ወር ነው። ቂቤው ደግሞ በወፊቾ ወይም በቱሻ ተጠቅልሎ፤ አናቱ በቃጫ ታስሮ ገበያ ላይ ይውልና፤ ወደያንዳንዳችን ቤት ይመጣል። ቅቤው በእንሰት ቅርፊት ወይም በወፊቾ ታስሮ ሲመጣ፤ በየቤቱ የልጆች ደስታ ይጨምራል። በቱሻ ወይም በኮባ ቅጠል የተጠቀለለ ቂቤ ለኛ ጥቅም የማይሰጥ፤ ጅራፍ የማይሰራበትና የሚበጣጠስ ነገር ስለሆነ፤ ውሸታም ሰው ካጋጠመን “ቱሻ” ማለት የተለመደ ሆነ።

አንዳንዴም ውሸታም የሆነ ልጅ ካጋጠመን…

“ቱሻ ገመዳ፣

ቢሞት አይጎዳ፤

ቢሰበር እዳ።” እያልን በቡሄ በሉ ምት እንዘፍንበታለን።

የቡሄ በሉ የግጥም ምት ከዘለሰኛ፣ ከመሰንጎ እና መዲና የተለየ ነው። በነገራችሁ ላይ፤ ቡሄ በሉ የግጥም አወራረድ በልጆች ዘንድ የሚዘወተር ተወዳጅ የግጥም ምት አይነት ቢሆንም፤ በአዲስ አበባ የቋንቋ እና ስነ ግጥም ዘርፍ ደግሞ፤ የ”ቡሄ በሉ” የግጥም ምት ራሱን የቻለ መደብ ተሰጥቶታል።

ሌላ ቀርቶ “ቡሄ ካለፈ፣ የለም ክረምት፤

ዶሮ ከጮኸ የለም ለሊት።” የሚለው ተረትና ምሳሌ ሳይቀር፤ ዘለሰኛ ሳይሆን የ”ቡሄ በሉ”ን ምት የተከተለ ነው። ቡሄ ከመምጣቱ በፊት…

“ቡሄ መጣ፣ (ሆ)

ያ መላጣ፤ (ሆ)

ቂቤ ቀቡት፣ (ሆ)

እንዳይነጣ።” (ሆ) እየተባለ የሚዘፈነው ዘፈን ጭምር ወደ ሆያሆዬ ዜማ ይወስደናል። እናም ሃምሌ አልፎ ነሃሴ ሲገባ፤ መሬቱ ጠፈፍ ይላል። በሃምሌ ወር የምናደርገው የጭቃ ጨዋታ ያበቃል። ቂቤ ታስሮ የሚመጣበትን ልጥ ወይም የ’እንሰት ወፊቾ አለቅልቀን፤ ጸሃይ ላይ እናሰጣዋለን። ልጡ ጠፈፍ ሲልልን እንደየችሎታችን እና እንደየቁመታችን መጠን ጅራፋችንን እንገምዳለን። ለምሳሌ ለ’ኔ እና ለወንድሞቼ፤ ለአጎቴ ልጆች ጭምር ጅራፍ የሚገምድልን አያታችን ነበር። አውታሩን አውራ ጣቱ ላይ ያስረውና አጠንክሮ ይገምደዋል። በመጨረሻ ጫፉ ላይ ቃጫ አስገብቶ ይጠልፈውና፤ ልጥ እና ቃጫ በአንድ ተገምደው “ጅራፍ” ይሆናሉ።

እንግዲህ ነሃሴ ሲገባ ጀምሮ… ክረምቱ ስለማይበረታ ገበያው እንደገና ነፍስ መዝራት ይጀምራል። ከገጠር ወደ ከተማ ቅቤና ማር በገፍ ይገባል። ማሩን ለመጪው አዲስ አመት ጠጅ ይጣልበታል፤ ለ’እንቁጣጣሽ ዶሮ ወጥ የሚሆን ቅቤ የሚነጠረውም በዚህ ወር ነው። በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን የኛ የህጻናቱ ልብ ያለው ቅቤ ተጠቅልሎ የሚመጣበትና ጅራፍ የምንሰራበት የልጥ ወፊቾ ላይ ነው።

እንዳሁኑ ከተማው በጫጫታ እና በመኪና ሁካታ ከመጨናነቁ በፊት፤ ያንዱ ሰፈር ልጅ ጅራፍ ሲጮህ እኛ ሰፈር ድረስ ይሰማል። እኛ የምናጮኸው ደግሞ ለሌላው ይሰማዋል። እናም ዝናብ መጥቶ ወደቤት እንስከምንገባ ድረስ፤ ጅራፋችንን እንደጥይት እያጮህን፤ የጅራፍ ፉክክር እናደርጋለን። በኋላ ላይ… “የጅራፍ ጩኸት እና የጥይት ድምጽ ተምታታብን” በሚሉ የደርግ አብዮት ጠባቂዎች ምክንያት ጅራፍን አብዝቶ ማጮህ እየተከለከለ መጣና… እዚያም እዚያም እንደካርቱሽ ወይም እንደፈንዲሻ “ጢሽ ጢሽ” የሚሉ ጅራፎች ይሰሩ ጀመር። አሁንማ ከናካቴውም ጠፍቷል መሰል።

ይልቅ አሁን ስለሌለው እና ብዙም ስለማያወራለት የቡሄ ዋዜማ “አሲዮ ቤሌማ” ዜማ ላውጋችሁ። ሆያ ሆዬ ከመባሉ ጥቂት ቀናት በፊት የሰፈር ልጆች፤ በቡድን በቡድን ሆነው የሚመራረጡበት አጋጣሚ የሚፈጠረው አሲዮ ቤሌማ ሲጨፈር ነው።

የሰፈር ልጅ ሰብሰብ ይሉና “ዋኔ ዋኔ ዋ!

“ዋኔ

ዋ” እያሉ ይንጫጫሉ። ከነሱ መሃል ግን አንዱ ጎበዝ ብድግ ይልና… “ዋኔ በል አንተ” ይላል።

“ዋ” ይላል ታዳሚው።

“ዋኔ በል… ዋኔ”

“ዋ” ይሄን ሲሉ ቀልባቸው ወዳንድ ይሰበሰብና … ዘለግ ባለ ዜማ፤ “ዋኔ ስትነሳ” ብሎ ይጀምራል። ዜማውም ለየት ያለ ነው።

“ዋኔ ስትነሳ…” ሲል ‘ሆውው’ ይላሉ ተቀባዮች። ዜማ አይጻፍም እንጂ “ሆ” አባባላቸው ዘለግ ብሎ “ሆ፟ውው” የሚል ድምጽ አለው።

“ዋኔ ስትነሳ”

“ሆ፟ውው”

“ዋንጫህን አንሳ”

“ሆ፟ውው”

“ዋኔ ስትቀመጥ”

“ሆ፟ውው”

“ዳቦህን ግመጥ”

“ሆ፟ውው” እያለ፤ አንድ ቦታ ቆመው የታዳሚውን ቀልብ ወደ አንድ ይሰበስባሉ። ሁሉም ወዳንድ ሃሳብ ገብቶ መቀበል ሲጀምር፤ ያኔ የዜማው አይነት ጭምር ይቀየራል፤ “አሲዮ አሲዮ ቤሌማ” ብሎ ይጀምራል ዋናው ዘፈን አውጪ። ከዚያ በኋላ ዜማ ድባቡ ይቀየራል። ሶምሶማ እየሮጡ “ሆ፟ሆው” እያሉ ይከተላሉ ተቀባዮች።

“አሲዮ አሲዮ ቤሌማ” …“ሆ፟ውው

“የቤሌማ ጥጃ፤ …“ሆ፟ውው

“አብረን እንጫጫ፤ …“ሆ፟ውው፤

“አሲዮ አሲዮ ቤሌማ”… “ሆ፟ውው

“ቤሌማ ማለቴ፤ …“ሆ፟ውው

“እኔስ ለብላቴ፤

“ሆ፟ውው።” እያሉ በሶምሶማ ወደሚቀጥለው ቤት ይሄዳሉ። ከአንዱ ቤት ሌላው ቤት ያለው ርቀት ቅርብ ከሆነ፤ “ሆያ ሆዬ” ይከተላል። ሆኖም ካንዱ ቤት ተነስተው ወደሌላው ለመሄድ መንገዱ ራቅ ካለ፤ ዱላቸውን ሽቅብ እያወዛወዙ “የወንዜው ሳቢሳ”ን ያዜማሉ። ይህን የሚያደርጉት ለመንገዱ ርቀት ብቻ ሳይሆን፤ ዜማው ወንዳወንድነትን የሚያላብስ በመሆኑ ነው። ለዚህ ብቻም ሳይሆን፤ ወደዚኛው መንደር ሲደርሱ የሚተናኮላቸው ካለ፤ ወዲህም ደሞ ወንዳ-ወንድነታቸውን ለማሳየት ዜማውን፤ በ”ወንዜው ሳቢሳ” ሊቀይሩት ይችላሉ።

”የወንዜው ሳቢሳ፣ ሊበላኝ ተነሳ፤

“የወንዜው! የወንዜው!

“የወንዜው አንበሳ፣ ሊበላኝ አገሳ፤

“የወንዜው! የወንዜው!

“የወንዜው ነብር፣ ሊበላኝ ነበር፤

“የወንዜው! የወንዜው!

“የወንዜው አሞራ፣ ብረር ከኛ ጋራ፤

“የወንዜው! የወንዜው!

በዚህ አይነት የማይደክም ነፍሳቸውን ከአሞራ ጋር እያበረሩ፤ በልጅነት እና በጉርምስና ድምጻቸው “ሆ” እያሉ፤ ከአንዱ ደጃፍ ይደርሳሉ። ይሄን ጊዜም የጨዋታው ዜማ ይቀየራል።

ዋናው የዘፈኑ አውጪ “መጣና መጣና፣ ደጅ ልንጠና፤” ሲል፤ እሱ ያለውን በመድገም…

“መጣና መጣና፣ ደጅ ልንጠና፤” ይላሉ።

“ክፈት በለው፣ በሩን የጌታዬን፤

“ክፈት በለው፣ በሩን የጌታዬን።”

“ክፈት በለው ተነሳ፣ ያንን አንበሳ፤

“ክፈት በለው ተነሳ፣ ያንን አንበሳ።”

“መጣና በዓመቱ፣ ኧረ እንደምን ሰነበቱ?

“መጣና በዓመቱ፣ ኧረ እንደምን ሰነበቱ!?”

ከተባለ በኋላ ሆያ ሆዬ ይጀመራል።

ሆያ ሆዬ፣ ሆ

ሆ የኔ ጌታ፣ ሆ

ጌታ ነው፣ ጌታ፣ ሆ

ጌታ ጥንበለል፤

ዝናቡ መጣ፣ ወዴት ልጠለል?

ከዚያ በኋላ ሆያ ሆዬው ሲቀጥል፣ አድማጩን ፈገግ ዘና የሚያደርግ ግጥም አስከትሎ ነው። ከድንክ አልጋ ላይ ተቀምጦ፤ ሙልሙል ሲበላ ከድንክ አልጋው ላይ የተገለበጠ መሆኑን፤ በራሱ ላይ በመቀለድ ወይም ዘና በማድረግ  ይጀምራል – ሆያ ሆዬን።

እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል፣

አጋፋሪ፣ ይደግሳል፤

ያቺን ድግስ፣ ውጬ ውጬ፤

ከድንክ አልጋ፣ ተቀምጬ፤

ያቺ ድንክ አልጋ፣ አመለኛ፤

 ያለ አንድ ሰው፣ የማታስተኛ።

ከዚያ ዜማው ወደመለማመጥ ይቀየርና…

መጣሁኝ በዝና፣

ተው ስጠኝ ምዘዝና

ሆያ ሆዬ ጉዴ

ብሯን ብሯን ይላል ሆዴ

ሆያ ሆዬ ጉዴ

ሙልሙል ነው ልማዴ።

…እያለ ይቀጥላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሌላኛው ጌታ የሰጠውን ሽልማት በማንሳት፤ ይሄኛውም ተመሳሳይ ወይም የበለጠ እንዲሰጠው በዘዴ ይጠይቃል።

የኔማ ጌታ፣ የሰጠኝ ሙክት፤

እግንባሩ ላይ፣ አለው ምልክት፤

መስከረም ጠባ፣ እሱን ሳነክት።

የኔማ ጌታ፣ የሰጠኝ ላም

አስር ዓመትዋ፣ ኖረች በዓለም።

የኔማ ጌታ፣ የሰጠኝ ካራ፤

እዚህ ብመዘው፣ ጎንደር አበራ።

ከዚያ ደግሞ የዚህኛውን ሰውዬ ስም ጠርቶ እንዲህ ያሞግሰዋል።

የኔማ ጌታ፣ የኔማ ንጉሥ፤

ሽጉጡን መዞ፣ ጥይት ቢተኩስ፤

ያነጣጠረው፣ የተኮሰበት፤

መሬት ቆፍሮ፣ ውሃ ሞላበት፤

እንኳን ሰውና፣ ወፍ አይደርስበት፤

የአሞራ ባልቴት፣ ውሃ ትቅዳበት።

ወንዱን ወይም አባወራውን በዚህ አይነት አሞግሰው ሲያበቁ እማወራዋን ደግሞ…. እንዲህ ይሏታል።

የኔማ እመቤት፣ መጣንልሽ

የቤት ባልትና፣ ልናይልሽ።

የኔማ እመቤት፣ የጋገረችው

የንብ እንጀራ፣ አስመሰለችው።

የኔማ እመቤት፣ ብትሰራ ዶሮ

ሽታው ይጣራል፣ ጓሮ ለጓሮ።

ወይ የኔ እመቤት፣ የፈተለችው

የሸረሪት ድር፣ አስመሰለችው

ሸማኔ ጠፍቶ፣ ማሪያም ሰራችው

ለዚያች ለማሪያም፣ እዘኑላት

ዓመት ከመንፈቅ፣ ወሰደባት።

የማነው እንዝርት፣ ካገልግሉ ላይ

የዚያች እመቤት፣ የቀጭን ፈታይ።

 ይሔ የማነው ቤት – የኮራ የደራ

 የማምዬ ነው ወይ የዛች የቀብራራ

የአባብዬ ነው ወይ የዚያ የቀበራራ

ልጆቹ እንዲህ እያሉ በማዜም እና በማሞገስ፤ ጨዋታቸውን ሲቀጥሉ፤ ሽልማቱ ከዘገየባቸው…

ተው ስጠኝና ልሂድልህ፣

እንዳሮጌ ጅብ አልጩህብህ፤

አሮጌስ ጅብ፣ ጮሆ ይሄዳል፤

እንደኔ ያለው፣ መች ይመለሳል።

ድንጋይ ቢቀበር፣ አይበሰብስም፤

አንዴ መጥተናል፣ አንመለስም።

…በማለት አዚመው አሁንም ሽልማቱ ከዘገየ እንዲህ ይላሉ – የቡሄ ልጆች።

ሆይሻ ለሚሻ፣ የሉም ወይ የኔ ጌታ፤

ሆይታ ለሚታ፣ ልምጣ ወይ ወደ ማታ? …በማለት ጨዋታውን አቋርጦ እስከመሄድ ይደርሳል። የ’እድል ነገር ሆኖ ባለቤቶቹ ካሉና ከተሸለሙ ደግሞ… እንዲህ በማለት ደስ በሚል ምረቃ ይለያያሉ።

ክበር በስንዴ

ክበር በጤፍ

ምቀኛህ ይርገፍ

እንደቆላ ወፍ

ይሄን ሁሉ የሚሉት ለየት ባለ ዜማና በጋራ ስለሆነ ደስ የሚል ስሜት ይሰጣል።

አውዳመት አመት፣ ድገምና… አመት ድገምና!

ያባብዬን ቤት፣ ድገምና.. አመት ድገምና!

ወርቅ አፍስስበት።

አውዳመት አመት፣ ድገምና… አመት ድገምና!

የመቤቴን ቤት፣ ድገምና.. አመት ድገምና!

ወርቅ አፍስስበት።

 ድገምና… አመት ድገምና! …እያሉ ምስጋና በጋራ ያቀርባሉ።

በመጨረሻም… ጨዋታው ሲጀምር በገለጽነው “የወንዜው ሳቢሳ” በሚለው ዜማ፤ እንዲህ በማለት ጨዋታው ይጠናቀቃል።

 ማር ይዘንባል ጠጅ…

 ከጌታዬ ደጅ… ያሆ ከጌታዬ ደጅ

ማር ይዘንባል ጠጅ

ከመቤቴ ደጅ… ያሆ ከመቤቴ ደጅ… ያሆ!

በማለት ይጀምሩና የመጨረሻውን ምርቃት እንዲህ ይላሉ።

በጌታዬ ቤት፣ በጉልላቱ፤

ወርቅ ይፍሰስበት፣ ባናት ባናቱ።

የኔማ ጌታ፣ ጌታ ነው ጌታ፣

ሲቀመጥ ሲያምር፣ ሲቆም ሲረታ።

ከዚያ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ…

አሆሆ በል እረኛ

በጊዜ እንተኛ። በማለት ጨዋታው ከፍጻሜ ይደርሳል።

እኛም…

 አሆ በል ተረኛ

በጊዜ እንተኛ። እንላለን። መልካም ቡሄ ይሁንልዎ።