Home ርዕሰ አንቀጽ ዴሞክራሲ ዳግም ‹‹ላም አለኝ በሰማይ…›› እየኾነ ነውን?

ዴሞክራሲ ዳግም ‹‹ላም አለኝ በሰማይ…›› እየኾነ ነውን?

ዴሞክራሲ ዳግም ‹‹ላም አለኝ በሰማይ…›› እየኾነ ነውን?

ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የዛሬ አምስት ዓመት ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት እና የሙያ ተሟጋቾች በኢትዮጵያ ስላለው የሕሊና እሥረኞች እውነታ ያወጧቸው የነበሩ መግለጫዎች እጅግ አስደናቂ ነበሩ፡፡ በመግለጫዎቹ ኢትዮጵያ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ‹‹ምንም ዐይነት የፖለቲካ እሥረኛ የሌለባት ሀገር›› ተብላ መወደሷን ተከትሎም፣ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ ሳይቀር የተቋማቱን ሪፖርት በዐደባባይ አስረጂ አድርገው በማቅረብ የመንግሥታቸው ዴሞክራሲያዊነት ማሳያ አድርገውት ነበር፡፡ ኾኖም ይኽ በፖለቲከኞች፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና በጋዜጠኞች ላይ ጋብ ያለ አፈናና እሥር አንድ ዓመት እንኳን መዝለቅ የቻለ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የ‹‹እርግማን›› ፖለቲካ መኾኑን ሲቀጥል፣ የጅምላ እሥሩም እንደ አዲስ ተቀሰቀሰ፡፡ አስከፊው የአፈና ምዕራፍም ዳግመኛ አሐዱ ተባለ፡፡ ይኽ ኹኔታ ደረጃ በደረጃ ሕገ ወጥ ሥወራንም እየጨመረ ሔደ፡፡

በዚህ ጊዜ የዓለም አቀፍ መብት ተሟጋቾች ድምጽ ጎላ ብሎ መሰማቱም እንደ አዲስ ቀጠለ፡፡ ሒዩማን ራይትስዎች፣ አሚነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ኮሚቴ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ)፣ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች እና ሀገርኛው ኢሰመኮን ጨምሮ በኢትዮጵያ ስለሚፈጸመው የጋዜጠኞች እና የሕሊና እሥረኞች አፈናና እሥር በስፋት መግለጫ መሠጠት ጀመረ ፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ የዚህ አሳፋሪ የቁልቁለት ጉዞ ኢትዮጵያን ተመድን ጨምሮ በዓለም የመብት ተሟጋቾች ፊት ዳግም አስከፊ ገጽታ እንድትይዝ ምክንያት ኾኗል፡፡ ለዚህ ጉልህ አብነት የሚኾነው ከአንድ ሳምንት በፊት በተከበረው የዓለም የፕሬስ ቀን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (RSF) ያወጣው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር (Index) ነው፡፡ በዚህ ዝርዝር ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነጻነት 16 ደረጃዎች አሽቆልቁላ 130ኛ ደረጃን አግኝታለች። ይኽ መረጃ እጅግ አስደንጋጭ ከመኾኑም በላይ ሀገራችን ‹‹ዴሞክራሲ አይውጣልሽ›› ተብላ የተረገመች ያስመስላታል፡፡

ኾኖም የአገዛዙ ሰድዶ ማሳደድ ጋብ ሊል አልቻለም፡፡ መንግሥት መሠረታዊ በሚባሉ የዜጎች ሕልውና ዙሪያ ጥያቄ የሚያነሱና የሚተቹትን ጋዜጠኞች፣ ዛሬም እንደቀደመው ኢሕአዴግ በ‹‹ሽብርተኝነት›› እና ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል መናድ›› በሚሉ አታካች አንቀጾች ዘብጥያ ለመወርወር እየሔደበት ያለው ርቀት፣ ዛሬም በሰላማዊ መንገድ የሚሰነዘሩ ትችቶችን እና የሚነሱበትን ጥያቄዎች በሕግ እና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ለመፍታት ዝግጁነት እንደሌለው ማሳያ ኾኗል፡፡

ይኽንንም የሀገር ቤቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ‹‹በጋዜጠኞች፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በተቃውሞ ድምጾች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት›› መፈጸሙን በማጋለጥ አስታውቋል። ኢሰመኮ ጉዳዩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢነቱ እየጨመረ መምጣቱን እና አስፈጻሚው አካልም ‹‹በጋዜጠኝነታቸው ወይም በሚዲያ ሥራቸው አይደለም ለጥቃት የተጋለጡት›› ብሎ አበክሮ መከራከሩን በመጥቀስም፣ ኹነኛው የአምባገነን መንግሥታት የክህደት መገለጫ አሁን ባለው አገዛዝም ፍንትው ብሎ መታየቱን አስረግጦልናል፡፡

ነገሩ ግን ከዓለም ተቋማት እና ኢሰመኮ ጩኸት አልፎ የመንግሥት ከፍተኛው የሥልጣን አካል እስከመኾንም ደርሷል፡፡ ለዚህ ጉልህ አብነት የሚኾነው ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት ሲገመገም ነው፡፡ በዚህ ግምገማ የፌደራል ፖሊስ ‹‹የፍርድ ቤቶችን ውሳኔዎች እና ትዕዛዞችን አይፈጽምም›› የሚሉ ግልጽ ቅሬታዎች በፓርላማ አባላት ቀርበውበታል፡፡ በተጨማሪም ፖሊስ፤ በፍርድ ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎች እና ትዕዛዞችን ‹‹ያለመፈጸም እና የመንጓተት አካሄድን ይከተላል›› የሚሉ ቅሬታዎችም ተሰምተውበታል፡፡ ምንም እንኳን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለቅሬታዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አለማክበር በተቋማቸው የማይታለፍ ‹‹ቀይ መስመር ነው›› ቢሉም እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒ ለመኾኑ ሕዝብ ሕያው ምሥክር ነው፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት ሺዎች ለዘመናት የታገሉለትን፣ በየጊዜውም የታሰሩለትን እና የሞቱለትን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለማፈን እየሔደበት ያለው ርቀት እጅግ አስጊ በመኾኑ፣ አሁንም የሚመለከታቸው የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ጫናዎችን እና ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል በማለት የሳምንቱን መልዕክታችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡