ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ ጋር የተፈራረመችው የ30 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት በፓርላማ ጥያቄ አስነስቷል። የህዝብ ተዘካዮች ምክር ቤት፣ 5ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን በትናንትናው ዕለት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በዚህ ስብሰባው የጤና ተቋማትን አገልግሎት እና ተደራሽነትን ለማሻሻል ያግዛል ያለውን የብድር ስምምነት ለዝርዝር እይታ መርቷል፡፡
ብድሩ ከደቡብ ኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ የተገኘ እና መጠኑም 30 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የብድር ስምምነቱ በ40 ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዲኤታ መሠረት ኃይሌ ለአባላቱ አሰረድተዋል።
የብድር ስምምነቱን በተመለከተ የምክር ቤት አባል ጥያቄ ያነሱ ሲሆን “ የብድር ስምምነቱ ላይ የወለድ መጠኑ ዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ነው፤ ይህ ደግሞ ከተበደረው በላይ ነው፤ ማለትም ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር ይጠጋል ” የሚለው ይገኝበታል።
“ ብድሩ በሚመለስበት ጊዜ ከብድሩ ይልቅ ወለዱ ይበልጣል ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ” ብለዋል። የምክር ቤቱ አባል አያይዘውም “ የፕሮጀክቱ ግዢ የሚፈፀመው በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ባለስልጣን አማካይነት መሆኑ ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም ይህ ስራ በዋናነት የጤና ሚኒስቴርን የሚመለከት በመሆኑ አሳማኝ ምክንያት አለ ወይ? ” የሚሉት ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
ሌላኛው የምክር ቤት አባል ከአዳዲስ የጤና ተቋማት በተጨማሪ የቆዩ የጤና ተቋማት ላይም ትኩረት ያደረገ ስራ እንዲሠራ እና አካታች እንዲሆን በተጨማሪም ለበርካታ ጊዚያት ያገለለገሉ የጤና ተቋማት ላይ “ የመታከሚያ መሣሪያዎች እጥረት እና ብልሽት ይገጥማል፣ ይህንን በተመለከተ በክልሎች የህክምና መሣሪያዎች የጥገና ማዕከል መቋቋም አለበት ” ብለዋል።
ብድሩ የ15 ዓመታት የችሮታ ጊዜ እና በ40 ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እንደሆነ ተገልጿል ።
በዚሁ መሠረትም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ የጤና ስርዓትን የሚያጠናክር አዋጅ መሆኑን አምኖ ለዝርዝር እይታ ለፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቷል።
አዲስ_ማለዳ
