የክርስቶስ ትንሣኤ          እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ!!

Date:



                                                                                                                                                                                                                                           ትንሣኤ፡- ተንሥአ ከሚለው ግሥ የወጣ ሲኾን ትርጓሜውም መነሣት፣ አነሣሥ፤ መውጣት ብቅ ማለት፣ መታደስ፣ መብቀል ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (1948)፡፡ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 643/፡፡
ትንሣኤ ምንድን ነው?
                                                                                                                                                                                                                                                                                     የክርስቶስ ትንሣኤ በትንቢት የተነገረ፣ በምሳሌ የተገለጠ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዐተ ቁርባንን በሠራበት ምሽት የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር አንሥቶ ለደቀ መዛሙርቱ በሰፊው ገልጿል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ወደ ዓለም ከመምጣቱም ሰው ከመሆኑም አስቀድሞ ነቢዩ ዳዊት “እግዚአብሔር አሁን እነሣለሁ መድኃኒትን አደርጋለሁ በላዩም እገለጣለሁ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ ጠላቶቹንም በኋላው መታ” /መዝ.፸፯፥፷፭/ በማለት ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሣና ጠላቶቹ አይሁድም በትንሣኤው እንደሚያፍሩ ገልጦ ነበር፡፡ “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራታለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤” በማለት አስቀድሞ እንደተናገረው ራሱን ለዓለሙ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ/ዮሐ.፲፥፲፯-፲፰/፡፡
                                                                                                                                                                                                                                                                           ሰውን ለማዳን በፈቃዱ ባደረገው የቸርነት ሥራ በሥጋ ቢሞትም በባሕርዩ ሞት የሌለበትን ጌታ ሞትና መቃብር ይዘው ሊያስቀሩት የማይቻላቸው በመሆኑ ኃጢአትን፣ ሞትንና መቃብርን ደምስሶ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በሦስተኛው ቀን እሑድ በሌሊት ተነሥቷል፡፡ በመቃብሩ ተገጥሞ የነበረው ታላቅ ድንጋይ ተገለባብጦ የተጠቀለለበት የከፈን ጨርቅ በአፈ መቃብሩ ተቀምጦ ተገኝቷል፡፡ ለጥበቃ ተመርጠው ልዩ መመሪያና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው የነበሩ ጭፍሮችም ራሳቸውን እንኳ መጠበቅ ተስኖአቸው በያሉበት ወድቀው እንደ በድን ሆነው ነበር፡፡ ይህች ጌታችን ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት ዕለት “ትንሣኤ” ትባላለች፡፡
                                                                                                                                                                   ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ትንሣኤ ሙታንን አስመልክቶ ሲያስተምር “ክርስቶስ ከሞት እንደተነሣ የሚሰበክ ከኾነ እንዴት ከእናንተ አንዳንዶቹ የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? ሙታን ከሞት የማይነሡ ከኾነ ክርስቶስ አልተነሣማ ደግሞ የእኛ ትምህርት ሆነ የእናንተም እምነት ከንቱ ነው” /፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፲፪-፲፬/፡፡ የሙታን አነሣሥ አስመልክቶ ሲናገር “ሙታን የሚነሡት እንዴት ነው? በሚነሡበትስ ጊዜ የሚኖራቸው አካል ምን ዓይነት ነው ብሎ የሚጠይቅ ሰው ይኖር ይሆናል፡፡ አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተና አፈር ውስጥ ገብቶ ካልበሰበሰ በስተቀር ሕይወት ሊኖረውና ሊበቅል አይችልም፡፡ የምትዘራት አንዲት የስንዴ ቅንጣት ወይም የሌላ እህል ዘር ነው እንጂ ዋናውን የአትክልት አካል አይደለም፡፡ በበቀለና ባደገ ጊዜ ግን አንተ ከዘራኸው ዘር የተለየ መልክና አካል ይኖረዋል” በማለት በምሳሌ አስደግፎ ገልጾአል /፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፴፭-፴፯/፡፡
በኵረ ትንሣኤ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ትንሣኤው አስቀድሞ ነቢያትን ትንቢት አናግሯል፡፡ “ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሬ እነሣለሁ ትንሣኤዬን አድርጋለሁ፤ ኃይሌንም በትንሣኤየ እገልጻለሁ” /መዝ.፲፩፥፭/፡፡ “እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ” ይላል /መዝ.፸፯፥፷፭/፡፡ ራሱም በወንጌል “ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀን እሠራዋለሁ”/ዮሐ.፪፥፲፱/፡፡

                                                      ከጌታችን በፊትና በኋላ ከሞት የተነሡ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ትንሣኤ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ማነጻጸር አይቻልም፡፡ እነዚህ ከሞት የተነሡ ይሁኑ እንጂ፤ አሥነሽ አስፈልጓቸዋል፡፡  የሰራፕታዋን መበለት ልጅ ነቢዩ ኤልያስ /፩ኛ ነገ.፲፯፥፲፪-፳፬/፤ የሱናማዊቷን ልጅ ነቢዩ ኤልሳዕ /፪ኛነገ.፬፥፴፪-፴፯/፤ በሐዲስ ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን /ዮሐ.፲፩፥፵፫/፤ የመኮንኑን ልጅ /ማቴ.፱፥፲፰/፤ ጣቢታን ቅዱስ ጴጥሮስ፤ አውጤኪስንም ቅዱስ ጳውሎስ /ሐዋ.፱፥፴፱፤ ፳፥፲/ እንዳሥነሷቸው ተጽፏልና፡፡ እነዚህ ሰዎች ሁለተኛ ሞት አለባቸው፤ እርሱ ግን የለበትም፡፡ በኋላም በትንሣኤ ዘጉባኤ አሥነሺ ያስፈልጋቸዋል፡፡ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፤ በክርስ ቶስም የሞቱ አስቀድመውወ ይነሣሉ” /፩ኛተሰ.፬፥፲፮/፡፡ እነዚህ ሁሉ ለጊዜው ቢነሡም ተመልሰው ሙተዋል፣ ዳግመኛም የሚያሥነሣቸው ይሻሉ፡፡ ስለዚህም ትንሣኤ ዘጉባኤን ይጠብቃሉ፡፡
                                                                                                                                                                                                                                                                           የክርስቶስ ትንሣኤ በትንሣኤ ዘጉባኤ ለሚነሡት ሙታን ሁሉ የትንሣኤ መጀመሪያ ነው፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ሞትን ዳግመኛ የማያስከትል ከመሆኑም ሌላ በኋለኛይቱ ቀን ለሚነሡት ሙታን መጀመሪያ ነው፡፡ በመሆኑም የጌታችን ትንሣኤ የሚመስል ትንሣኤ የሚነሣ፣ የተነሣም የለም፡፡ ምክንያቱም በሥልጣኑ እንደ ሞተ በሥልጣኑ መነሣቱ ዋናው ልዩ የሚደርገው ነገር ቢኾንም ሌሎች ተጨማሪ ክስተቶችም ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ መቃብር ውስጥ ቢያድርም በመለኮቱ ሕያው ስለኾነ እንደ ሌሎቹ እርሱ መለወጥ (መበስበስ) የለበትም፡፡ በሌላ በኩል በፍጹም ድንግልና ተፀንሶ በፍጹም ድንግልና እንደተወለደ የተነሣውም በዝግ መቃብር “መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ” ሳይል በገዛ ሥልጣኑ ሙስና መቃብርን (በመቃብር መበስበስን) አጥፍቶ የተነሣ ነው፡፡ እነዚህም ተነሥተዋል ቢባል እንደገና ዐረፍተ ዘመን ገትቷቸው ሞተዋል፡፡ መድኃኔ ዓለም ግን “ሞት ሆይ መውጊያህ ይት አለ?” እንድንል አድርጎ ሞትን ድል የነሣ ዳግመኛ ሞት የሌለበት ልዑለ ባሕርይ ነውና፡፡ ከመቃብሩ ላይ የተቀመጠውን ድንጋይ ከትንሣኤ በኋላ መልአኩ አንከባሎታል፡፡ ይኸውም የጌታን በመቃብር አለመኖር አይተው ትንሣኤውን ያለጥርጣሬ እንዲቀበሉት ነው /ማር.፲፮፥፩-፰፤ ማቴ.፳፰፥፩—፫/፡፡ በመኾኑም ከእርሱም በፊት ይሁን በዚያች የእርሱ የትንሣኤ ዕለት ከዚያም በኋላ የእርሱን ትንሣኤ በሚመስል የተነሣ የሚነሣም የለም፤ ለትንሣኤውም ከዚያ በፊት ቀዳሚ ከዚያም በኋላ ተከታይ የለውምና ጌታችን በኲረ ትንሣኤያችን ይባላል፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጆች
                                                                                                                                                                                                                                                                       የክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛ ትንሣኤ በኵር መኾኑንና ክርስቶስ እንደ ተነሣ ሰዎችም ሁሉ እንደሚነሡ ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡ “ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፣ ተቀበረ፤ በሦስተኛውም ቀን ተነሣ፤ ለኬፋም ታየ፤ በኋላም ለዐሥራ ሁለቱ ከዚያም በኋላም ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ… ስለዚህ ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኩር ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና ሁሉ በአዳም እንደ ሞቱ እንዲሁ ደግሞ ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ” በማለት አስረድቷል /፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፩-፰/፡፡ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ሳዊሮስ “የጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል የመወለዱ፣ የመሞቱን የትንሣኤው ሥርዐት እኛን ለማዳንና እኛን ወደ እርሱ ለመመለስ ተደረገ” ይላል፡፡ /ሃይማኖት አበው፤ ክፍል ስድስት/፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ በስሙ ያመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ትንሣኤ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ልጆች ከሠሩት ሥራ ጋር ወደፊት በጌታችን ዳግም ምጽአት ነፍሳቸው ከቀደመው ሥጋቸው ጋር ተዋሕደው ይነሣሉ፡፡ ይህም “ትንሣኤ ዘጉባኤ” ይባላል፡፡ በትንሣኤ ዘጉባኤ ከተነሡ በኋላ ድጋሚ የሥጋና የነፍስ መለያየት(ሞት) የለም፡፡ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኵር ሆኖ ተነሥቶአል፡፡ የክርስቶስም ትንሣኤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ፣ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ የተሻረበት፣ ርደተ ገሃነም ጠፍቶ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ ፍጹም ነጻነት የማይለወጥ ደስታ የተገኘ ስለሆነ “ፋሲካ” ይባላል፡፡ ፋሲካ ደስታ ነው፤ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበት ቀን ነው፡፡  የእርቅ፣ የሰላም የድኅነት ቀን ነውና፡፡

እንደ ማጠቃለያ
                                                                                                                                                                                                                                                                     
አምላካችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራ ተቀብሎ የሞተው ለመላው የሰው ዘር ለአዳም ልጆች ሁሉ ነው፡፡ የወደደን መከራ የተቀበለልን እኛ ስለወደድነው አልነበረም፤ እሱ ስለ ወደደን እንጂ፡፡ አባ ሕርያቆስም “ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው” በማለት እንደተናገረው፤ እግዚአብሔር ወልድ ወዶ ያድነን ዘንድ በሥጋ ሞተ ወዳጆቹ ጻድቃንን ትንሣኤ ለክብር ያስነሣቸውና ያጸድቃቸው ዘንድ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዋቤ መጻሕፍት
                                                                                                                                                                                                                                                                                 ✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ሃይማኖተ አበው
✍️ ቅዳሴ ማርያም
✍️ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ
✍️ ከስቅለት እስከ ትንሣኤ

መ/ር ጌታቸው በቀለ
                                

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...