ይፋዊ የሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ብዛት የሚያመላክት ቁጥራዊ መረጃን አላወጣሁም ሲል የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ለኢትዮ ኤፍኤም አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎትን ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 109.4 ሚሊዮን ነው የሚል መረጃ ሲሰራጭ ጣቢያችን አስተውሏል፡፡
በመረጃው መሰረት በ2007 ዓ.ም በነበረው የህዝብ ቆጠራ የወንዶች ቁጥር ከሴቶች ቁጥር ሲነፃፀር የ700,000 ብልጫ የነበረ ሲሆን አሁን ልዩነቱ ከ250,000 በታች ነው የሚል መረጃም ተካቶበታል።
ኢትዮ ኤፍ ኤምም ይህንን አስመልክቶ መረጃው ምን ያህል እውነት ነው ሲል የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎትን ጠይቋል፡፡
በአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሳፊ ገመዳ “ኢትዮጵያ ህዝብ ቆጠራ ካካሄደች ወደ 20 ዓመት አልፏታል ፤ አሁን ላይ ምንም ይፋ የተደረገ መረጃ የለም” ብለዋል፡፡
‹‹አሁን ላይ የህዝብ ቁጥርን በተመለከተ ቁጥሮች የሚቀመጡት በግምት ‹‹ ፕሮጀክሽን › በሚባል አለም አቀፍ አሰራር ዘዴ ነው ፡፡ በዚህ አሰራርም በአመት ካለው ከከፍተኛው የህዝብ ሰፈራ ግመታ ዝቅተኛውን የህዝብ ሰፈራ ግመታ ወይም ሴናሪዮ የሚባለውን በማቀናነስ የሚሰራ አሰራር አለ ›› የሚሉት አቶ ሳፊ ‹‹ እሱን ስናቀናንስ የምናገኘው ቁጥር ተሰልቶ በግምት የሚቀመጥ ቁጥር ቢኖርም ይፋዊ ቁጥር ግን አላወጣም›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው በ1976 ዓ.ም. ነው።
ሁለተኛው ደግሞ በ1987 ዓ. ም. እንዲሁም ሦስተኛው ከ1999 ዓ. ም. እስከ 2000 ዓ. ም. ተካሂዷል።
ሦስተኛው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው በ1997 ዓ. ም. ሲሆን የተካሄደው ግን ሁለት ዓመት ዘግይቶ በ1999 ዓ.ም ነው።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስከአሁን የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ የተከናወነው ሦስት ጊዜ ነው። አራተኛው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ከ2010 ዓ. ም. እስከ 2013 ዓ. ም. ባሉት ዓመታት አራት ጊዜ የተራዘመ ሲሆን፣ በ2014 ዓ. ም. ለአምስተኛ ጊዜ ተራዝሟል።
