ጣናነሽ ሁለትን ከጅቡቲ እስከ ባሕር ዳር ድረስ በመኪና እድትጓዝ የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው ? ብዙ ኪሎሜትር በየብስ ላይ ተጉዛ እንድትሄድ መደረጉን በማስመልከት የተነሱ የአዋጭነትና አንዳንድ ጥያቄዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ምላሽ ሰጥተዋል ።
የጀልባዋን አካላት ለትራንስፖርት በሚመች መልኩ ለያይቶ በማምጣት በሀገር ውስጥ መገጣጠም አይቻልም ነበር ወይ ?
ይህን አይነት ትላልቅ ጀልባዎችን አካላትን መገጣጠም የሚችል በሙያው የሰለጠነ የሰው ሀይል ባለመኖሩ ይህ መሆን እንዳልቻለ ተናግረው የደኅንነት ችግር እንዳይገጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባ በመኪና ማጓጓዙ ተመራጨ መሆኑን ተናግረዋል ።
እንዲህ ያለው ተሞክሮ በመሬት በተከበቡ ሌሎች ሀገራትም ትላልቅ ጀልባዎችን ዲዛይን አድርገው ከሰሯቸውና በሙያው ልዩ ስልጠና ከሌላቸው ባለሙያዎች ውጭ ዳግም ለመገጣጠም በሚሞከርበት ወቅት ከጀልባዎቹ ውስብስብ አሰራር አኳያ ትልቅ ብልሽት ያጋጥማል ።
የጀልባ አካላትን ለያይቶ ማምጣትና ገጣጥሞ በጥቅም ላይ ማዋል የአገልግሎት ዘመናቸውን ከማሳጠርም ባለፈ ለትልቅ አደጋና ብልሽት የሚዳርግ እንደሆነ አስታውቀዋል።
እንደ ስዊዘርላንድ ባሉ የሰለጠኑ ሀገሮችም ትላልቅ የትራንስፖርትና የቱሪስት ጀልባዎችን ክፍሎች ለያይቶ ከማምጣት ይልቅ በየብስ ትራንስፖርት አጓጉዘው አገልግሎት ወደሚሰጡበት የውሀ አካል መውሰድ ተመራጭ ነው።
ይህም ሲሆን ከረጅም ጊዜ አገልግሎት አኳያ፣ ከፍተኛ የዘርፉ አማካሪዎች ለረጅም ጊዜ የአዋጭነት ጥናት ተደርጎ እና ከአለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር ጀልባዋ በየብስ ተጓጉዛ ወደሚፈለገው ቦታ እንድትደርስ ተወስኗል።
በቀጣይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚያካልላቸው የውሀ ክፍሎች፣ በባሮ ሀይቅ ላይ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አነስተኛ ጀልባዎችን ለማሰማራት ዕቅድ አለ።
ይህንንም በስፋት ለማድረግ እንዲቻል ቀላል ጀልባዎችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችል ማዕከል እንደሚከፈትና ባለሙያዎችንም ከሀገር ውጭ አሰልጥኖ በማምጣት በዘርፉ እንዲሰማሩ ይደረጋል።
ይህ እስኪሆን ድረስ ግን በተለይ እንደጣናነሽ አይነት ዘመናዊ እና ግዙፍ ጀልባዎችን ለማጓጓዝ ያለው አማራጭ በየብስ አሁን እየተደረገ እንዳለው መሆኑ የጠቆሙት አቶ ደምስ ወደፊት ግን በዚህ ዘርፍ ያለውን የሀገር ውስጥ አቅም ለማሻሻልና ለማሳደግ እንደታሰበ ነው።
ምንጭ:- ኢቢሲ
