የቦረና ሕዝብ የሰቆቃ ጩኸት!

Date:

ኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ ውድ ከኾነባቸው የአፍሪካ ሃገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምትመደብና ከዓለም 8ተኛ ደረጃ ላይ መኾኗ በቅርቡ ተሰምቷል፡፡ ከዚምባቡዌ ቀጥላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለባት ሃገር እንደሆነችም በጥናት ተረጋግጧል፡፡ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በዋጋ ግሸበት ምክንያቶችና መፍትሄ ላይ ያደረገውን ጥናት በስካይ ላይት ሆቴል ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደገለጸው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 49.1 በመቶ ነው የተባለ ሲኾን የምግብ የዋጋ ንረት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ እንደጥናቱ ምልከታ የዋጋ ግሽበቱ ከክልል ክልል የተለያየ ሲኾን በአማራና ደቡብ ክልል ያለው የዋጋ ግሽበት ከሃገራዊ ምጣኔው ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡ ገበሬው ከሚያመርተው ምርት ከራሱ ፍጆታ ተርፎት ለገበያ የሚያቀርበው በአማካይ ከ20 በመቶ እንደማይበልጥ ተጠቁሟል፡፡ ከሚመረተው በቆሎ 85 በመቶው ገበሬው ለዕለት ፍጆታው ያውለዋል የተባለም ሲኾን ከሚመረተው ጤፍ ደግሞ ለገበያ ቀርቦ ከተማው የሚሸምተው 30 በመቶውን ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ97 በመቶ በላይ የዘይት ፍላጎቷን ከውጭ ገዝታ እንደምታመጣም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይ በቅርቡ የዓለም ሕፃናት አድን ድርጅት (Save the Children) እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት ለርሃብ መከሰት ዋነኛው መንስኤ ነው። ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብ እጥረት እንዳገጠማቸው ያነሳው ድርጅቱ ለዚህም የተጋነነ የዋጋ ግሽበት፣ ጦርነቱ እና የሰላም እጦቱ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ እንደ መንስኤ አስቀምጧል። በርካታ ዜጎች ገቢያቸው አነስተኛ በመኾኑ የምግብ ፍጆታቸውን መግዛት እንዳልቻሉ ድርጅቱ በጥናቱ ገልጿል።

ከፍ ሲል ያለው ጥናት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እውነታ በዚህ መልኩ ሲያስቀምጠው መንግሥት ደግሞ ሀገሬው በከፍተኛ የኑሮ ውድነትና ችጋር እየታመሰ ያመረተውን ስንዴ ወደ ውጭ በመላክ ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ በቦረና ዞን ውስጥ ከ800ሺ በላይ ሰዎች እርዳታ ይፈልጋሉ፡፡ በዞኑ ድርቅ ያስከተለው ረሀብ የሰዎች ሕይወት ወደ መቅጠፍ ተሸጋግሯል። በቅርቡ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ ከድርቅ ጋር በተያያዘ ሕዝቡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረው ለአምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ ከብቶች ማለቃቸውን፤ ሕዝቡ ላለፉት ሦስት ዓመታት እህል አለማምረቱን ገልጸዋል። በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል አደጋ ሥጋት እና መከላከል (ቡሳ ጎኖፋ) ኃላፊ ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድር ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በተከሰተው ዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ ዘንድሮ በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል። በአሁናዊ መረጃዎች መሠረትም በድርቅ እና በተለያዩ ምክንያቶች 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች በክልሉ ለተረጅነት መጋለጣቸውንና ከእነዚህም 3 ሚሊዮን 355 ሺህ 804 በድርቅ ምክንያት ሲኾን 824 ሺህ 324ቱ በድህነት እና በሠላም ችግር ተረጅ እንደኾኑ ገልጸዋል። ድርቁ በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በተለይ በሁሉም ቦረና አከባቢዎች፣ ምስራቅ ጉጅ ቆላማ ስፍራዎች፣ ምስራቅ ባሌ ቆላማ አከባቢዎች፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ቆላማ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥሏልም ብለዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ በተለያየ ጊዜ ተገልጿል፡፡ ችግር ለመቅረፍ ከሁለት ወር በፊት በገንዘብ ሚኒስቴርና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ለቦረና ዘላቂ ውሃ ልማትና ለተሻሻለ ሕይወት መርሐ ግብር ትግበራ የሚውል የ14 ሚሊዮን ዶላር (756 ሚሊየን ብር) ዕርዳታ ስምምነት ተፈርሞ ነበር፡፡ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአካባቢ ልማት፣ ሥርዓተ ፆታን ያገናዘበ የተቀናጀ ዘላቂ የውሃ ልማት፣ የአካባቢና የግል ንጽህና አገልግሎትን ለማስፋፋትና በውሃ አጠር አከባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን በጤና፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በሥነ-ምግብ እና በምግብ ዋስትና የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ የሚውል ነውም ተብሎ ነበር። በወቅቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እንደተናገሩት የእርዳታ ገንዘቡ በቦረና ዞን በተከታታይ ድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ በማልማት በአርብቶ አደሩ ዘንድ ዘላቂ ልማት ለማምጣትና በተለያዩ ዘርፎች ኑሮን ለማሻሻል እንደሚውል አመልክተው ነበር። ኾኖም ግን እስካሁን ድረስ ይህ ጉዳይ ከምን እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የቦረና ሕዝብ አሁንም የጉድጓድ ውሃ የለውም፡፡ በደጉ ወቅት የሚታወቅባቸው የዳልጋ እስሳቱ በድርቁ ሳቢያ እንደቅጠል እየረገፉ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳን መንግሥት እና ለጋሽ ድርጅቶች ተቀናጅተው ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ሠርተናል ቢሉም ድርቁ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ተረጂ ያለው በቦረና ብቻ ሳይኾን እንደሀገር በሁሉም አካባቢ ቢኾንም መንግሥት ለዚህ አካባቢ አቅዶ ይዟቸው የነበሩ ተግባራትን ግን በአስቸኳይና በአፋጣኝ መፈጸም ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንጻር በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት በቆላማ አካባቢዎች ውሃ ማቆር፣ የጉድጓድ ውሃ ማዘጋጀት፣ የተገኘውን ውሃ በአግባቡ መጠቀም ላይ ትኩረት አድርጎ የተግባር ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የአንድ አካባቢ ሕዝብ በየዓመቱ ተመሳሳይ ችግር የሚያስተናግድበት አሠራርን መቅረፍ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በአካባቢው ከድርቅ ጋር በተያያዘ ምን ያሕል ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው ድርቅ እጅግ የከፋ ይመስላል፡፡ ባለፈው ዓመት የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር፤ ተከስቶ በነበረው ድርቅ በክልሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ እንስሳት መግደሉንና በዋጋ ደረጃ ደግሞ ከ26 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸውን እንስሳት እንዳሳጣ እንዲሁም ከ14 ሚሊዮን በላይ እንስሳትም በድርቁ ጉዳት የደረሰባቸው መኾኑን ጠቅሰው ነበር።

የዘንድሮው ደግሞ ከዚህ ሊልቅ ስለሚችል የክልሉ መንግሥትም ይሁን የፌደራል ሕዝባቸው እያለቀ ዕለታዊ ፕሮፓጋንዳዎች ከመሥራት በዘለል በተግባር ሊደርሱላቸው ይገባል፡፡ ለሚዲያ ድምቀት ሲባል ብቻ ይህን ያሕል እርዳታ ገባ፤ ይህን ያሕል ገንዘብ ተመደበ እያሉ ማስተጋባት የሕዝብን ሰቆቃና ሞት አያስቆመውም፡፡ ቦረና እየተራበ አርሲና ባሌ ያመረተውን ስንዴ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ተግባር ነው፡፡ የሀገሬውን ምርት ለሀገሬው በማድረግ የዜጎችን ሕይወት ማሻገር ቀዳሚው ተግባር ሊኾን ይገባል፡፡ ከጦርነትም በላይ ረሃብ ጊዜ አይሰጥምና አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ያሻል፡፡ ልክ የዛሬ ዓመት አካባቢ (ጥር 26/2014) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ በድርቅ የተጎዱ ማኅበረሰቦችን በጎበኙበት ወቅት “በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቸገሩ ማኅበረሰቦችን በመደገፍ የአየር ንብረት ለውጡን መፋለም አስፈላጊ ነው፤ የመካከለኛ ጊዜ የውኃ ልማት ፕሮጀክቶች ደግሞ ችግሮች ሳይከሠቱ መፍትሔ ለማበጀት ያስችላሉ።” ሲሉ ችግሩን በአፋጣኝ እንደሚያስቆሙት ተናግረው ነበር፡፡ ነገር ግን ቃላቸው ተግባራዊ ሳይኾን የቦረና ሕዝብ በድርቁ እንደተዋጠ እሮሮና ጩኸቱ በበርሃ እደሰጠመ ድፍን ዓመት ሞላው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እርሳቸው “ለህዝባችን የተናገርነውን በተግባር ፈጽመን ዛሬ የኢትዮጵያን የስንዴ ኤክስፖርት ዕውን አድርገናል። የኢትዮጵያ ህዝብ መገንዘብ ያለብት  እኛ የምናልም ያለምነውን የምንናገር የተናገርነውን ቀን ከሌት የምንሰራ የሰራነውን ደግሞ አጠናቀን የምናሳይ እንጂ እንዲሁ የምንቃዥ አይደለንም” ሲሉ በመደስኮር በአደባባይ በችጋር እያለቀ ያለውን የቦረና ሕዝብ ዳግም ክደውታል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...