በቀን በአማካይ አምስት የውጭ ሀገር ዜጎች የሆኑ ግለሰቦች፤ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ሲጠቀሙ እንደሚያዙ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ። ሀሰተኛ የቪ አይ ፒ መስተንግዶ ሰነድ በማሰራት ወደ ተቋሙ የሚገቡ ሰዎች እንዳሉም መስሪያ ቤቱ ዛሬ በተካሄደ የፓርላማ የቋሚ ኮሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አመልክቷል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም ለመገምገም፤ ዛሬ ሰኞ ህዳር 8፤ 2018 ስብሰባ የጠራው የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። ሪፖርቱን በንባብ ያቀረቡት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፤ መስሪያ ቤታቸው በሩብ አመቱ 545,491 ፓስፓርት ለዜጎች መስጠቱን ገልጸዋል።
በዚሁ ጊዜ ውስጥ 860 ኢትዮጵያዊን እና የውጭ ዜጎች ሀሰተኛ የጉዞ ሰነድ በማቅረባቸው ተይዘው በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጋቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። ሀሰተኛ የጉዞ ሰነድ ይዘው የሚገኙ ዜጎች በመስሪያ ቤቱ ስራ ላይ “ተጨማሪ ጫና” መፍጠራቸውን የጠቆሙት ሰላማዊት፤ ችግሩ “በየጊዜው እየጨመረ የመጣ” ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

በተቋሙ ሪፖርት መሰረት፤ በሩብ ዓመቱ ውስጥ የተጭበረበረ የጉዞ ሰነድ ሲጠቀሙ የተያዙ የውጭ ሀገር ዜጎች ብዛት 96 ነው። በፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሳዲቅ አደም፤ የውጭ ሀገራት ዜጎችን በተመለከተ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ አሁንም “በርካታ” “ያልተደረሰባቸው” የውጭ ሀገራት ዜጎች እንዳሉ በማንሳት ጥያቄ አቅርበዋል።
እኚሁ የፓርላማ አባል ያለ ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ የመግባትም፣ የመኖርም ሁኔታ መኖሩን “ብዙ መረጃዎች” እንደሚያሳዩ አንስተዋል። “ለምሳሌ ኤርትራዊያን ተብሎ ብዙ ጊዜ ይነሳል” ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ ይህ ጉዳይ እንዲብራራላቸው የመስሪያ ቤቱን አመራሮች ጠይቀዋል።
ኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ፤ የውጭ ዜጎችን የተመለከተውን ጉዳይ ከፋፍሎ ማየት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ህግን ሳይከተሉ “በማይገባቸው አኳኋን የጉዞ እና የይለፍ ሰነድ የወሰዱ”፣ “በህገ ወጥ አግባብ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ” እና “ያለምንም ሰነድ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ እና የሚሰሩ” የውጭ ዜጎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህን በተመለከተ በተቋሙ “የህግ እና የአሰራር ክፍተት” እንደነበር አንስተው፤ በአሁኑ ጊዜ ይህ “መልክ እንዲይዝ” መደረጉን ለምክር ቤት አባላቱ አስረድተዋል። በተቋሙ ያሉ የአገልግሎት አይነቶች እና የቁጥጥር ስራዎች ያለመንገራገጭ (seamlessly) እንዲከናወኑ በማድረግ እና “ሀሰተኛ” እና “የማይገባቸውን” ሰነድ ሚጠቀሙትን የውጭ ዜጎች “እየለዩ” እርምጃ የመውሰድ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህ መልክ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ መጡበት እንዲመለሱ (deport) የማድረግ እና እርምት የመውሰድ እርምጃዎች እንደተወሰዱም አብራርተዋል። “በአማካይ አሁን በቀን አምስት የሚያህሉ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ፣ የኢትዮጵያን ፓስፖርት የወሰዱ የውጭ ዜጎች እናገኛለን” ያሉት አቶ ጎሳ፤ ይህ ሁኔታ “በቀድሞ ጊዜ” የውጭ ዜጎችን ከመቆጣጠር አንጻር “ክፍት ሁኔታዎች” እንደነበሩ የሚሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የተቋሙ 42 ሰራተኞች “በሙስና እና ብልሹ አሰራር” ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት፤ ህገ ወጥ ፖስፖርቶችን መስጠት በክስ መልኩ ቀርቦባቸው እንደነበር አይዘነጋም። የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ የውጭ ሀገራት ዜጎች፣ የፓስፖርት፣ የሊሴፓሴ “አየር በአየር በመሸጥ እና በማስተላለፍ” ተወንጅለው ነበር።

እነዚሁ ሰራተኞች ተመሳሳዩን አገልግሎት “በወንጀል ተከስሰው የጉዞ ሰነዳቸው ለታገደባቸው” እና “ሀሰተኛ የማንነት መገለጫ” ላላቸው ጭምር ይሰጡ እንደነበርም በክሳቸው ላይ ተጠቅሷል። በዛሬው የፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ፤ በበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ሀሰተኛ ሰነድ ያዘጋጁ እና የተገለገሉ ዜጎችን እየለዩ “የመቅጣት” ተግባር መከናወኑን አቶ ጎሳ ተናግረዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ስደተኞችን በተመለከተ፤ በህጋዊ መንገድ በከተማ እና በካምፕ የሚኖሩ እንዳሉ ማስተዋል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። እነኚህ የውጭ ሀገራት ዜጎች የሚያከናውኗቸው ተግባራት፤ ከሀገሪቱ “ደህነንት እና ጥቅም” አንጻር የተስማማ (aligned) እንዲሆን የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል። በህገወጥ ሁኔታ ውስጥ ያሉት ዜጎች ጉዳይ “እየተለየ” ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በዛሬው የፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ የነበረው፤ ተቋሙ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የፓርላማ አባላቱ ራሳቸው “እርካታ የላቸውም” መባሉ ነው። ይህንን ጉዳይ በጥያቄ መልክ ያነሱት፤ በፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አዳሙ ቀንዓ ናቸው።

አቶ አዳሙ የመስሪያ ቤቱን የሩብ አመት ሪፖርት አስመልክቶ በተደረገ ስብሰባ ላይ በተቋሙ አገልግሎት ላይ ቅሬታ እንዳለ ከፓርላማ አባላት መረዳታቸውን ተናግረዋል። የህዝብ ተወካዮች “እምነት” ያላሳደሩበት እና በአገልግሎቱ መርካት እንኳ ያልቻሉበት መስሪያ ቤት ህዝብን ስለማርካት መነገሩ “ትንሽ ቅሬታ ይፈጥራል” ሲሉም ጉዳዩን አብራርተዋል።
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የመስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ፤ በጥያቄው “ቅር” መሰኘታቸውን አልሸሸጉም። የፓርላማ አባላቱ ወደ መስሪያ ቤቱ ሲመጡ መረጃ አስቀድሞ ካልደረሳቸው ወይም ይሄንን የሚገልጽ ሰነድ ማሳየት የማይቻል ከሆነ፤ እነርሱን ከመደበኛው ተገልጋይ መለየት እንደማይቻል አስረድተዋል።
“እውነት ከምክር ቤት የተጻፈ ደብዳቤ ይዘን የተመለስን ሰዎች አለን ወይ? ‘አገልግሎት ፈልገን መጥተን፣ ደብዳቤ ይዘን መጥተን ተመልሻለሁ’ የሚል ካለ፣ ‘ከሆነ ተቋም ደብዳቤ ይዤ መጥቼ ተመልሻለሁ’ የሚል ሰው ካለ ውስጣችን መፈተሽ ይኖርብናል” ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። መስሪያ ቤታቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋም መሆኑ የገለጹት አቶ ቢቂላ፤ “መቶ በመቶ ንጹህ እንዳልሆነ” እና ክፍተት ሲፈጠር እየተሻሻሉ የሚሄዱ ጉዳዮች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት እራሱን የቻለ የቪ አይ ፒ ተገልጋዮች እና ቤተሰቦችም ጭምር የሚስተናገዱበት ቦታ እንዳመቻቸ ያስረዱት አቶ ቢቂላ፤ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የተቋሙ መስሪያ ቤት ሀሰተኛ (fake) የቪ አይ ፒ ሰነድ በማሰራት “መሳሪያ ይዘው” የሚገቡ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። “እኔ እከሌ ነኝ ብሎ መግባቱስ ትክክል ነው ወይ?” ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልሰው የቋሚ ኮሚቴ አባላቱን ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር
