የቱ አጀንዳ? ሕብረተሰብ የሚፈልገው ወይስ ሕብረተሰብ የሚለውጠው?

Date:

ሕብረተሰብ ውስጥ የሚንተከተክ አጀንዳ እና አገርን ሊለውጥ የሚችል አጀንዳ በአመዛኙ በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን በተከታታይ ያስተዳደሩ መሪዎች በአመዛኙ ለሥልጣናቸው ብቻ የሚያስቡ በመኾኑ “በሕብረተሰብ ውስጥ ቢስተናገድ ተቀባይነት ያስገኝልኛል፣ ሥልጣኔን ለማራዘም ይረዳኛል” ያሉትን አጀንዳ ይዘው ያራግባሉ እንጂ አገርን የሚለውጥ አጀንዳ ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ለዚህ ነው ሁሉም መሪዎቻችን ውጤት የራቃቸው፡፡ እነ ማኦ ሴቱንግ፣ እነ እስታሊን፣ እነ ጀነራል ፓርክ አገራቸውን በመሠረቱ ከድህነት አውጥተው ወደ ብልጽግና መውሰድ የቻሉት አገር የሚጠቅም ነገር ግን ሕብረተሰቡ ስላልገባው በፍጹም የማይፈልገውን አስተሳሰብ ተግባራዊ በማድረጋቸው ነው፡፡

አንድ አገሩን መለወጥ የሚፈልግ መሪ መጨነቅ ያለበት ትክክለኛውን ሳይንሳዊ የሕብረተሰብ ዕድገት ሊያመጣ የሚችልን አስተሳሰብ በግዴታም ጭምር በሕብረተሰብ ላይ ለመጫን መሥራትና አገርን ለማሣደግ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የተወሠነ የሕብረተሰብ ክፍሎችን “ሊያስቀይም ይችላል” በሚል ዕሳቤ ኋላ ቀር የኾነን አስተሳሰብ ይዞ በመጓዝ በተአምር ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ “Demagoguism” የሚባል ጽንሰ ሐሳብ አለ፡፡ ይህ አስተሳሰብ የሚገለፀውም የፖለቲካ መሪዎች “ይህንን አስተሳሰብ ባራግብ (ባራምድ) ብዙ ተከታይ ላገኝ እችላለሁ፤ ከዚያም ወደ ሥልጣን ለመምጣት ወይም የያዝኩትን ሥልጣን ለማቆየት ይረዳኛል” ብለው የሚያራምዱት አስተሳሰብ ነው፡፡

በሀገራችን በተከታታይ ወደ ሥልጣን የመጡ መሪዎች የዚህ ብልሹ አስተሳሰብ ሰለባዎች ናቸው፡፡ በዓለማችን በየትም አገር አዲስ አስተሳሰብ ይዞ የመጣ መሪ ወዲያውኑ በቂ ተከታይ አግኝቶ አያውቅም፡፡ ሕዝቦች ያ አዲስ አስተሳሰብ እስኪገባቸው ጊዜ ይወስዳል፡፡ በተወሰነ መልኩ አዲሱ አስተሳሰብ መደበኛ የኑሮ ሁኔታን ሊያዛባ ይችላል፡፡ የሽግግር ወቅት መኖሩ ወይም መፈጠሩ አይቀርም፡፡ አዲሱ አስተሳሰብ አድጎ ፍሬ ማፍራት እስኪጀምር ድረስ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ቻይና አዲስ አስተሳሰብ በየጊዜው እየቀያየረች አዲሱ ሐሳብ ፍሬ ማፍራት እስኪጀምር ድረስ በርካታ ዐሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የቻይና ማዕከላዊ መንግሥት ጠንካራ መንግሥት በመኾኑና አዲሱን አስተሣሠብ በተከታታይ የማስፈፀም ብቃት ያለው መንግሥት በመኾኑ ዛሬ ቻይና ከድሕነት ወጥታ ኃያል ሀገሮችን መቀላቀል ችላለች፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ከቻይና እጅግ በተሻለ ሁኔታ ላይ የነበረን ሲኾን አሁን ከበርካታ ዐሥርት ዓመታት በኋላ ቻይና እኛን አልፋ ኃያል መንግሥት ስትኾን እኛ ገና ስለዳቦና ዘይት በማውራት ላይ ነን፡፡ ይህ ክስተት በግልጹ የሚያሣየን ያለፉትን 70 ዓመታት አገራችንን ያስተዳደሩ መሪዎች ምንም ሥራ አለመሥራታችውን ነው፡፡ አንድን ሕብረተሰብ ኋላ ቀር ከኾነ አስተሳሰብ መንጭቆ ማውጣት እጅግ ፈታኝ ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር የተሳካላቸው መሪዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ አፍሪካን ቅኝ የገዙ አውሮፓውያን የአፍሪካን ሕዝቦች በባርነት ቀንበር ውስጥ አስገብተው ብዙ ሐብት ያፈሩ ቢኾንም የአፍሪካን ሕዝቦች በግዴታም ቢኾን የአውሮፓን ባሕል እንዲለምዱ በማድግ፣ ለሥልጣኔ የሚጠቅም እና የአፍሪካ ሕዝቦች በተመሣሣይ ቋንቋ መግባባት እንዲችሉ በማድረጋቸው ቅኝ የተገዙ የአፍሪካ ሕዝቦች ዛሬ ከኛ በተሻለ ሁኔታ በሰላም እየኖሩ ሙሉ አቅማቸውን ወደ ኢኮኖሚ እድገት እንዲያዞሩ እድል አግኝተዋል፡፡

ቅኝ መገዛታቸው በተወሰነ መልኩ ጠቅሟቸዋል፡፡ እኛ ደግሞ በተቃራኒው ለዘመናት ይዘን የቆየናቸው ባሕሎች፣ ሐይማኖታዊ አስተሣሠቦች በመላው ዓለም ተቀባይነት ያገኘውን የሥልጣኔ አስተሣሠብ እንዳንከተል እንቅፋት ከመኾንም በተጨማሪ ጠንካራ እና ለለውጥ ዝግጁ የኾነ መሪ ማግኘት ባለመቻላችን ይህ ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ እንኳን የበለፀገች አገርን ልናወርስ ይቅርና ተቀባይነት ያለው ሥርዓት መትከል እንዳንችል አድርጎናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አገር መምራት የሚገባው የሕብረተሰብ ክፍል አገር መምራት እንዲችል የተዘረጋ ሥርዓት ባለመኖሩ ይህንን የሚያውቁ የሥልጣን ጥመኞች ያለ ማንም ከልካይ ወደ ሥልጣን ይመጣሉ፡፡ ሐገር መምራት የሚገባው የተማረው ሕብረተሰብ በሽኩቻ እና በሸር የተሞላውን የሥልጣን ግብግብ ውስጥ ገብቶ ሥልጣን ለመያዝ ፍላጎቱም ችሎታውም ስለሌለው የኢትዮጵያ በትረ ሥልጣን አሁንም ወደፊትም ለሕገወጦች ሙሉ በሙሉ ክፍት የኾነ መድረክ ነው፡፡

ያ ማለት የኢትዮጵያ ችግርም ኋላ ቀርነትም ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ በቅርብ ጊዜ መሻሻል የሚያሳይበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ በጣም በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አንድን ሕብረተሰብ ከድሕነት እና ከኋላ ቀርነት ለማውጣት የሚያስችለው አስተሣሠብ አብዛኛውን ገዜ በሕብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ስለሌለው የሚጠቅመውን አስተሳሰብ ሕብረተሰብ ላይ ለመጫን የግድ ጠንካራ አመራር፣ ጠንካራ አደረጃጀት ያስፈልጋል፡፡ አሁን በዶክተር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት እንኳን ሕብረተሰብን የሚለውጥ ተግባር ሊፈጽም ይቅርና እራሱ ፓርቲው ሕልውናውን ማስቀጠል አቅቶት ለመውደቅ የሚንገዳገድ መንግሥት ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን ሲወድቅ ብቻውን ይወድቃል ወይስ ኢትዮጵያን ይዞ የሚለው ነው፡፡ ዜጎች ማድረግ የፈለጉትን ማንኛውም ዐይነት የልማት ሥራ እንዲሠሩ ትልቅ ግብዓት መሬት ነው፡፡

በአገራችን የገጠር መሬት መሸጥ የሚቻልበት ሥርዓት አለመዘርጋቱ ዜጎች እንደ ብቃታቸው እንደ ዝንባሊያቸው መሥራት የሚችሉበት ሥርዓት ተዘርግቶ አገር ማልማት የሚቻልበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ አንድ ሰአሊ የስዕል ችሎታውን ለማሣየት የግድ የተወጠረ ጨርቅ እና ቀለም ያስፈልገዋል፡፡ አንድ የዋና ችሎታ ያለው ሠው ችሎታውን ለማሣየት የግድ የመዋኛ ቦታ መኖር አለበት፡፡ አንድ የተፋጠነ የልማት ሥራ መሥራት የሚፈልግ ዜጋ የፈለገውን መሬት ገዝቶ ያሰበውን ልማት መሥራት ካልቻለ ወጣቶችም ሥራ አያገኙም መንግሥትም የግብር ገቢ አያገኝም፤ ዕድገትም አይኖርም፡፡

በዶክተር ዐቢይ አመራር በግልጽ መታረም ያልቻለው አስተሳሰብ የብሔር ጽንፈኝነት በተገቢው አቅም መዋጋት ሲገባ ይባስ ብለው “ሕብረብሔራዊ አንድነት” የሚል መፈክር የመንግሥት መፈክር በማድረግ የብሔር ጽንፈኝነት እየተጠናከረ መሄዱ ነው፡፡ የብሔር ጽንፈኝነት እያለ በተአምር ሐገራዊ አጀንዳ ማስተናገድ አይቻልም፡፡ ወይ በብሔርተኝነት ሳጥን ውስጥ መግባት ነው ወይ ደግሞ ብሔርተኝነትን በሕግ አግዶ ሐገራዊ አጀንዳን ብቻ ማራመድ ነው፡፡ የዶክተሩንም ፍጻሜ እያቃረበው ያለው አካሄድ አንዱና ዋነኛው ይህ አስተሳሰብ ነው፡፡ መቀራረብ ሳይቻል በጽንፎች መካከል ያለውን ርቀት ማጥበብ ሳይቻል ሐገራዊ አጀንዳን ማራመድ አይቻልም፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍም ሁሉም ነገር እጅግ ወደሚያስፈራ አቅጣጫ እየተጓዘ በመኾኑ ሕብረተሰቡ አሁን እየጠበቀ ያለው አንድ ኳርኳሪ ምክንያት እስኪፈጠር ብቻ ነው፡፡ በኢኮኖሚው ላይ የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በተለይ የዩክሬን እና የራሺያ ውጥረት የፈጠረው ተጽእኖ አገር ውስጥ ካለው የኢኮኖሚ ውድቀት ሠላም መደፍረስ በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ውጥረት፣ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው መናናቅና መናበብ አለመቻል፣ ሁሉም ነገር ተደማምሮ ሊያመጣ የሚችለው ውጤት አስፈሪ እየኾነ ነው፡፡ እኔ በእድሜዬ የኃይለሥላሴን አሣዛኝ አወዳደቅ አይቻለሁ፡፡ የኢህአዴግ አንድ ጥይት ሣይጮህበት ደርግ ከቤተመንግሥት ሲባረር ታዝቤያለሁ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከእነዚህ ስሕተቶች ሁሉ ባለመማር በተመሳሳይ መልኩ በአሣዛኝ መልኩ ለመውደቅ መዘጋጀታቸው በእጅጉ ያሣዝናል፡፡ አንደ መሪ የሀገሪቱን ዜጎች ሁሉንም ዐይነት መብቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ ካልቻለ የሚጠብቀው ውድቀት ብቻ ነው፡፡ ከካድሬዎች እና ከወታደሮች ጋር ሠርቶ ውጤት እንደሚያመጣ በእኛ ዕድሜ በተከታታይ አይተናል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከታሪክ ባለመማር ለተመሣሣይ ስሕተት እየሠሩ ወደ ውድቀት እያመሩ ነው፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...