‹‹ተጽዕኗችን ከፍተኛ ስለነበር ከየኤምባሲው ዲፕሎማቶች ጋር እንገናኝ ነበር››
‹‹የትምህርት ሴክተሩን የሚመሩት እነማቸው የሚለው ነገር ያሳስበኛል››
አቶ አንተንሳይ ታፈሰ ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ከሚባሉ ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት ዐሠርቶች ደግሞ በትምህርት ዘርፉ ላይ አሻራውን ለማሳረፍ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ አሁን ላይ ከወዳጆቹ ጋር ‹‹ሂልሳይድ›› የተሰኘ ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያተምር የግል ትምህርት ቤት መሥርቶ አገልግሎት በመሥጠት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ለዓመታት በርካታ ጥያቄዎችና ትችቶች ሲነሱበት ቆይቷል፡፡ ችግሩ በመንግሥትም ዘንድ ታምኖ አሁን ላይ አንዳንድ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይሰማል፡፡ ይኽንን እና በዘርፉ (በተለይም በግል ት/ቤቶች) መሠማራት የነበረውን ተግዳሮት እና ውጤት አስመልክቶ የሚከተለውን ቆይታ ከዝግጅ ክፍላችን ጋር አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- ራስህን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ብትጀምር?
አንተንሳይ፡- አንተንሳይ ታፈሰ እባላለሁ፡፡ እድገቴ ልደታ አካባቢ ነው፡፡ አባቴ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ነበር፡፡ በኋላ ላይም በጥብቅና ሥራ ተሠማርቶ ይሰራ ነበር፡፡ የማንበብ ፍላጎት በልጅነቴ እንዲያድርብኝ የአባቴ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር፡፡ ከጽሑፍና ከጋዜጠኝነት ጋር ከልጅነቴ ጀምሮ ከፍ ያለ ፍላጎት ስለነበረኝ ዩንቨርሲቲም ተማሪም ሆኜ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ላይ እጽፍ ነበር፡፡ በ1984 ዓ.ም ከአ/አ ዩንቨርሲቲ ከኢኮኖሚክስ ት/ት ክፍል ከተመረኩ በኋላ ከጓደኛዬ ክንፉ አሰፋ ጋር ወደ ነፃው ፕሬስ ተቀላቀልን፡፡ የነፃው ፕሬስ መሥራቾች ነን፡፡ አብዛኞቹ የእኔ ባቾች የቅርብ ጓደኞቼ በኢኮኖሚክስ ሙያና በዲፕሎማሲው ውስጥ የሚሳተፉ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች፣ ሚኒስትሮች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው፡፡ እኔ ግን በቀጥታ ወደ ፕሬሱ ነው የገባሁት፡፡ ክንፉ አሰፋ እንደምታውቀው አንጋፋ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ከእሱ ጋር ሆነን ነው ሞገድ የሚባለውን ጋዜጣ በ1986 የጀመርነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እንደተፈራ አሥማረ፣ እስክንድር ነጋ፣ በፍቃዱ ሞረዳ፣ ሰይፉ ፋንታሁን ወዘተ የመሳሰሉ ትላልቆቹ ጋዜጠኞች ከእኛ ጋር ይሠሩ ነበር፡፡ በዚያ ግዜ እኛ በጣም ወጣቶች ነን፡፡ 22 እና 23 ዓመታችን ነው፡፡ በዚያን ወቅት ሞገድ ጋዜጣ በጣም ታዋቂ ሆና ነበር፡፡የተባረሩት 42ቱ የዩንቨርሲቲ መምህራኖቻችንም የበሰሉ ጽሑፎች ያቀርቡበት ነበር፡፡ እኛም የበለጠ ወደሙያው እየገባን ከሁለት ዓመት በላይ ሞገድ በሕትመት ላይ ቆይታለች፡፡
ግዮን፡- ኢኮኖሚክስ አጥንቶ ወደ ጋዜጠኝነት መምጣት ተግዳሮት የለውም?
አንተንሳይ፡- ዋናው ነገር ሥራው ከፍላጎት ጋር የተገናኘ ስለኾነ ነው፡፡ በኢኮኖሚክስ ሥራ ፈልጎ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ እውነት ለመናገር በኢሕአዴግ የመጀመሪያ ዘመን ለነፃው ፕሬስ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እስርና ወከባው መጀመሪያ ላይ አልነበረም፡፡ በሳምንት እስከ 40 ሺህ ኮፒ እናትም ነበር፡፡ ከፍተኛ ጉልበትና ፍላጎት ስለነበረን በርካታ ሰዓታትን በስራው ላይ እናሳልፍ ነበር፡፡ ከእኛ ቀድመው የነበሩት ‹‹እይታ›› እና ‹‹ጦማር›› ጋዜጦች ብቻ ነበሩ፡፡ ጦቢያ እና ሪፖርተር ጋዜጣና መጽሔት የመጡ ከእኛ በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ ተጽእኗችን ከፍተኛ ስለነበር ከየኤምባሲው ከዲፕሎማቶች ጋር እንገናኝ ነበር፡፡ ከየዩንቨርሲቲው ፕሮፌሰሮች እና አስተማሪዎችም ጋር ጥብቅ ግንኙነት ነበረን፡፡ የውጪ ስብሰባ እድሎችም ላይ እንሳተፍ ነበር፡፡ ወቅቱ ብዙ ልምድ ያገኘንበት ነበር፡፡ በኋላ ግን በተለይም ከ1987 ዓ.ም በኋላ የመንግስት ቁጥጥር በጣም እየባሰ መጣ፡፡ በተደጋጋሚ መታሠር ተለመደ፡፡ ለምሳሌ እኔ ፍርድ ቤት ለሦስት ጊዜ ተከስሻለሁ፡፡ ለበርካታ ግዚያት ታስርያለሁ፤ በገንዘብ ተቀጥቻለሁ፡፡ኋላ ላይ ክንፉ አሰፋ ከሀገር ሲወጣ ብቻዬን ቀረሁ፡፡ ጫናው ሲበዛ እኔም ሥራውን ለመተው ተገደድኩ፡፡
ግዮን፡- ከፕሬሱ ቀጥሎ ወደ የትኛው የሥራ መስክ ተሰማራህ?
አንተንሳይ፡- ፕሬስ ላይ የግራፊክስና ኤዲቲንግ ሥራው ላይ ቀጥታ እንሳተፍ ስለነበር የኮምፒውተር ልምዳችንን አዳብረን ነበር፡፡ ስለዚህ ፕሬሱን ስተው አንድ ውጪ ሀገር የነበረ ዘመዴ አገዘኝና ጥቂት ኮምፒውተሮች ላከልኝ፡፡ ከዚያም የኮምፒውተር ትምህርት ቤት ከፍቼ በቀን ለ3 ክ/ግዚያት ማስተማር ጀመርኩ፡፡ ሦስቱንም ክ/ግዚያት ለ10 ሰዓታት እኔው ነበር የማስተምረው፡፡ በወቅቱ የኮምፒውተር ትምህርት ብርቅ ስለነበር ብዙ ሰው ይማር ነበር፡፡ ለሁለት ዓመታትም በዚህ ስራ ውስጥ ከቆየሁ በኋላ ከ1990 ዓ.ም በኋላ ወደ ግል የትምህርት መስክ ተሰማርቼ ሂልሳይድ የሚባለውን የመጀመሪያውን ትምህርት ቤት ላምበረት አካባቢ ከፈትን፡፡ ላለፉት 25 ዓመታትም በዚሁ ሥራ ላይ እገኛለሁ፡፡
ግዮን፡- ሂልሳይድ ትምህርት ቤት እስከ ምን የትምህርት ደረጃ ያስተምራል?
አንተንሳይ፡- ሂልሳይድ ትምህርት ቤት ከቅድመ መደበኛ እስከ 12 ክፍል ድረስ ያስተምራል፡፡ ሦስት ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ከ370 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡
ግዮን፡- ሦስቱ ቅርንጫፎቻችሁ የት የት ነው የሚገኙት?
አንተንሳይ፡- አንዱ ለም ሆቴል አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ላምበረት አካባቢ ይገኛል፡፡ ይኼ ደግሞ የኬጂ ቅርንጫፍ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ወሰን አካባቢ ሲኤምሲ መስመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ1-12 ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት ነው፡፡
ግዮን፡- ትምህርት ቤት በመክፈት ሂደት ውስጥ ያሉት ፈተናዎች ምንድናቸው?
አንተንሳይ፡- ትምህርት ቤቱ በ1990 ዓ.ም ሲከፈት ምንም ዓይነት የመንግሥት ቁጥጥር ያልነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ በሰዓቱ ትምህርት ቤት ለመክፈት ቤት መከራየት፣ ካሪኩለም መቅረጽ/መምረጥና መምህር ቀጥሮ ሥራውን መጀመር ብቻ ነበር የሚያስፈልገው፡፡ ፈቃድ የሚሰጥ ተቋም ቢኖርም ከንግድ ተቋምነት አኳያ እንጂ አሁን ባለው ደረጃ የቁጥጥር ሥርዓት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ነው ትምህርት ቤቱን የከፈተነው፡፡ በዚህም በመጀመሪያው ዓመት ላይ ከ200 በላይ ተማሪዎች ነበሩን፡፡ የከፈትነው ትምህርት ቤትም ከኬጂ እስከ 2ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምር ነበር፡፡ ስለዚህ ስንጀምር ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ከመክፈት በፊት ፈቃድ ሰጭው የመንግሥት አካል ተገኝቶ ለትምህርት ሥርዓት የሚሆን ሁሉም ግብዓቶች ተሟልተዋል ወይ ብሎ ይገመግማል፡፡ ከገመገመና ፈቃድ ከሰጠ በኋላ ነው ሥራው መጀመር የሚቻለው፡፡
ግዮን፡- ሂልሳይድ የሚለው የትምህርት ቤታችሁ ሥያሜ ትርጓሜው ምንድነው?
አንተንሳይ፡- የትምህርት ቤታችን ሥም ሀገረኛ ሥም ቢኾን ኖሮ ይመረጥ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያን ጊዜ የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ላምበረት አካባቢ ሲከፈት የካ ተራራ አካል በሆነው ላምበረት አካባቢ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ስለሚገኝ ለቦታው ገላጭ እንዲሆን ተብሎ “ሂል ሳይድ” ወይም “ከተራራው ጎን” የሚል ስያሜ የተሰጠው፡፡
ግዮን፡- ትምህርት ቤቱን ስትከፍቱ ቦታ ለማግኘት ከመንግሥት ያገኛችሁት ድጋፍ አለ?
አንተንሳይ፡- የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ ስንከፍት ተከራይተን ነው የከፈትነው፡፡ ዋናው ግቢ ስንከፍት ደግሞ በሊዝ ተጫርተን ነው፡፡ የጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ በግልፅ ጨረታ አሸንፈን ነው የያዝነው፡፡
ግዮን፡- የግል ትምህርት ቤቶች አትራፊዎች ናቸው ይባላል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?
አንተንሳይ፡ እንደሁኔታው ይለያያል፡፡ የራሴን ከሌሎች የንግድ ሴክተሮች ጋር ሳነፃፅረው ግን ፍጹም ማወዳደር የማይቻል ነው፡፡ ሲጀመር የሥራው ዓይነት በራሱ ትርፍ ብቻ ተሰልቶ የሚገባበት ዘርፍ አይደልም፡፡ የማኅበራዊ ግዴታን ለመወጣትም ጭምር ነው ወደ ዘርፉ የሚገባው፡፡ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ጥቅም የማያስገኝባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የመነሻ ወጪው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ሰፊ ቦታ፣ የህንፃ ግንባታና በርካታ ግብዓቶችና ቁሳቁሶችን ማሟላት ስለሚፈልግ በጣም ውድ ኢንቨስትመንት ነው፡፡የክፍያ ግዜውም በረጅም ዓመታት የሚሰላ ነው፡፡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ስለሚጠይቅ የግድ ብድር መጠየቁ አይቀርም፡፡ ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የትምህርት ቤቶች ገቢ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ለመንግሥት አካላት ግልጽና የታወቀ ነው፡፡ ሊጭበረበር የማይችል በቋሚ ደንበኞች የሚገኝ ገቢ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ተከታትሎ ደረሰኝ ይወስዳል፡፡ በሌላው ሴክተር እንደሚታየው ዐይነት ገቢን የመደበቅ ነገር የለበትም፡፡ ይህ በመሆኑም ግልጽ አሠራር ስላለው ከፍተኛ ግብር ይከፈልበታል፡፡ ከሕንፃ ግንባታና ከመማር ማስተማሪያ ግብዓት ጋር እንዲሁም ከቦታ ኪራይ ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ወጪዎች አሉበት፡፡ ስለዚህ የተጋነነ ገቢ ወይም ትርፍ አለው ብዬ አላምንም፡፡
ግዮን፡– የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች አንዱ ከአንዱ መዋዋስ ያለባቸው ምን ዓይነት ነገሮችን ነው?
አንተንሳይ፡- እውነት ለመናገር የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከግል ትምህርት ቤቶች ብዙ ነገር መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት የሚመደብ በጀት ሦስትና አራት የግል ትምህርት ቤቶችን ሊያስተዳድር የሚችል ነው፡፡ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የሆነ የሃብት ብክነት ይታይባቸዋል፡፡ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት የሚሠራ መምህር በሳምንት 5 እና 10 ክፍለጊዜ ብቻ ያስተምራል፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች አሁን ካላቸው በግማሽ መምህራን ማስተማር ይችላሉ፡፡ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠናከረ የትምህርት ሥራ ክትትል (educational supervision) አለ፣ ጥብቅ የመምህራን የሥራ ውጤት ምዘና አለ፣ ከፍተኛ የሆነ ወጭ ቆጣቢ የሥራ አካሄድ ይከተላሉ፣ የተሻለ የተማሪዎች የባሕሪ ክትትል እና ቀረፃ አለ፣ የተሻለ ፋሲሊቲ አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ናቸው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከግል ትምህርት ቤቶች መማር ያለባቸው በርካታ ነገሮ አሉ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ለመንግሥት የምንከፈለው ግብር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ምን ያክል እየባከነ እንደሆነ የመንግሥት አካላት ፈጽሞ ያስተዋሉት አይመስልም፡፡ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ቤተሰቦች ሳይቀሩ ልጆቻቸውን ማስተማር የሚፈልጉት በግል ትምህርት ቤት ነው፡፡ በነፃ የመንግሥት ትምህርት ቤት እያለላቸው ከፍለው ማስተማርን የመረጡት በመንግስት ት/ቤቶች ደረጃ ሁለገብ በሆነ መልኩ የተሟላ ባለመሆኑ ነው፡፡ የመምህራን ጥራት፣ የግብዓት ጥራት ፣ የስራ ተነሳሽነትና የትምህርት አመራር (instructional leadership) በመንግሥት ትምህርት ቤት አካባቢ የወደቀ ነው፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ክፍላቸው ባዶ ነው፡፡ የመማሪያ ክፍሎቹ ተማሪ አጥተው የታሸጉ አሉ፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ በዚህ ስራ ላይ 25 ዓመታት እንደቆየ ሰው የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች የቀሰምነው በጎ ተሞክሮ አለ ብዬ ለመውሰድ እቸገራለሁ፡፡ ይልቅ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከግል ትምህርት ቤቶች ብዙ ሊማሩ ይገባል እላለሁ፡፡
ግዮን፡- በዘርፉ በቆየህባቸው ዓመታት ያገኘኸው ወይም ያጣኸው ነገር ምንድነው?
አንተንሳይ፡- አሁን አሁን የኢትዮጵያ የትምህርት ውድቀት የደረሰበትን ደረጃ ሳይ ብዙ እቆጫለሁ፡፡ የችግሩን ደረጃ እኛ ውስጥ እያለን እናውቅ ነበር፡፡ አሁን በግልጽ ሕዝቡም ጭምር የሚያውቀው ጉዳይ ሆኗል፡፡ በጣም የሚገርመው መምህራንን ለመቅጠር ማስታወቂያ ስናወጣ ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ ዲግሪ ያላቸው ምሩቃን እኛ ከምናስተምራቸው ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ካሉ ተማሪዎች ያነሱ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ መሰረታዊ የ1ኛ ደረጃ የትምህርት ግብ የሆነውን መሰረታዊ የንባብና የስሌት ክህሎት (basic literacy and numeracy) ከሌለው የትምህርት ስርዓቱ ህመም ሊታከም የሚችል አይደለም ማለት ነው፤ እንደ አዲስ ፈርሶ መሰራት ያለበት እንጂ፡፡ አንድ አንቀፅ አንብቦ ስለርሱ በመረዳት መልስ መስጠት መቻል የመጀመርያው ሳይክል (ከ1ኛ-4ኛ ክፍል) ዋና የትምህርት ግብ ነው፡፡ እንዲሁም አራቱን የስሌት ዓይነቶች በማወቅ የማስላትና በሕይወትም ውስጥ መተግበር መቻል በዚሁ የትምህርት ደረጃ ሊሳካ የሚገባ ክህሎት ነው፡፡ እነዚህን መሰረታዊ ክህሎቶች ማሟላት ያልቻሉ ናቸው ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው የሚመጡት፡፡ በዚህ ደረጃ ትምህርቱ መውደቁን ለዓመታት እያየንው ስለመጣን ከዚህ የሥራ መስክ ለመውጣት ጭምር ገፊ የሞራል ምክንያት ሲሆን ይታያል ፡፡ በሌላ በኩል ተስፋችንን የሚያለመልመው ጥቂት የማይባሉ ከግል ትምህርት ቤት የሚወጡ ተማሪዎች በየዩንቨርሲቲው ገብተው የሚያሳዩት ውጤት፣ በተለያዩ ተቋማት ተቀጥረው የሚያሳዩት የሥራ አፈፃፀም፣ የሕይወት ስኬታቸው፣ መርሐቸውና ዲሲፕሊናቸውን ስናይ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ነገር በትውልዱ ላይ ተስፋ እንድንጥል ያደርገናል፡፡ ነገር ግን ብዛታቸውን ስናይ ደግሞ ሌላ ስጋት ይጫነናል፡፡ ስለዚህ የተደበላለቀ ስሜት ነው ያለኝ፡፡ በተለይ የትምህርት ሴክተሩን የሚመሩት እነማቸው የሚለው ነገር ያሳስበኛል፡፡ ብዙዎቹ በሙያቸውና በዲስፕሊናቸው ዘርፉን ሊመሩት ብቁ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሴክተሩን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች የሙያ ብቃት የሌላቸውና ከተለያየ ት/ቤቶች በመምህርነት ሞያቸው ብቃት ስለሌላቸው ተቀንሰው በአመራርነት የተመደቡ ናቸው፡፡ ስልጠናቸው ከትምህርት ሥራ ውጪ የሆኑ የፖለቲካ ካድሬዎችና መሰሎችም ዘርፉን ሲመሩት ይታያሉ፡፡
በሌላ በኩል ለግል ትምህርት ተቋማት ተስፋ አስቆራጩ ነገር በሴክተሩ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ይህ ችግር በስፋት ይታያል፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ከ1500 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ከስልሳ ፐርሰንት በላይ የሚሆው የከተማው ተማሪ የሚማረው በነዚህ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥት ለጠቅላላ ትምህርት (ቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል) ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ራሱ በሚያስተዳድራቸው ት/ቤቶች በኩል መስጠት አልቻለም ማለት ነው፡፡ እዚያ ውስጥ የሚፈሰው ሃብት ውጤታማ እንዲሆን አላደረገም ማለት ነው፡፡ የአስተዳደር ሥርዓቱ የተበላሸ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ተማሪው ወደ ግል ትምህርት ቤት እንዲመጣ ተገዷል ማለት ነው፡፡ ወላጅ አሁን በሚታየው የኑሮ ውድነት በሌለው አቅሙ እየከፈለ ለማስተማር ተገዷል፡፡ መንግሥት በግል ትምህርት ቤቶች ላይ በጣም ጥብቅ የሆነ የክትትል መስመር ዘርግቷል፡፡ ሊያሟሉት የሚገባው ግብዓቶች፣ የሰው ኃይል አደረጃጀታቸው፣ የግቢው ስፋት ወዘተ ሁሉ ቁጥጥር ይደረግበታል፡፡ በ26 ስታንዳርዶች ውስጥ በተዘረዘሩ 108 አመልካቾች እና በ278 ገላጮች በያዘ ዝርዝር እና ጥብቅ ቼክ ሊስት ይገመገማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ስታንዳርዶች የሃገሪቱን እና የከተማውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን በግሌ ቁጥጥሩንና ክትትሉን እደግፋለሁ፡፡ ምክንያቱም ያንን የማይከተሉ የደቀቀ ቤት ውስጥ ፍፁም ለትምህርት ስራ አመቺ ባልሆነ ደረጃ ያለበቂ ግብዓት ሥራ የሚጀምሩ ት/ቤቶችን መልክ ያስይዛል፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክ የግል ት/ቤቶች የቢዝነስ ተቋማት መሆናቸው እሙን ነውና ሌሎች የግል የቢዝነስ ተቋማት ያላቸውን በፋይናንስና በቢዝነስ ጉዳያቸው ላይ በነጻነት የመወሰን መብታቸው ሲጋፋ ይታያል፡፡
ግዮን፡– እነዚህ ነፃነት ተጋፊ ፖሊሲዎች ቢጠቀሱ?
አንተንሳይ፡- ለምሳሌ ባለፉት 3 ዓመታት ሁለት ጊዜ የትምህርት ክፍያ ማስተካከያ እንዳይደረግ ክልከላ ተጥሏል፡፡ይኼ በየትኛውም መመዘኛ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ከ2012 ለ2013 በኮቪድ 19 ምክንያት በሚል ተከለከለ፤ ከ2014 ወደ 2015 ደግሞ በየሁለት ዓመት ነው መጨመር ያለባችሁ በሚል በድጋሚ ታገደ፡፡ ይኼ በግል ትምህርት ቤቶች ባለሃብቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ተስፋ መቁረጥ አስከትሏል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ ከ100% በላይ በጨመረበት ሀገር ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ትምህርት ቤቶቹ እንዲሸከሙ ተገደዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በትምህርት ግብዓቶች አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ የመምህራን ደሞዝ በተገቢው ለማስተካከል አቅም ስለሚያሳጣ የትምህርት ስራው ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር የሆኑት መምህራን የስራ ተነሳሽነታቸው ይቀንሳል፡፡ ባለሃብቶቹም ሃብታቸውን ያፈሰሱበት መዋዕለ ነዋይ የሚፈለገውን ትርፍ ስለማየስገኝላቸው የስራ መስኩን የመሸሽ አዝማምያ ያሳያሉ፤ አዲስ ባለሃብቶችም ወደ ሴክተሩ ለመምጣት ይፈራሉ፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ የትምህርት ጥራቱ እንዲወድቅ ደርጋል፡፡ ይኼ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት የግል ትምህርት ቤት ተቋማትን የሚያዳክም ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ “የትምህርት ቤት ክፍያ ማስተካከያ ሲደረግ ወላጆችን ሰብስባችሁ ስለጭማሪው ማስተካከያ አስረዱ” በማለት አላስፈላጊ ውዝግብና ጭቅጨቅ አስከትሏል፡፡ ይሄ በመርህ ደረጃ ትክክል አይደለም፡፡ ደንበኛ አገልግሎት የሚገዛበትን ዋጋ አይቶ መወሰን የራሱ ድርሻ ነው፡፡ የመንግሥት አካላት ግን የግል ትምህርት ቤቶች ወጭዎች ላይ ምንም አስተዋፅኦ ሳያደርጉ በዋጋ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይገባቸውም፡፡ ይህ ጣልቃ ገብነት ዘርፉን እየጎዳው ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ከሦስት በላይ ትልልቅ ትምህርት ቤቶች ከዘርፉ ለመውጣት ተዘጋጅተው እንደሚገኙ አውቃለሁ፡፡ እኛ እራሳችን ዘርፉን ቀይረን ሆስፒታል እናድርገው፣ ሪልስቴት እናድረገው ወዘተ የሚል እቅድ አለን፡፡ ስለዚህ ብዙ ተግዳሮቶች አሉት በተለይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፡፡
ከዚህ ጉዳይ ውጪ በመንግስት ጫናነት ሊነሳ የሚገባው የግል ት/ቤቶችን መቶ በመቶ በሁልም ረገድ እንደ መንግስት ት/ቤት ለማድረግ የሚኬድበት መንገድ ነው፡፡
ግዮን፡- መንግሥት እናንተ ላይ ከጣለው ጫና ውጪ ያበረከተው በጎ አስተዋጽኦ አለ?
አንተንሳይ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ዘርፉን የተረዳው ይመስላል፡፡ የመንግሥት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት የግል ትምህርት ቤቶች በጥራት ረገድ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን እንዲመስሉ ያደርጋል፡፡ የአዲስ አበባ የትምህርት ጥራትና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው እያንዳንዳንዱን የትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ የሚከታተለው፡፡ ይህ ተቋም ከላይ አካባቢ ጥሩ ጥሩ ሰዎች ያሉት ነው፡፡ ተቋሙ ካሪኩለም አተገባበር ላይ፣ የግብዓቶች ማሟላት ላይ፣ የትምህርት ጥራት ላይ ነው ትኩረት አድርጎ ይሰራል፤ ተገቢም ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ፋይናንሻል ነገሮች ላይ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ግን የግል ትምህርት ቤቶችን ያዳክማል፡፡ ባለሙሉ ተስፋ ሆነው በዘርፉ እንዲቆዩ አያርጋቸውም፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ረጅም እጅ ቢሰበሰብ የተሻለ ይኾናል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ከጠፉ ምን ሊከሰት እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በቅርቡ ለከፍተኛ ትምህርት ፈተና አብዛኛው ያለፉ ተማሪዎች ከግል ትምህርት ቤቶች ነው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑም ይህን መሠረት አድርጎ እነዚህን ትምህርት ቤቶች እንዴት እንንከባከባቸው እንዴትስ ከእነርሱ ልምድ እንውሰድ የሚል ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ግን ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላለው የሚመለከተው የአ/አ መስተዳደር ስለሆነ የግል ት/ት ተቋማት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በመረዳት በመሬት አቅርቦት፣ በታክስ እፎይታ፣ በመምህራን ጥቅማጥቅም፣በስልጠና ወዘተ ሊያግዘን ይገባል፡፡
ግዮን፡- መንግሥት በእናንተ ላይ ጫና ሲያደርግ እናንተ እንዴት ነው ጫናውን የምትቋቋሙት?
አንተንሳይ፡- እኛ የግል ትምህርት ቤቶች ባለንብረቶች ማኅበር የሚባል ማኅበር አለን፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ የተደራጀ ነው፡፡ ብዙ ሥራዎች ያካሂዳል፡፡ እንደ ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔ ያካሂዳል፡፡ አመራሮች መርጦ ሾሟል፤ ወዘተ…፡፡ ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት የሚካሄደው በዚህ ማኅበር በኩል ነው፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ፖሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት በግል ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የመንግሥት ፖሊሲ አስፈፃሚዎች ከፍ ሲልም ፖሊሲ አውጪዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የግል ትምህርት ቤት ክፍያን በተመለከተ ሥጋት አለን፡፡ ምክንያቱም ፖሊሲውን የሚያወጡ እነዚህ ሰዎች በትምህርት ቤት ክፍያ ረገድ ከስነምግባር ውጪ የግል ጥቅማቸውን በሚያወጡት ፖሊሲ በኩል የማስፈጸም ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ግዮን፡- የግል ትምህርት ቤቶች ባለንብረቶች ማኅበር ከተቋቋመ ምን ያህል ዓመት ኾነው? የሚመጡባችሁን ጫናዎችስ በምን ዓይነት መልኩ እየተቋቋመው ነው?
አንተንሳይ፡- ማኅበሩ ከተቋቋመ ከ10 ዓመት በላይ ይኾነዋል፡፡ የተለያዩ አመራሮች መርጠናል፡፡ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚቃጣውን ጫናም ለመታገል ጥረት ያደርጋል፡፡ በተለይ ጣልቃ ገብነቱ እየሰፋ በመጣ ቁጥር እርሱን ለማጠናከር ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ የምንፈልገውን ያህል ውጤት አምጥቷል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በማኅበሩ በኩል ብቻ የሚደረገው ጥረት አድማጭ ካላገኘ ለውጥ ስለማያመጣ ነው፡፡
ግዮን፡- እንደ ባለሙያ ከለውጡ በኋላ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከአመራር ጀምሮ የተደረጉትን ለውጦች እንዴት አየኻቸው?
አንተንሳይ፡- ከለውጡ በኋላ መሰረታዊ ለውጥ ተደርጓል፡፡ዋናው የትምህርት ሴክተሩ ችግር እጅግ ከፍተኛና ሃገራዊ ርብርብ የሚሻ (national emergency) መሆኑን የመንግስት አካላት ተረድተዋል፡፡ይህንን ተከትሎም የከሪኩለም ለውጥ ተደርጓል፡፡ በስራ ላይ የነበረው ከሪኩለም ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ዓለም ባንክ አንድ ጥናት አድርጎ የሚያስደንቅ ውጤት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ የ2ኛ ደረጃው ከሪኩረም በአሜሪካና በአውሮፓ ከሚሰጠው ትምህርት በይዘት ደረጃ ሰፊና ጥልቀት ለው መሆኑን አሳይቷል፡፡ 11ኛ እና 12 ክፍል ላይ ያሉ በርካታ ዩኒቶች እኔ ዩንቨርስቲ ፍሬሽማን እና 2ኛ ዓመት ጭምር የተማርኳቸው ናቸው፡፡ አሁንም በርካታ ዩንቨርሲቲዎች በዓለም ላይ የሚሰጡት በእኔ ዘመን እንዳለው ነው፡፡ ነገር ግን የቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት የዩንቨርሲቲ የማጠናቀቂያ ግዜን ወደ 3 ዓመት ለማውረድ ሲባል 2ኛ ደረጃ ትምህርት 10ኛ ክፍል ላይ እንዲጠናቀቅ ያደረገ ነበር፡፡ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ለዩኒቨርሲቲ መሰናዶ በሚል ከልጆቹ አቅም በላይ ያለ የትምህርት ይዘት ውስጥ እንዲያልፉ የሚያስገድድ ነው፡፡ እጅግ ዝቅተኛ በሆነው የመምህራን አቅም እና በትምህርት ይዘቱ ስፋትና ክብደት ሳብያ የተማሪዎቹ የትምህርት ተነሻስነት ዝቅተኛ ስለሆነ ለዓመታት በወጣቶቻችን የትምህርት አፈፃፀም ረገድ የሆነውን አይተናል፡፡ ይህ ካሪኩለም ለርካታ ዓመታት ተማሪዎቹን መሞከርያ ካደረገ በኋላ አሁን በለውጡ ጊዜ ተቀይሯል፡፡ ይሄ መሠረታዊ ለውጥ ነው፡፡ 2ኛ ደረጃ ማጠናቀቂያም እንደቀድሞው 10ና ክፍል ሳይሆን 12ኛ ክፍል ሆኗል፡፡ የኮሪኩልም ሽግሽግም ተደርጓል፡፡
ይህ ለውጥ የትምህርት ሴክተሩን ሕመም ለማከም የተወሰደው የመጀመርያ እርምጃ ነው፡፡ሆኖም መሰረታዊው ጉዳይ እና የትምህርት ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍ ቁልፉ ጉዳይ ብቃት ያላቸው መምህራንን የማዘጋጀት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሲባል መምህሩ በመጀመሪያ ደረጃ በሥርዓቱ ተምሮና አውቆ የወጣና በሥልጠናው ዘርፍ የእውቀት ውስንነት የሌለበት ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሙያዊ አቋሙ የዳበረ ተማሪዎችን በስብዕና ሊቀርፃቸው የሚችል አርአያ የሆነ መምህር ሲሆን ነው፡፡ የትምህርት ይዘቱን በደንብ የሚያውቅ እንዲሁም ሀገራዊ ኃላፊነት ወስዶ የልጆቹን ሕይወት ከዋናዎቹ ሀገረኛ እሴቶች ጋር ለማዋደድ የፈቀደና የሚችል ባለ ሙሉ ስብዕና መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚሀ ረገድ የመምህራን ማሠልጠኛዎችም እንደአዲስ መደራጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ልክ እንደድሮው መውደቂያ ያጣና ዝቅተኛ ነጥብ ያመጣውን ለአስተማሪነት መመደብ ካልቀረ የትምህርት ጥራት ሊመጣ አይችልም፡፡መምህራን በማህበረሰቡ ዘንድ ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኙና መሰረታዊ ቁሳዊ ፍልጎታቸውን ማሟላት የሚስችል ደሞዝ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ወደ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋማት መውሰድ ግዴታ ነው፡፡ ለዚህም ሳቢ ጥቅማጥቅሞች፣ የሞራል ድጋፍና የህብረተሰቡ ለመምህራን ክብር የሚሰጥ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ልክ የኢትዩጵያ አየር መንገድ፣ኢትዮ ቴሌኮም እና ሌሎች ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ተማሪዎች እንደሚመለምሉ ት/ት ሚኒስቴርም ከነዚህ ጋር መፎካከር አለበት፡፡ ለዚህም በየመንግስ ት/ቤቶች እና በየዩኒቨርሲቶዎች ውስጥ የሚታየውን ቅጥ ያጣ ዘረፋና ከፍተኛ የሃብት ብክነት በመቆጣጠር ጥራት ላለው የመምህራን ስልጠናና ጥቅማጥቅም የሚሆን በቂ በጀት ማግኘት ይቻላል ባይ ነኝ፡፡
ግዮን፡- በግል ትምህርት ቤቶች በተለይ ለሕፃናት የሚሰጡት ትምህርቶች ይበዛሉ፡፡ በሕፃናቱ ላይም ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ የሚሉ አስተያየቶች ብዙ ጊዜ ይሰማሉ፡፡ አንተ እንዴት ታየዋለህ?
አንተንሳይ፡- አስተያየቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እውነትነት አለው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በመንግሥት በኩል የቀረበው ካሪኩለም ከ5 እስከ 6 ትምህርቶችን እንዲማሩ ነው፡፡ በተለይ በአዲሱ ከሪኩለም ላይ የመጡ አዳዲስ ትምህርቶችም አሉ፡፡ ምንም ዐይነት የመምህራን አቅርቦት የሌለባቸው ናቸው፡፡ ማንም መምህር ያልሰለጠነባቸው የትምህርት ዓይነቶች አሉ፡፡ የተማሪ መጻሕፍትም የላቸውም፡፡ ይህ ካሪኩለም ሲዘጋጅ አንድን አማካኝ በአዲስ አበባ ቤተሰብ ውስጥ የሚድግን ህፃን/ታዳጊ ማዕከል አድርጎ ነው፡፡ ለምሳሌ የግል ትምህርት ቤት የሚመጣ ወላጅ በመጠኑም ቢኾን ለመረጃ የቀረበ፣ በቤት ውስጥ ልጆቹን በትምህርት ለመደገፍ ልምምድና ፍላጎት ያለው፣ ስለትምህርት ጉዳይ የተሸለ ግንዛቤ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ከመንግሥት የሚመጣ ካሪኩለም ከዚህ አንፃር የእኛ ተማሪዎችን ሙሉ ጊዜ ያሠሯቸዋል ብዬ መናገር አልችልም፡፡ ብዙ ግዜ ልጆች ትርፍ ጊዜ ስለሚኖራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው የተወሰኑ ተጨማሪ ትምህርቶችን ቢያገኙ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ግን የመንግሥትን ካሪኩለም በተገቢው ሁኔታ ካጠናቀቁ በኋላ ነው፡፡ በትርፍ ሰዓት የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡
በተማሪዎችም ላይ ይህ ነው የሚባል ጫና ፈጠረ ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህ ተጨማሪ ተሳትፎዎች በተማሪዎች ላይ ጫና ያመጣሉ ብሎ ትምህርት ጽ/ቤት ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በተግባር ግን በተማሪዎች ላይ ጫና ሲኾን አልታየም፡፡ ለምሳሌ በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ የግልና የመንግሥት ት/ቤች ጥያቄና መልስ ውድድር ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ውድድር አንድም ቀን የመንግሥት ት/ቤት አሸናፊ ሆኖ አላየሁም፡፡ አሸናፊዎቹ የግል ት/ቤት ተማሪዎች ናቸው፡፡ በብሔራዊ ፈተና ውጤትም የግል ት/ቤት ተማሪዎች ከፍተኛውን ቅጥር ይይዛሉ፡፡ ይህ ማለት በመንግሥት የተቀመጡ የትምህርት ግቦች በግል ት/ቤት ተሳክተዋል፡፡ ስለዚህ ትርፍ ሰዓታቸውን በሌሎች ትምህርቶች ላይ ማሳለፋቸው እንደተጨማሪ ጥቅም ነው መወሰድ ያለበት፡፡ ወላጆችም ወደ ግል ት/ቤት የሚመጡት ይኼንኑ ፈልገው ነው፡፡
ግዮን፡– ት/ቤታችሁ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ተሣትፎ ያውቃል?
አንተንሳይ፡- በዋናነት የበጎ አድራጎት ሥራ የምንሠራው በተማሪዎች ክበብ አደረጃጀት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ክበብ የሚሰበሰብ በርካታ ገንዘብና ቁሳቁስ አለ፡፡ ይህ ሥራ የሚከናወነውም በቋሚነት ነው፡፡ የክበብ ሥራውን የሚያከናውኑትም ተማሪዎቹ እራሳቸው ናቸው፡፡ ተማሪዎች በዚህ ውስጥ ለጋስነትን እሴት አድርገው ያድጋሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ ት/ቤቱ በራሱ ከመንግሥት ት/ቤቶች በትምህርት በአፈፃፀማቸው እና በዲሲፕሊናቸው ለተመረጡ ተማሪዎች ስኮላር ሺፕ ሰጥቶ በነፃ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች አሉ፡፡ ይህን ነገር ወደፊት በተለይም ከ2016 ጀምሮ አጠናክረን ከወረዳ ት/ት ጽ/ቤት በኩል ተማሪዎች ተመርጠው መጥተው እንዲማሩ እናደርጋለን፡፡ የሚመረጡት ተማሪዎች ግን እነማናቸው የሚለው በጣም ወሳኙ ነጥብ ነው፡፡ በአጠቃላይ በበጎ አድራጎት ሥራ በኩል የተሳካ ሥራ በማከናወን ላይ እንገኛለን፡፡
ግዮን፡- የትምህርት ተቋማችሁን ወደ ዩንቨርሲቲ የማሳደግ እቅድ አላችሁ? ያን ብታደርጉ የሚገጥማቹ እንቅፋት ምንድነው?
አንተንሳይ፡- እስካሁን ወደ ዩንቨርሲቲ የማሳደግ እቅድ የለንም፡፡ ምክንያቱም አሁን በሀገሪቱ የሚታየው የጸጥታ ችግር ምክንያት ብዙ ተማሪዎች ወደተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች መሄድ አቆሙ እንጂ ነገሮች ሲረጋጉ በቂ የሆነ ዩንቨርስቲዎች በሀገራችን እንዳሉ እናምናለን፡፡ ይህ ማለት ግን ለ120 ሚሊዮን ህዝብ በቂ ዩኒቨርሲቲ አለ ሳይሆን 12ኛ ለሚያጠናቅቁ ለማለት ነው፡፡ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ዩንቨርሲቲ የመክፈት ወይም ወደ ዩንቨርስቲ ማሳደግ እቅድ የለንም፡፡
ግዮን፡– ከሌሎች መሠል ዓለም አቀፍ ይሁን ሀገር አቀፍ የዘርፉ ተቋማት ጋር ያላችሁ የልምድ ልውውጥስ ምን ይመስላል?
አንተንሳይ፡- እንዲህ ዓይነት ተግባራትን ብዙ ግዜ አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ት/ቤቶች አይሲኤስ ከሚባል የአሜሪካ ትምህርት ቤት ጋር ልምድ ተለዋውጠናል፡፡ ት/ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስታንዳርድ ያለው ነው፡፡ ለዚህ ት/ቤት ባለፉትም ዓሠርት ዓመታት ሰባት ተማሪዎችን ስኮላር በማሳለፍ ትምህርት ቤታችንን ቀዳሚ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ የሚገኝ አፍሪካ ሊደር ሺፕ አካዳሚ ከሚባል ት/ቤትም ጋር ከፍተኛ ግንኙነት አለን፡፡ ወደዚህ ትምህርት ቤትም በስኮራልሺፕ ብዙ ተማሪዎችን አሳልፈናል፡፡ ከኮቪድ ወዲህ እንዲሁም ከጸጥታው ጋር በተገናኘ በርካታ ተማሪ ወደ ውጪ ይሄዳል፡፡ በዚህም ከተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ጋር በተማሪዎቻችን ጉዳይ ብዙ መረጃ ልውውጦች እናደርጋለን፡፡
ግዮን፡- በአዲስ አበባ በቅርቡ የተጨመረውን የቋንቋ ትምህርት በተመለከተ ትምህርት ቤታችሁ የገጠመው ተግዳሮት ነበር?
አንተንሳይ፡- ይህን በተመለከተ በእኛ ት/ቤት የገጠመን ችግር የለም፡፡ ሌሎች የግል ት/ቤቶች ውስጥም ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ የገጠመ ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገሩ የመጣው አፋን ኦሮሞን እንድናስተምር ዓመቱ አጋማሽ ላይ መመሪያ ተላለፈልን፡፡ በእርግጥ ላለፉት በርካታ ዓመታት ት/ቤታችን ዘወትር ቅዳሜ ጠዋት አፋን ኦሮሞ፣ ግዕዝና ፈረንሳይኛ ለሚፈልጉ ተማሪዎች ሲያስተምር ስለነበር በቂ ልምድ ነበረን፡፡በዚያ መሠረት እኛም ከያዝነው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ አፋን ኦሮሞን በ3ኛ እና 4ኛ ክፍል ደረጃ እያስተማርን ነው፡፡፡ እኛም ውጪ የሚወራውን ስለምናውቅ ከወላጆች በኩል ምናልባት ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል ብለን ጠብቀን ነበር፡፡ ሆኖም ይህን በተመለከተ ከእኛ ት/ቤት ከወላጆች በኩል የተነሳ ምንም ዐይነት ቅሬታ ወይም ጥያቄ የለም፡፡ስገምት ወላጆች ተጨማሪ ሀገራዊ ቋንቋ አስፈላጊ መሆኑን ስለሚረዱ ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካ መልክ ሲሰጠው አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው፡፡ እኛ እራሳችን አንዳንድ ሀገርኛ ቋንቋዎችን አለመቻላችን በጣም ያስቆጫል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት ሦስት ሀገርኛ ቋንቋ ገኖ ቢወጣ የእርስ በእርስ ግንኙነት ይጨምራል፣ ሀገራዊ አንድነትንም ያመጣል፣ ለንግድ መቀላጠፍም የራሱ ሚና ይኖረዋል፡፡ ስለዚህም ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ለመሥራት ይቻል ነበር አላለሁ፡፡ የግል ምልከታዬ ነው፤ ለምሳሌ የአ/አ የስራና የትምሀርት ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ አፋን ኦሮሞን ተማሪዎች በግዕዝ ፊደል ቢማሩት የበለጠ የመማር ፍላጎት እና ውጤት ያመጣል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ይሄ ደግሞ አዲስ አበባ ብቻ ሳይኾን በሌሎች ክልሎች ቢደረግ ትምህርቱን የበለጠ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ መግባባትና ስምምነት እየጨመረ ሲመጣ ወደፊት መኾን የሚችል ይመስለኛል፡፡
ግዮን፡- አንዳንድ የግል ት/ቤቶች ላይ ችግሮች ሲፈጠሩ ሁሉንም የግል ት/ቤች የመውቀስ ነገር ይታያል፡፡ በዚህ ዙሪያ አንተ ያለህ ሐሳብ ምንድነው?
አንተንሳይ፡- ይሄ በጣም የተለመደ ነገር ነው፡፡ በእርግጥ ነው በርካታ ችግር ያለብን የግል ት/ቤቶች አለን፡፡ ሆኖም ሁሉንም በጅምላ መፈረጅ የተለመደ አካሄድ ሆኗል፡፡ በተለይ ሚዲያ አካባቢ ያሉ ሰዎች የግል ት/ቤትን ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ያራግባሉ፡፡ ልጆቻቸው በግል ት/ቤት የሚማሩ ስለመሆኑ መገመት አይከብድም፡፡ በመሆኑም ሚዲያውን ተጠቅመው ነው ባልተገባ ደረጃ ችግሮቹን የሚያራግቡት፡፡ የግል ት/ቤቶች ባይኖሩ የመጀመሪያ ተጎጂው ወላጅ ነው፡፡ እርግጥ ነው ጥቂት የማይባሉ የግል ት/ቤቶች ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ ያልተገቡ ነገሮችን የሚያደርጉ አሉ፡፡ ጨምረው የሚያስተምሩት ትምህርት ዓይነት ላይም መሠረታዊ ችግር ያለባቸው “ጆርጅ ዋሽንግተንን የኛ ጀግና” እያሉ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ተማሪና ቤተሰብ ላይ አላፈላጊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ በተለይ ሳሙና ሶፍትና መሰል ነገሮችን “አምጡ” የሚሉ ት/ቤቶችም አሉ፡፡ እራሳቸውን በደንብ ሳያደራጁ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስከፍሉ ት/ቤቶችም አሉ፡፡ ግን ደግሞ ጥፋተኞቹን ነጥሎ እራሳቸውን የሚያስተካክሉበት መንገድ መቀየስ ቢቻል መልካም ነው፡፡ የግል ትምህርት ቤቶችን በአጠቃላይ መፈረጅ ሁሉንም ተጎጂ ያደርጋል፡፡
ግዮን፡- የትምህርት ቤት ክፍያ የወላጅን አቅም ያላገናዘበ ነው የሚሉ አካላት አሉ፡፡ የአንተ መልስ በዚህ ላይ ምንድነው?
አንተንሳይ፡- አንድ አገልግሎት ዋጋው የሚወስነው በተቋሙ ወጪዎች ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግስት በሚያወጣው መመርያ መሰረት የሚከወን ነው፤ በተለይ ከግዜ አኳያ፡፡ በጣም የሚያስገርመው አዲስ አበባ ላይ በዓመት 300ሺ 400ሺና ከያዚ በላይ የሚያስከፍሉ የግል ት/ቤቶች አሉ፡፡ በተቃራኒው በዓመት ከ15-20 ሺህ የሚያስከፍሉ አሉ፡፡ ሌሎችም በነዚህ ማሃክል ያሉ አሉ፡፡ እነዚያ ከፍተኛ ዋጋ የሚስከፍሉ ት/ቤቶች ውስጥ የሚማሩ በርካታ ተማሪዎች ኢትዮጵውን ናቸው፡፡በእነዚህ ት/ቤቶች ላይ የመንግሥት ቁጥጥር የለም ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ካሪክለማቸውን፣የክፍያቸውን፣ የአካዳሚክ ካላንደራቸውን ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ አንድ ከፍተኛ የመክፈል አቅም ያለው ወላጅ/ቤተሰብ ልጁ የሚማርበትን ሁኔታ(የትምህርት አይነቶች፣ የእረፍት ግዚያት ወዘተ) የመምረጥና የመወሰን የተለየ ነጻነት አለው ማለት ነው፡፡፡ በመደበኛው የግል ት/ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው የሚማሩበትን ሁኔታ የሚወስንላቸው መንግስት ነው ማለት ነው፡፡
በት/ቤት ክፍያ ጉዳይ ወላጆች ቢማረሩ አይገርምም፡፡ ምክንያቱም የት/ቤት ክፍያ የአንድ ቤተሰብ ቋሚ ወጪ በመሆኑ ከአጠቃላይ የቤተሰቡ የኑሮ ደረጃ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሆኖም ት/ቤቶች በሃገር ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት ሰለባዎች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ እየተደረገ ያለው የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በመንግሥት ትምህርት ቤት በነፃ ስለተማርን በትምህርት አገልግሎት ክፍያ መክፈል ጉዳይ ሲከብደን ይታል፡፡ ስለዚህ የኋላ ታሪክ ጉዳይም ይይዘናል፡፡ ከፍ ብለን ካሰብነው ግን ትምህርትም በገንዘብ የሚገዛ አገልግሎት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ ስንታመም የግል ሆስፒታል ሄደን ስንታከም የአገልግሎት ክፍያውን መክፈል ግዴታችን ነው፡፡ ካልተመቸን እና ከተወደደብን ወደሚቀንሰው እንሄዳለን፡፡ የግል ምርጫችን ነው፡፡ የጤና አገልግሎት ክፍያን የሚቆጣጠር የመንግሥት አካል ግን የለም፡፡ ከዚህ አኳያ ትምህርት ከጤና አይቀድምም፡፡ ትምህርት ከጤና በኋላ ነው መምጣት ያለበት፡፡ ሌላው የግል ት/ቤቶች የክፍያ ማስተካከያ እንዳያደርጉ በከተማ መስተዳድሩ በተጣለው ክልከላ ምክንያት ት/ቤቶች ለ24 ወራት (ከመስከረም 2014-ነሃሴ 2015) ገቢቸው አልጨመረም፡፡ተጨማሪ ተማሪ በመቀበል ገቢያቸውን ማሳደግ አይችሉም ምክንያቱም ማስተማር የሚፈቀድላቸው የተማሪ ቁጥር በመንግስት የተወሰነ ነው፡፡ሆኖም በነዚህ 24 ወራት የዋጋ ግሽበቱ የት እንደደረሰ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ባጠቃላይ ከገብያው አኳያ ዝቅተኛ፣መካከለኛ እና ከፍተኛ ዋጋ የሚስፈክሉ ት/ቤች ስላሉ ይሄኛው ውድ ነው ይሄኛው ተመጣጣኝ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ተጠቃሚው መርጦ እንደአቅሙ መገልገል ያለበት ይመስለኛል፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻም ማተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለህ እድሉን ልስጥህ?
አንተንሳይ፡- ማለት የምፈልገው የትምህርት ጉዳይ መሠረታዊ ነው የሚለውን ነው፡፡ የሀገሪቱ እድገት የሚመጣው በወታደራዊ አቅም ወይም በፖለቲካ ራዕይ ወዘተ ሳይሆን በተማረ የሰው ኃይል ነው፡፡ አጠቃላይ የሀገሪቱን መፃኢ ዕድል የሚወስነው በትምህርቱ ጥራት ነው፡፡ ይሄ በኤሲያ ሀገራት በነታይዋን፣ በኮርያ፣በጃፓን ወዘተ በትክክል ታይቷል፡፡ ለዚህ ቁልፍና መሠረታዊው ነገር እስከዛሬ ሲኬድበት የነበረውን የትምህርት ፖሊሲ ውድቀቱን በትክክል ተረድቶ አፋጣኝና ወሳኝ ለውጦችን ማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያውና መሠረታዊው ነገር መምህር ነው፡፡ መምህራን በትምህርቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት ወሳኞች ናቸው፡፡ ጥራት ያለው መምህር እንዲኖር ማድረግ የቅድሚያ ቅድሚያ መኾን ይኖርበታል፤ የሥራ ባሕሉም መቀየር ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ የገዢው ፓርቲ መዋቅር ከላይ እስከታች የተሞላው በቀድሞ መምህራን ነውና ለሙያቸው ወገንተኝነታቸውን ለማሳየት አሁን ወቅቱ ነው እላለሁ፡፡
ከዚህ ሌላ የመንግስት ት/ቤቶችን አቅም በወሳኘ መልኩ በማሳደግ የድሃው ልጅ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኝ በማድረግ መፃኢ ህይወቱ የተሻለና ተወዳዳሪም እንዲሆን ማስቻል የማህበራዊ ፍትህ መገለጫ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ውስጥ ሆኖ እየተቸገሩ ያሉ በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በመንግስት ት/ቤቶች በነጻ በማስተማር ለግል ት/ቤት የሚከፍሉትን ገንዘብ ለሌሎች የቤተሰብ ወጪዎች እንዲሉ ያስችላል፡፡ እኔ የፖሊሲ ቀራጭ ብኾን መጀመሪያ የማደርገው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚባከነውን ሀብት መልክ ለማስያዝ ትክክለኛ አመራር እመድባለሁ፡፡የመምህርና የኃላፊዎችን የሥራ ባሕል የሚቀየር እርምጃ እወስዳለሁ፡፡ በግል ት/ቤቶች ደግሞ የተሻለ የሥራ አፈፃፀም እንዳለ እሙን ነው፡፡ ይህን አጠናክሮ በማስቀጠል በመምህራን ብቃት ላይና በቴክኖሎጂ ታግዞ ማስተማር ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተማሪዎች ሥነምግባር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በመሥራት የተሸሉ ዜጎችን ማፍራም ያስፈልጋል፡፡
ከትምህርት ቤታችን አንፃር ማተላለፍ የምፈልገው ሃሳብ ደግሞ ትምህርት ቤታችን ሂል ሳይድ 25 ዓመት ባልተቋረጠ እድገት እዚህ ደርሷል፡፡ የፖሊሲ ሁኔታዎቹ ከፈቀዱ በቀጣዩቹ ዓመታት በጥራት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በመስራት ት/ቤታችንን ቀዳሚ የከተማችን ተመራጭ ት/ቤት ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ት/ቤታችን ባለፉት 7 ዓመታት ሁለት ግዜ በአዲስ አበባ ደረጃ በአንደኝነት መመረጡ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ሆኖናል፤ለበለጠ ስራም አነሳስቶናል፡፡ ከዚህ በበለጠ ብዙ ርቀት ለመሄድ በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ይህንን ለማሳካት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብም ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን፡፡
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡
