ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፈረንሳይ እውቅናና ድጋፍ እንደምትሰጥ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደርና በአፍሪካ ኅብረት የሀገሪቱ ተወካይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደርና በአፍሪካ ኅብረት የሀገሪቱ ተወካይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት ተገቢና ሕጋዊ የሆነ ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡
በአውሮፓ ብዙ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት እንዳሉ ጠቁመው ሀገራቱ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ባደረጓቸው ምክክሮች የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።
አምባሳደር ላሜክ፤ “የጥያቄውን ተገቢነት እንረዳለን። ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው ውይይት አካል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎት በጥሩ የትብብር መንፈስ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ ምክክርና በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንደሚያገኝ አምናለሁ” በማለት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል አቅምን ለማሳደግ ፈረንሳይ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለባሕር ኃይሉ ድጋፍ ለማድረግ ደስተኞች ነን፤ ድጋፎችን እያደረግን ነው›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ማደራጀቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን የራሷን አስተዋጽኦ እንድታበረክት እንደሚያስችላት ጠቁመው፤ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የሥልጠና ድጋፎችን እያደረገች ትገኛለች።
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ125 ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪክ እንዳላቸው ያስታወሱት አምባሳደር ላሜክ፤ የሀገራቱ ግንኙነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ የወዳጅነት ትስስር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ያደረጓቸው ጉብኝቶችና ያካሄዷቸው ውይይቶች ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረቱ ቀዳሚ ሀገራት መካከልም ፈረንሳይ ሁለተኛዋ ሀገር ናት፡፡ ረጅም ታሪክ እንጋራለን፤ በእዚህም ኩራት ይሰማናል ብለዋል፡፡
ጋዜጣ_ፕላስ
