ሐሙስ ነሐሴ 29 2017 ዓ.ም የሚከበረውን የመውሊድ በዓል አስመልክቶ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ አባልና የወጣቶችና ሴቶች ዘርፍ ተጠሪ ሼህ አብድልሃሚድ አህመድ፤ መውሊድ ሲከበር የአካባቢን ሰላም በማስጠበቅና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የታላቁ አንዋር መስጊድ ኢማም ሼህ ጠሃ መሐመድ ሃሩን በበኩላቸው፤ ” ነቢዩ መሐመድ ለዓለም ሰላምና ለሰው ልጆች እዝነት የተላኩና የሰሩ በመሆናቸው ሙስሊሙ ማህበረሰቡ አርዓያነታቸውን ሊከተል ይገባል” ብለዋል።
በመውሊድ በዓል አከባበር ወቅት የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱና በዓሉ የእስልምና አስተምህሮን ለእምነቱ ተከታዮች ለማስረፅ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
በዓሉ ነገ ሐሙስ በመላው ኢትዮጵያ የሚከበር ሲሆን፤ በአዲስ አበባም በታላቁ አንዋር መስጊድ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ተጠቁሟል፡፡
