የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አፍሪካ የዓለም የታሪክ መድረክ ዋና ተዋናይ እየሆነች መምጣቷን በመግለጽ፣ ያለ አፍሪካ ንቁ ተሳትፎ ጣሊያንም ሆነች አውሮፓ ብሩህ የወደፊት ተስፋ ሊኖራቸው እንደማይችል ገለጹ።
በንግግራቸው አህጉሪቱ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ የእርሻ መሬት እና ወሳኝ የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ ጣሊያን በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል እንደ ድልድይ ሆና ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በተለይም ወጣቶች በቴክኖሎጂ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ እንዲሰለጥኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም የአፍሪካን ተሰጥኦ ወደ ውጭ ከመውሰድ ይልቅ በአህጉሪቱ ውስጥ እንዲያድግ የሚያደርግ አዲስ የልማት ሞዴል እንደሆነ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው የመኖር እና የመሥራት ነፃነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ወጣቶች በስደት ሀገራቸውን ሲለቁ የሚፈጠረውን የታሪክ እና የባህል ክፍተት ለመሙላት ጥራት ያለው ትምህርት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ጠንካራ የኢንዱስትሪ ትብብር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ስደትን እንደ ብቸኛ አማራጭ ማየት “ራስ ወዳድነት” መሆኑን የጠቀሱት ሜሎኒ፤ የማይቻለውን ነገር በትብብር ወደ እውነት ለመለወጥ እና ዓለምን ለማስደመም ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ “ሁልጊዜም ከአፍሪካ አዲስ ነገር ይገኛል” የሚለውን ጥንታዊ አባባል በመጥቀስ ለአዲሱ የአጋርነት መንፈስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
