የግድቡ ሙሌት፤ መብረቃዊ ጥቃት የኾነባት ግብጽ!

Date:

የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ፣ የሀገሪቱ ብዙኃን መገናኛዎች፣ የማኅበራዊ ገጾቻቸው አዝማቾች ሰሞኑን ደረሰብን ካሉት መብረቃዊ ጥቃት ጥቂት ቀደም ብሎ “ተስፋ” የጣሉበትን አንድ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኹነት ሲከታተሉ ሰንብተዋል፡፡ ይኸ ፖለቲካ ኹነት ሁሉም እንደሚገምተው በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ኹነት ጋር የተያዘ ነው፡፡ “የትግራይ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ድል አደረጉ” የሚል አርዕስት ያለው ዜና ሲቀባበሉ መሰንበታቸው፣ ኢትዮጵያ በተረጋጋ ቁመና ኹለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ታከናውናለች የሚለው ሥጋታቸውን ያለዘበላቸው ይመስል ነበር፡፡

ነገሩ ኹሉ ግን ከቀናት በላይ መሻገር አልቻለም፡፡ አንድ ዱብ ዕዳ ሰማን አሉን፡፡ ከባለቤቶቹ ከኢትዮጵያውያን ቀድመው “የሕዳሴውን ግድብ ኹለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወን መጀመሯን ኢትዮጵያ በስልክ ሹክ ብላናለች” አሉ፡፡ ማለዳውን Egypt Daily News, Al-Ahram online, Egypt Independent, Egyptian Streets, The Middle East Observer, Egyptian Mail እና ሌሎችም ሚዲያዎች መርዶውን አስተጋቡት፡፡ ኢትዮጵያውያንም ለውለታቸው አመስግነው ደስታቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሲያስደነብራቸው በሰነበተው `IT_IS_MY_DAM` ሃሽ ታግ ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያ የኹለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትን በይፋ መጀመሯን ተከትሎ አስገራሚ ዘገባን ያስነበበው ግን ዘ-ጆርዳን ታየምስ የተሰኘው ጋዜጣ ነበር፡፡

ጋዜጣው በአስደማሚ ኃይለ ቃል “ዓባይ ግድብ ውሃም ኤሌክትሪክም ተሸካሚ ‘ቦምብ’ ሆነ” ብሏል፡፡ ጋዜጣው ይኽን ካለ በኋላ ባስከተለው ዘገባ አፍሪካ ውስጥ የግብፅን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲን የፖለቲካ አካሄድ የሚረዳው መሪ ዐቢይ አሕመድ ብቻ ነው ሲል አግራሞቱን ገለጸ። አያይዞም “ሕዝቡ የሰጠውን ቃል ሳይበላ … ሀገር ውስጥ ያለው የውጭ ጫናና ማስፈራሪያ ሳያሸንፈው፣ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ፈፅሞ ለኢትዮጵያውያን ታማኝነቱን አረጋግጧል” ሲል የሲአይኤ ጉምቱዎች ይዘውሩታል የሚባለውና ትልቁ የመካከለኛው ምሥራቅ ጋዜጣ የኾነው ዘ-ጆርዳን ታየምስ በግብጽ አልቦ ፉከራ ላይ እስኪበቃው ተሳልቋል፡፡

ይኽ በእንዲህ ይኹን እንጂ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሩን ተከትሎ ግብፅ የተለመደው ማስፈራሪያዋን ከማወጅ አልተቆጠበችም፡፡ የኢትዮጵያን እርምጃ በጥብቅ እንደምታወግዝ በመግለጽ፣ የግድቡ ሙሌት የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት በእጅጉ እንዳያናጋው ከፍተኛ ስጋት እንዳላት አስታውቃለች፡፡ ሱዳን በበኩሏ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ሙሊት መጀመሯን ማሳወቋን ተከትሎ “በሱዳን ላይ ሊደርሱ ይችላሉ” ያለችውን ተዛማጅ ጉዳቶች ለመቀነስ ሥራዎችን ለመስራት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኗን የሕዳሴ ግድብን የሚከታተለው የሱዳን ከፍተኛ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ ይህ የሱዳን ሃሳብ የኢኮኖሚስቱ አብደላ ሀምዶክ እንደኾነ ቢጠረጠርም የውጭ ጉዳዩዋ መርየም ሳዲቅ ግን የግብጽን ጩኸት ከማስተጋባት ጋብ ማለት አልፈለገችም።

ከዚህ በተጨማሪ የዐረብ ሊግ የዓለምን ሰላምና የዐረብ ሕዝቦች ሊያናጋ ይችላል ያለውን የኢትዮጵያን እርምጃ ለማስቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታው ም/ቤት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፏል። የጸጥታው ም/ቤት በግድቡ ዙሪያ ሦስቱ ሃገራት አለመግባባታቸውን በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ተወያይተው እንዲፈቱ ምክረ ሃሳብ ከመሥጠት የዘለለ “አንተም ተው፣ አንችም ተይ” የማለት ሥልጣን እንደሌለው በተደጋጋሚ ገልጾዋል፡፡ ኾኖም ጫናው የበረታበት ተመድ ሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ዳግም በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት አምባሳደሮች፣ መልዕክተኞች እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮችም  ገና ከሳምንት በፊት አንስቶ ኒውዮርክ ከተማ ከትመው ሲዶልቱ ነበር፡፡ የተመድ ቀጠሮ ለግብጽ ተስፋ ጭሮ የነበረ ቢኾንም ኢትዮጵያ “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” በሚለው መርኅ መሠረት ቀድማ የውሃ ሙሌቱን መጀመሯን ለተፋሰሱ ሀገራት ይፋ ማድረጓ የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ ሳይቀር ሲገፉትና ሲንቁት ወደነበረው አፍሪካ ሕብረት ጉዳዩን ዳግም አጀንዳ አድርጎ ለመወያየት ፍላጎት እንዳላቸው እስከመግለጽ አድርሷቸዋል፡፡

ይኽም ኾኖ ግብጽ አሁንም የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር ጥረት ማድረጓን አላቆመችም፡፡   ለአብነትም ባተሌው የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ ኹለተኛው የውሃ ዙር ሙሌት ተከናወነ በተባለ ሰዓታት ውስጥ ከደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋልና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ተወካዮች ጋር ተገናኝቶ በጉዳዩ ዙርያ ለማግባባት መሞከሩን የተለያዩ የዜና ወኪሎች ገልጸዋል፡፡ ግራ የገባት ሱዳንም ብትኾን ወደዚህ የግብጽ አዙሪት ከመግባት የምትታቀብ አይመስልም፡፡ ምንም እንኳን ይኅ ስንኩል ጥረታቸው የተለመደና አዲስ ነገር የማያመጣ ቢኾንም የመንግሥትን ጥብቅ ክትትል እንደሚሻ ግን አያወላዳም፡፡

ከዚህ በተለየ ግን ግብጽ ያለሃፍረት ለዓለም የምትከፍተው አዲስ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንደሚኖር ተገንዝቦ ነቅቶ መጠበቅ ይገባል፡፡ “የግደቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመር የግብጽ አካክሲዮን ገበያ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉ ተገለጸ” የሚለው የሰሞኑን ዜና ደግሞ ለዚህ ጥሩ አባሪ ነው። ዜናው የግብጽ ዋና የአክሲዮን ገበያ መረጃ ማክሰኞ ዕለት ሁለት በመቶ ያህል የቀነሰ እንደኾና ለዚህም ምክንያቱ ሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መጀመሩ እንደኾነ ለዓለም ተዘግቧል። የስሪ ዌይ ብሮከሬጅ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ራኒያ ያኩብ “የሚከናወኑት የባለሀብቶች ግብይቶች የፍርሃት ናቸው። ከሕዳሴው ግድብ [የውሃ ሙሌት] በስተቀር ለውድቀቱ ሌሎች ምክንያቶች የሉም” ማለታቸውም የሰዎቹ የስብዕና ቆዳ ምን ድረስ ተሸጦ እንደተበላ ይናገራል።

የሚገርመው ነገር ከአንድ ቀን በፊት ኢትዮጵያ ዘንድሮው የምታደርገው ሁለተኛ ሙሌት የውሃ መጠን በምታገኘው የክረምት ዝናብ ላይ እንደሚወሰን የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ መሐማድ ጋኒም ለአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ መናገራቸውን እና “በአሁኑ ወቅት ላይ በናይል ምንም አይነት ለውጥ አናይም። ልዩነቱን ከአንድ ወይም ከአንድ ወር ተኩል በኋላ የምናየው ይሆናል” ማለታቸውን አስታውሰን የግድቡ ኹለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተጀመረ መባሉን ተከትሎ “የግብጽ አካክሲዮን ገበያ ተቀዛቀዘ” መባሉን ስንደምርበት እርኩሰታቸው የት ሊደርስ እንደሚችል እንረዳለን፡፡

በተመሳሳይም እንዲሁ አልጀዚራ “ግድቡ ኹለተኛው ዙር የውሃ ሙሌቱ ተጀመረ” በተባለበት ዕለት በሰራው ዘገባ በሱዳን ምዕራባዊ የኮርዶፋን ግዛት በጣለው እጅግ ከባድ ዝናብ ኮሒ (Khoi) ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በውሃ ሙላት ተጥለቅልቆ አካባቢው ወደ ጊዜያዊ ሃይቅነት ተቀይሯል፡፡ ሱዳን በግድቡ ሙሌት ሳቢያ የውሃ እጥረት እንዳይገጥመኝ ስትል የነበረው ሥጋት “በውሃ ጎርፍ ሀይቅ ፈጠርሁ” ወደሚል “ደስታ” መቀየሩ ተጨማሪ አጃኢብ ነው፡፡ ሀገራቱ (ግብጽና ኡዳን) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዲፕሎማሲ አክሮባት ፖለቲካዊ ባሕላቸው እየኾነ መምጣቱ ግልጽ ቢኾንም ፈጣሪ እና ተፈጥሮ ግን ከኢትዮጵያ ጋር መተባበራቸውን እስካላቆሙ ድረስ የሚገቱት አንዳች ነገር እንደሌለ ታሪክ መዘገቡን ቀጥሏል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...