ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የወሎ ኮምቦልቻ የመንገደኞች አውሮፕላን ማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ። ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የኢትዮጵያ አየር መንግድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በተገኙበት በዛሬው ዕለት ሐምሌ 24/ 2017 ተመርቋል።
ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በመርኃግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የወሎ ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ግንባታ መጠናቀቁ ለክልሉም ይሁን ለሀገራዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የበርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመከናወን ላይ መሆኑን አንስተው ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የአየር ትራንስፖርቱን በማዘመንና ተደራሽነቱን በማስፋት የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በውጭና በሀገር ውስጥ መዳረሻውን እያሰፋ እና እየዘመነ መምጣቱን አንስተው፤ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የወሎ ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃ ህንጻ በአንድ ጊዜ 320 መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ ስድስት አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን በተያዘላቸው ጊዜና በጥራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
