የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በክልሉ ለሚገኙ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች የግብርና ብድር አቅርቦት ለማስጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
ስምምነቱ በጦርነት ክፉኛ የተጎዳውን የክልሉን ግብርና ለማነቃቃትና አርሶ አደሩን የፋይናንስ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተና ጀነራል ታደሰ ወረደ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ባንኩ ለአርሶ አደሩ ያዘጋጀው የብድር አቅርቦት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ከገበሬው የሚጠበቀው ምርታማነት ፍሬ እንዲያፈራ የፋይናንስ አቅርቦቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ መሆን አለበት” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰሜን ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል ተስፋሁነኝ በበኩላቸው፣ ባንኩ የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግና አርሶ አደሩ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የራሱን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩም አርሶ አደሮች የብድሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከባንኩ ጋር በቅርበት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
የባንኩ የመቐለ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ልሳነወርቅ፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የብድር አቅርቦቱ በተለይ በትንንሽ እርሻዎች ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ቀጥተኛ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ይህ ስምምነት በትግራይ ክልል የተጀመረውን የመልሶ ማቋቋም ጥረት የሚያግዝ ሲሆን፣ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል።
