Home ዜና የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በጊዜያዊነት እንዲያቆም አምነስቲ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በጊዜያዊነት እንዲያቆም አምነስቲ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በጊዜያዊነት እንዲያቆም አምነስቲ ጠየቀ


የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ለሚያደርገውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሰዎችን በግዳጅ ማፈናቀል በአፋጣኝ እንዲያቆም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ። አምነስቲ መንግሥት “በግዳጅ መፈናቀልን ለመከላከል ቁልፍ የሕግ እና የአሠራር ሥርዓቶች ባለማዘጋጀቱ የተጎጂዎችን ሰብአዊ መብቶች ጥሷል” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ እያደረገ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሰዎችን በግዳጅ ማፈናቀል በአፋጣኝ እንዲያቆም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ለፕሮጀክቱ ሲባል “በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎች ውጤታማ መፍትሔ እስከሚያገኙ” የኮሪደር ልማት ሊቆም እንደሚገባ የጠየቀው ትላንት ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ነው።


አምነስቲ ጥያቄውን ያቀረበው የኮሪደር ልማት በመጋቢት 2016 በተጀመረባት አዲስ አበባ በተለይ በሁለት ክፍለ ከተሞች ምርመራ ካካሔደ በኋላ ነው። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ባደረገው ምርመራ በቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ቢያንስ 872 ሰዎች በሕዳር 2017 ብቻ ለኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግዳጅ መፈናቀላቸውን አስታውቋል።
በግዳጅ ከተፈናቀሉት መካከል 254 ሰዎች የ47 የቤት ባለቤት የነበሩ የቤተሰብ አባላት ናቸው። ሌሎቹ 618 ሰዎች ተከራዮች መሆናቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጥናቱ ይፋ አድርጓል። ከተፈናቃዮቹ ውስጥ 114 ሕጻናት እና 13 አረጋውያን ይገኙበታል። 


በሁለቱ ክፍለ ከተሞች በሕዳር ወር በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎችን አጠቃላይ ቁጥር ማወቅ እንዳልቻለ የገለጸው አምነስቲ በጥናቱ ከተገለጸው በላይ “እጅግ የላቀ” ሊሆን እንደሚችል እምነቱን ገልጿል።
በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ለኮሪደር ልማት ከመኖሪያ ቤታቸው ከተፈናቀሉ ሰዎች ጋር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት “በቂ ምክክር” አለማድረጋቸውን እና “ተገቢ ማስጠንቀቂያ” አለመስጠታቸውን አምነስቲ በምርመራው እንደደረሰበት ሰነዱ ይጠቁማል።


በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎች የሕዝብ ስብሰባ ከተካሔደ ከአንድ ሣምንት በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ ቤታቸው ሊፈርስ እንደሆነ በማስጠንቀቅ በሦስት ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ እንደነገሯቸው ለአምነስቲ አስረድተዋል። ለአምነስቲ መጠይቅ መልስ የሰጡ 47 የቤት ባለቤት የነበሩ ሰዎች የከተማ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት ቤት ለቤት ተዘዋውረው ትዕዛዝ በሰጡ ከ24 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ መኖሪያ ቤቶቻቸው እንደፈረሱ ገልጸዋል።


ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱ ክፍለ ከተሞች በተጠቀሰው ጊዜ ከመኖሪያ ቤታቸው ከተፈናቀሉት የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች መካከል “አንዳቸውም ምንም ዓይነት ካሳ” እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።
አምነስቲ መንግሥት “በግዳጅ መፈናቀልን ለመከላከል ቁልፍ የሕግ እና የአሠራር ሥርዓቶች ባለማዘጋጀቱ የተጎጂዎችን ሰብአዊ መብቶች ጥሷል” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ዶይቼ ቬለ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምርመራ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እናትዓለም መለስ ምላሽ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም እና ለመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ በኢ-ሜይል ያቀረባቸው ጥያቄዎችም ምላሽ አላገኙም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት ፌድራል መንግሥት ሹማምንት ግን በተደጋጋሚ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ላይ የሚነሱ ትችቶችን ያስተባብላሉ።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው መጋቢት 11 ቀን 2017 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕጋዊ ማስረጃ ኖሮት ወይ መሬት፤ ወይ ካሳ ሳይከፈለው የተነሳ አንድ ሰው እኔ እስከ ማውቀው የለም” ብለው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ “ከ17 ቢሊዮን [ብር]  በላይ ካሳ ተከፍሏል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ማላዘን የሚፈልጉ ሰዎች ሊያላዝኑ ይችላሉ” ያሉት ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ “ከእኛ በላይ ለኢትዮጵያ ደሐ ሊቆረቆሩ አይችሉም” በማለት በመንግሥታቸው ላይ የሚቀርቡ ወቀሳዎችን አጣጥለዋል።


“ከእድሬ ተባርሪያለሁ”
በየካቲት 2016 የተጀመረው የኮሪደር ልማት ዓላማ “ለልጆቻችን መልካም ሀገር፤ መልካም ከተማ ጥሎ መሔድ” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረግባቸውን አካባቢዎች “ሠፈር ማለት አይቻልም” ያሉት ዐቢይ ከአዲስ አበባ ውጪ ጭምር “ለማየት የሚያስቸግሩ ሠፈሮች እየተቀየሩ” እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲሆን በተለይ በፒያሳ እና በካዛንቺስ ነባር ሠፈሮች ፈርሰዋል። የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ መደብሮች በመገንባት ላይ ለሚገኙ እና ወደፊት ለሚሠሩ ሕንጻዎች፣ የእግረኛ መተላለፊያዎች፣ ፓርኮች እና የመኪና ማቆሚያዎች ቦታቸውን እየለቀቁ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው መጋቢት 11 ቀን 2017 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕጋዊ ማስረጃ ኖሮት ወይ መሬት፤ ወይ ካሳ ሳይከፈለው የተነሳ አንድ ሰው እኔ እስከ ማውቀው የለም” ብለው ነበር።

“ሰዎችን ያለ ፍላጎታቸው ሕጋዊ ከለላ እና ሌሎች ጥበቃዎች ሳይኖሯቸው” ለኮሪደር ልማት ሲባል የሚፈጸመውን “በግዳጅ ማፈናቀል” አምነስቲ ኢንተርናሽናል “በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ” ብሎታል። “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በድንገት እና በግዳጅ ማፈናቀል” የኮሪደር ልማት እየተከናወነ በሚገኝባቸው ከተሞች የሚኖሩ ሚሊዮኖችን “በፍርሐት” እና ለመፈናቀል ሥጋት መዳረጉን አምነስቲ በሰነዱ አትቷል።


ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው በግዳጅ ሲፈናቀሉ በአኗኗራቸው፤ በልጆች ትምህርት፣ በሕብረተሰባዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነቶቻቸው ላይ ተጽዕኖ እንደተፈጠረ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ላካሔደው ምርመራ ሐሳባቸውን ያካፈሉ የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
አንድ ስማቸው ያልተገለጸ ግለሰብ “አሁን ከእድሬ ተባርሪያለሁ። ልጆቼም የአዕምሮ ጤና ችግር ገጥሟቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። ሌላ ግለሰብ “በማሕበራዊ ሕይወት እና በአዕምሮ ጤና ችግሮች ገጥመውኛል።

የቤት ኪራል ለመክፈል እየተቸገርኩ ነው” ሲሉ ከቤታቸው በግዳጅ ከተፈናቀሉ በኋላ ያሉበትን ሁኔታ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል አስረድተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት “በግዳጅ መፈናቀልን ለመከላከል ቁልፍ የሕግ እና የአሠራር ሥርዓቶች ባለማዘጋጀቱ የተጎጂዎችን ሰብአዊ መብቶች ጥሷል” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። መንግሥት የሰብአዊ መብቶችን የጣሰው ባለሥልጣናቱ ከተጎጂዎች ጋር “ትርጉም ያላቸው ምክክሮች ባለማድረጋቸው”፣ “ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓትን ባለመከተላቸው” እና አማራጭ “የመኖሪያ ቤት ባለማቅረባቸው” እንደሆነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አብራርቷል።


የኮሪደር ልማት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እና ሌሎች 65 ከተሞች ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ የመንግሥትን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን በገመገመበት ስብሰባ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በመካሔድ ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሁለተኛ ምዕራፍ “በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል” ሲሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ ተናግረዋል።

ከመጋቢት 2016 ጀምሮ በአዲስ አበባ ለተከናወነው የኮሪደር ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ ብቻ 33 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረው ነበር። ሥራው በተጀመረበት በአዲስ አበባ በመካሔድ ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሁለተኛ ምዕራፍ “በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል” ሲሉ ዶክተር ፍጹም ተናግረዋል።
“በግዳጅ ማፈናቀል በአፋጣኝ ይቁም”
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ የኮሪደር ልማት “በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚያስከትለው ዳፋ በገለልተኛ ወገን እስኪጣራ በጅምላ ማፈናቀል በጊዜያዊነት እንዲቆም” የሚያደርግ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጥሪ አቅርቧል። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ እንዳለው ፕሮጀክቱ መቆም ያለበት “ሰዎችን ማፈናቀል ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር መጣጣማቸውን የሚያረጋግጥ” አሰራር እስኪዘረጋ ጭምር ነው።


ሰዎችን ማፈናቀል ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት ጋር በተጣጣመ መንገድ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ያሳሰበው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ይህን አሠራር “እንደ መጨረሻ አማራጭ ብቻ” ሊከተል እንደሚገባ ምክረ-ሐሳብ አቅርቧል።


ለዚህም “ሁሉም አዋጭ አማራጮች ተፈትሸው” እና “ከሚፈናቀሉ ሰዎች ጋር ሐቀኛ ምክክር ተደርጎ” መሆን ይኖርበታል። መንግሥት ለሚፈናቀሉ እና አቅሙ ለሌላቸው በቂ የመኖሪያ ቤት እንዲያቀርብ አምስነቲ ጠይቋል። ሁሉም “የግዳጅ ተፈናቃዮች ውጤታማ መፍትሔዎች እና ማካካሻ የማግኘት መብታቸውን” የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እንዲያረጋግጥ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ጥሪ አቅርቧል። ይህ “ወደ ቦታ መመለስ፣ ካሳ፣ ማገገሚያ፣ እርካታ እና ወይም እንደማይደገም ዋስትና” ሊያካትት ይገባል።
 
አርታዒ ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር