Home ቅኝት የኢትዮጵያ ዘጋቢዎች ስለ ዶቼቬለ 60ኛ ዓመት የሰጡት አስተያየት

የኢትዮጵያ ዘጋቢዎች ስለ ዶቼቬለ 60ኛ ዓመት የሰጡት አስተያየት

የኢትዮጵያ ዘጋቢዎች ስለ ዶቼቬለ 60ኛ ዓመት የሰጡት አስተያየት

ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል የሚዘግቡ ባልደረቦችን ስለ ዶቼቬለ 60ኛ ዓመት አስተያየታቸውንና የመልካም ምኞት መግለጫዎቻቸውን አስተላልፈዋል።

የ DW የአዲስ አበባ ዘጋቢ ሐና ደምሴ አዲስ አበባ ከመምጣቷ በፊት ከለንደን [እንግሊዝ] ትዘግብ ነበር። ሀን ባለፉት በርካታ ዓመታት ከጀርመን ድምጽ ራዲዮ ጋር በቆየቸባቸው ጊዜያት «በሙያ ብቻ ሳይሆን በሕይወትም የተማርኩበት፣ ራሴን ያሳደግሁበት ቤት ነው» ትላለች። ባልደረቦቿንም ፣ አድማጮቻችንንም በሙሉ ለ60ኛ ዓመት በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብላለች።


«ዶቼ ቬለ ራዲዮን ማድመጥ የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው። ከጣቢያው ጋር አብሬ ነው ያደግኹት ማለት እችላለሁ። ተማሪ ኾኜ በደብዳቤ እሳተፍ ነበር። ካደኩ በኋላም ቅዳሜ ቅዳሜ በተለይ ዘውዱ ታደሰ የሚያቀርበውን ዝግጅት (ፕሮግራም) በደንብ ነበር የምከታተለው። ግጥሞቹ በጣም ደስ ይሉ ነበር።» ያለው ደግሞ DW የባሕር ዳር ዘጋቢ ዓለምነው መኮንን ነው።  «ዛሬ ደግሞ የጣቢያው ባልደረባ ኾኜ እንደ ነጋሽ መሐመድ ከመሳሰሉ ነባርና ታዋቂ ጋዜጠኞች ጋር የመሥራት ዕድሉን አግኝቻለሁ። በጣም ደስተኛ ነኝ። 60ኛ ዓመቱን ሲያከብር [ጣቢያው] ደግሞ ተካፋይ በመኾኔ በእጅጉ ተደስቻለሁ” ብሏል አለምነው። 


የ DW የመቀሌ ዘጋቢ ሚሊዮን ኃይለሥላሴ”ለረጅም ዘመን እንደቆየ፣ በሀገራዊ ቋንቋም እንዲሁ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ አንድ ተቋም እንዲሁም በዚህ ተቋም ደግሞ እኔም አካል ኾኜ መሥራቴ በጣም ትልቅ ክብር፣ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል። በሀገሪቱ የሚዲያ ዕድገት፣ ታሪክም በጣም ትልቅ ቦታ ያለው ተቋም ነው”። ያለው ሲል፤


ሸዋንግዛው ወጋየሁ – የDW የሀዋሳ ዘጋቢ “ዶቼ ቬለ በልጅነት ወላጆቼ ሲከፍቱ እየሰማኹ ያደኩት የሬድዮ ጣቢያ ነው። ዛሬ ላይ የዚህ ተወዳጅ እና አንጋፋ ተቋም ሠራተኛ በመኾኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት ጀርመንም ኾነ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩ የፖለቲካ ለውጦች ሳይስተጓጎል ያለማቋረጥ ከግማሽ ምዕተ ዐመት በላይ ማገልገል ቀላል አይደለም”።


ነጋሳ ደሳለኝ – የDW የአሶሳ ዘጋቢ “ዶቼ ቬለ እንግዲህ ብዙዎችን – እኔን ጨምሮ ጋዜጠኝነትን እንድንወድ ያደረገን የሚዲያ ተቋም ነው። ሳዳምጠው ያደግኩት። አሁን ደግሞ የተቋሙ አንድ አባል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። ዶቼ ቬለ የአማርኛው አገልግሎት ሥርጭት ከጀመረ 60ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው። የዚህ ታሪካዊ ሂደት አንድ አካል በመኾኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሁላችንም እንኳን አደረሰን ለማለት እወዳለሁ”።


ስዩም ጌቱ – የDW የአዲስ አበባ ዘጋቢ “ያው ዶቼ ቬለን መቀላቀል እንዲህያው በዋዛ የሚታይ ዕድል አይደለም። በዩኒቨርሲቲ የተማርነውን – ትክክለኛ የሆነውን ገለልተኝነትን፣ ሚዛናዊነትን የሚጠይቀውን ሙያውን በትክክል የምንተገብርበት አድርጌ ነው የማየው። በተቻለኝ መጠን ሚዛናዊ፣ ትክክለኛ እና የተጣሩ መረጃዎችን ብቻ ለዶቼ ቬለ አድማጮች ለማድረስ ሁልጊዜም ጥረት አደርጋለሁ። እናም ይህን ሞያዊ አገልግሎት ለድፍን 60 ዓመታት ከሰጠው ተቋም ጋር መሥራት ኩራትም፣ ደስታም እንዲሰማህ ያደርጋል”። ስዩም ጌቱ – የDW የአዲስ አበባ ዘጋቢ


መሳይ ተክሉ – የDW የድሬደዋ ዘጋቢ 
“ተቋማችን 60ኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኝበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። እንግዲህ ስድሳ ዓመት ትልቅ ዕድሜ ነው። ይህን ስናስብ ደግሞ በቅብብሎሽ ይህንን ትልቅ ተቋም እዚህ ለማድረስ የተከፈለው ዋጋም እንደዚሁ ትልቅ መሆኑን ያመለክታል። በዚህ አጋጣሚ በዚህ ቅብብሎሽ ውስጥ ይህንን ትልቅ ተቋም እዚህ ላደረሱ የሙያ አጋሮቻችን ያለኝን አክብሮት መግለጽ እፈልጋለሁ”።


ኢሳይያስ ገላው – የDW የደሴ ዘጋቢ 
“ለስድስት ዐሥርት ዐመታት ያኽል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዐይን እና ጆሮ ኾኖ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን ክፉውንም መልካሙንም ጊዜ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያሳለፈ ተቋም ነው ዶቼ ቬለ። እኔም እንደ ጋዜጠኛ ይህንን አንጋፋ ተቋም ስቀላቀል አዲስ የሥራ ባሕል፣ የላቀ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር፣ ከፍተኛ የኾነ ሞያዊ ክህሎት ያገኘሁበት ቀዳሚ እና ተመራጭ ተቋም ነው DW”።


ሰለሞን ሙጬ – የDW የአዲስ አበባ ዘጋቢ
“ይህ ተቋም [ዶቼ ቬለ] የኢትዮጵያን ታሪክ በውል እንዲሁም በቅጡ ሰንዷል ብየ አምናለሁ። ከዚህ ባለፈም ሚዛናዊ፣ ተዐማኒ እና በትክክል ለሕዝብ የሚበጁ ወቅታዊ ዘገባ እና ትንታኔዎችን – በኹሉም የሕይወት መስክ ማለት ነው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በየ ዕለቱ በማቅረብ ወደር የለሽ ውለታ አበርክቷል የሚል እምነት አለኝ። ለዚህም የጀርመን ሕዝብ እና መንግሥት በጣም ሊመሰገኑ ይገባል”። ሰሎሞን