ዜናዬነህ ግርማ፣ ከተመሠረተ ከ10 ዓመታት በላይ የኾነው የ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በግዮን መጽሔት ቁጥር 215 ዕትም በነበራቸውም ቆይታ በወጣቶች ላይ በተለያዩ የዐቅም ማጎልበቻ ሥራዎችን በመሥራት እንዲሁም በባሕል በማንነት ዙርያ የለውጥ አራማጅ እንዲኾኑ በማብቃት ረገድ ድርጅታቸው ምን ያህል ውጤታማ ተግባራት እንዳከናወነ አስረድተው ነበር፡፡
የሥራቸውን አድማስ ወደ ተለያዩ ክልሎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማስፋትም፣ ወጣቶችን በትምህርት፣ በተለያዩ ክህሎት ሥልጠና በመሥጠት፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ራሳቸውን በመቻል የበቁ ኾነው የሚወጡባቸው ድጋፎችን በተቋማቸው በኩል ማከናወናቸውን፣ ለዚህ ትጋታቸውም እርሳቸውም ኾኑ ተቋማቸው በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ፣ በርካታ ሽልማቶችና ዕውቅናዎችን ማግኘታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
አሁን ደግሞ ድርጅታቸው ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› በመጪዎቹ ዐሥር ዓመታት የሚተገበር፣ የትኩረት ማዕከሉንም በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በሚገኙ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 35 ዓመት በገጠር በከተማ በትምህርትና ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ወጣቶች ላይ ያደረገ መሪ ዕቅድ (ስትራቴጂክ ፕላን) ይፋ አድርጓል፡፡
ለመኾኑ ይኽ በብዙ መልኩ አምራች የሚባለውን የማኅበረሰብ ክፍል ለመለወጥ የተነደፈ ዕቅድ ምን ምን ይዘቶችና ግቦች አሉት ስንል ከድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዜናዬነህ ግርማ የሚከተለውን ቆይታ ከግዮን ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር አድርገዋል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- የድርጅታችሁ ያለፈው የ10 ዓመት እቅድ አፈጻጸም እንዴት ነበር?
ዜናዬነህ፡- ድርጅታችን ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎመንት ፋውንዴሽን›› ላለፉት 12 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ ወጣቶች ላይ በሁለንተናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲሠራ ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ በአካባቢ ጥበቃና በጤና፣ በንቁ ዜጋና በዘላቂ ሰላም ማስፈን እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ስንሠራ ነበር፡፡
ተቋማችን ያለፉትን ከ10 ዓመታት በላይ በርካታ ምዕራፎችን አልፎ አያሌ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በእኛ የለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ ለተቋቋመበት ዓላማና ተልዕኮ ከሞላ ጎደል ግቡን አሳክቷል ማለት ይቻላል፡፡
አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወጣቶች ሁለንተናዊ የዕድገት ፓኬጅ አዘጋጅተን ምን እየተሠራ ነው የሚለውን ጥናት በማድረግ ለቀጣዩ 10 ዓመታት የሥራችንን መሪ እቅድ ይዘን መጥተናል፡፡
ግዮን፡- የ10 ዓመት መሪ እቅዶቹ ምን ምን ናቸው? በዕቅዱ የተካተቱት ማኅበረሰብና የእድሜ ክልልስ የትኛው ነው?
ዜናዬነህ፡- በመጀመሪያ የድርጅቱን ተልዕኮ ለማስፈጸም ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ዋናው መሪ እቅድ ማዘጋጀት ነው፡፡ ለዚህ መሪ እቅድ፣ ድርጅቱ በእለት ተዕለት የሚያከናውናቸውን እንቅስቃሴዎች፣ በፕሮጀክትና በፕሮግራም የሥራ ድርጊት ክንዋኔዎች፣ ለተልዕኮው መሳካት እንቅስቃሴውን ማጤን አለበት፡፡
ድርጅታችን ከእኛ ጋር ለተመሳሳይ ዓላማና ተልዕኮ የሚያግዙን ተቋማት ወይም ድርጅቶች እነማን ናቸው? በሀገሪቱ ከሁሉም ዐይነት ወጣቶች ጋር በምን ዓይነት መልኩ እንሠራለን? የሚሉትን ጉዳዩች ጥናት አድርጎ ነው ወደዚህ እቅድ የገባው፡፡
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወጣቶች በሚሰጠው ትኩረትና አቅጣጫ መሠረት ምን መሠራት አለበት? ከችግርና እጥረት አኳያም፣ ፍላጎትና አቅርቦትን በመለየት ምቹ ሁኔታዎችንና መልካም አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ምን ተሞክሯል? በተቻለ መጠን ፍላጎትን ማሟላትና ዐቅም ማጎልበት የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲሁም ሀብት ማሰባሰብ እንዴት ይቻላል? ከዓለም አቀፍ እርዳታ በተጨማሪ የእነኚህን ተቋማት ተጽዕኖ ተቋቁሞ አገር ውስጥ ካሉ አጋር ተቋማት ጋር በምን ዐይነት ሁኔታ መቀጠል ይቻላል? የሚሉትን ጉዳዮች ሳይቀር ጥናት አድርገንበታል፡፡
ይህ ጥናት ከ2 ዓመት በላይ ፈጅቷል፡፡ የተለያዩ ተሞክሮዎች ከራሳችንና ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ወስደናል፡፡ ይህ መሪ እቅድ ከ2025 እስከ 2035 የሚተገበር እቅድ ነው፡፡ ሦስት መሠረታዊ ምዕራፍችም አሉት፡፡
ግዮን፡- ምዕራፎቹ ምንድን ናቸው?
ዜናዬነህ፡- የመጀመሪያው ምዕራፍ የድርጅቱን ጠንካራ መሠረት በደንብ ማስፋትና ማጠናከር የምንለውና ከ2025 እስከ 2028 የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ተቋሙን ዳግም ያለውን ቅቡልነትና አቅም ማጠናከርና የሚሠራቸውን ሥራዎች ብራንድ ማድረግ ነው፡፡
ሥራዎችን በተሻለ መንገድ ከአጋር ተቋማት ጋር ያለውን ምስስሎሽና አቋም በማጤን ድርጅቱ የሚጠናከርበት ምዕራፍ ይኾናል፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከ2029 እስከ 2032 ያለውን ዓመታት የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ መሪ እቅድ ውስጥ እስካሁን ድረስ ስንጓዝባቸው የመጣናቸውን ሥራዎች በማስቀጠል ወደ ከፍታ ማማችን የምንደርስበት ይኾናል፡፡
ባለፉት 12 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ብናከናውንም አጠናክረናቸው ቢያድጉና ሌሎችም ተቋማት ቢሠሯቸው ጥሩ ናቸው ብለን የምናምንባቸውን 4 ዋና የድርጅታችን ምልክት የሚሆኑ የፕሮግራም (የፕሮጀክት) መልካም ተሞክሮዎችን ለይተናል፡፡
ከዚህም አንፃር በተለይ ወጣት ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና በአመራርነት ለማብቃት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሴቶች ተማሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቀነስ የሠራነው ተግባር፣ በመምህራን ዐቅም ግንባታ ላይ ያከናወነው ተግባር፣ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሠራናቸው ሥራዎች፤ በተለይ ወጣቶች የአካባቢ ጥበቃ ላይ እንዲሳተፉ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ በኩል የተገበርናቸው ፕሮጄክቶች ስኬታማ ነበሩ፡፡
በዚህም በርካታ ዕውቅናዎችን ያገኘን ሲሆን በተጨማሪም ከእንግሊዝ ሀገርም የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተናል፡፡
ስለዚህም በሁለተኛው ምዕራፍ እነኝህን ፕሮግራሞች ከማስቀጠል ባለፈ በማኅበራዊ ዘርፍ በጤና፣ ትምህርት እና ከመጠጥ ውሃ ጋር በተያያዘ ከወጣቶች ጋር የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት አቅደናል፡፡
በተለይ የወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የምናረጋግጥበትን ዕቅድ ይዘን ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በተሻለ መጠን ብንከውናቸው የድርጅታችን የከፍታ ሂደት አሁን ካለው የበለጠ ይኾናል፡፡ ከአጋሮቻችንም ጋር ወደሌላ ምዕራፍ ያሸጋግረናል፡፡
የመሪ ዕቅዳችን ሦስተኛው ምዕራፍ ከ2033 እስከ 2035 የሚዘልቅ ነው፡፡ ይኸውም የድርጅቱን ዘላቂነትና ቀጣይነት ማስቀጠል ነው፡፡
አሁን መንግሥት በፈቀደልን የገቢ ማስገኛና እኛን በሚደግፉ ፕሮግራሞች ዙርያ በተለይ የግብርና ኢንተርፕራይዝ በማቋቋም ገቢ ማስገኛ መንገዶች ላይ እንድንሳተፍ አተኩረን እንሠራለን፡፡
ለዚህ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ጀምረናል፡፡ በድርጅቱ አንድ ጥላ ሥር ሌላ የአግሮ ቢዝነስ ኢንተርፕራይዝ ላይ የምንሠማራበትና በርካታ ወጣቶችም ተጠቃሚ የሚኾኑበትን መንገድ እያመቻቸን ነው፡፡
ይህ አካሄድ የድርጅቱን ዘላቂነት በማስቀጠል በተመሳሳይ ለእኛም ተተኪዎችን እንደ አመራር አብረን የምናፈራበት አካሄድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በዚህ ሂደትም በርካታ ወጣት አመራሮችን ወደ ድርጅቱ በማምጣት የተቋሙን ዘላቂነት እናጸናለን፡፡ ይህ አጠቃላይ ማዕቀፍ ሲኾን በዚህ አቅጣጫ ውስጥ ስድስት ንዑሳን ጉዳዮች አሉ፡፡
ግዮን፡- እነዚህ ስድስት ስትራቴጂያዊ ግቦች ምን ምን እንደኾኑ በዝርዝር ቢያስረዱን? የዚህን እና የሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይዘን ሐሙስ በ11-03-2018 ዓ.ም ይዘን እንቀርባለን ።
