Home የኢትዮጵያ ደጀን ጀነራሉ ያቺን ሰዓት!

ጀነራሉ ያቺን ሰዓት!

ዘሪሁን ኑሪ

የሬዲዮ ግንኙነቱ ተቋርጧል። የስልክ መስመሮች ድምፅ አልባ ሆነዋል። የከተማው መብራት ጠፍቷል። የወታደራዊ ሬዲዮ ግንኙነት አባላት ግን ጥበብ በተሞላበት መልኩ ከበላይ አመራርጋ የሚያገናኛቸውን ግንኙነት ፈጠሩ።  የሀገሪቷ የጦሩ የሰላ ጫፍ ለይ ያሉ ጄነራል በከበባ ውስጥ ያሉትን አዛዥ ለማነጋገር መስመር ለይ ናቸው። አዛዡ ቀርበው የሬዲዮውን እጀታ ወደ ጆሯቸው አስጠጉ። እጅግ አስገምጋሚ ድምፅ በሞገድ ውስጥ መጣ!

“አዝናለው እንዳለን ወዳጅነት እንደመሪ እና ተመሪ ግንኙነታችን ልባዊ እና ጥልቅ ሰላምታ ለመለዋወጥ የሚሆን ጊዜ የለንም! እስክንደርስለህ ድረስ ባለህ ነገር ሁሉ ተፋለም። ታንኮችህ ቀጥታ ተኩስ እየተኮሱ እንዲሁም የጠላትን ሀይል እየደፈጠጡ አንተ ወዳለህበት ማዘኛ ጣቢያ እንዲመጡ አድርግ። ከዛ ሀይልህን ይዘህ ጎረቤት ሀገር ግባ።” አዛዡ “እሱን አልችልም! ብረት ለበሶቹም ሆኑ ታንኮቹ የሞሉት ነዳጅ እኔ ወዳለሁበት ማዘኛ ጣቢያ አያደርሳቸውም!! ቀድመን የተዘጋጀነው ከፊት እንጂ ከጀርባችን እንወጋለን ብለን አይደለም!!”

“ባሉበት ሆነው ወዳንተ እየተኮሱ ድጋፍ እንዲሰጡህ ማድረግስ አትችልም!?”

ብ/ጄነራል “ክቡር ጄነራል! እርሶም እንደሚያውቁት ዳንሻ ያለንበት ካንፕ በህዝብ መሀል ይገኛል። የመጀመሪያው ጥይት ሲተኮስ ያረፈበትን አይቶ ለማረም ያስቸግራል። ከረዘመም ካጠረም ህዝባችን ለይ ይወድቃል! ያ ከሚሆን ደሞ እኛ ብናልቅ ይሻላል።”

“ካንተ የቅርብ ርቀት ለይ ያሉት ሀይሎች የተሻለ ከፍታማ ቦታ ለይ ስላሉ እራሳቸውን ለመከላከል በቂ ናቸው። ስለዚህ የተወሰነ ሀይል ቀንሰው ወዳንተ እንዲልኩልህ አድርግ❗”

“ጠላት ቀድሞ ተዘጋጅቶበት ስለሆነ ዲሽቃ እና መትረየስ የታጠቀ የተወሰነ ሀይል እንዳንገናኝ እና በተኩስ እንዳንተጋገዝ መሀል ለይ አስቀምጧል። ቢሆንም ግን በትንሽ መሰዋዕትነት የጠላትን ሀይል ሰብረው ወደ እኛ ለመምጣት አሁን ውጊያ ለይ ናቸው። ተሳክቶላቸው ይመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዛ እናንተ እስክደርሱ እራሳችንን እንከላከላለን”

ባለ ብዙ ኮኮቡ ጄነራል ቀጠሉ። “ባንተ የፀና እምነት አለኝ።አሁን ቀጥዬ የምነግርህ መመሪያ ነው። ካንተ ስር ያሉት አባላቶችህ ተስፋ ቆርጠው መዋጋታቸውን እንዳያቆሙ። ጠላት የድል መንፈስ እንዳይላበስ። ለዚህም ሲባል ለአንተ መሞትም ሆነ መማረክ በፍፁም  አልፈቅድልህም። መልካም እድል!” ግንኙነቱ ተዘጋ።

ድጋፍ ለመስጠት የተወሰነ ሀይል ይዘው ይመጡ ከነበሩት ሁለቱ ኮረኔሎች አንዳቸው ቆስለው አንድ ሰው ሰውተው ከግቢው ደረሱ።

አዛዡ የነፍስ ወከፍ ኤኬም ከዘጠና ጥይት ጋር የታጠቁ የእስታፍ አባላትን ይዘው በልበ ሙሉነት ገጠሙ። እንደ ጄነራል አዋጉ፣ እንደተራ ወታደር ተዋጉ‼ የግል አጃቢዎቻቸው እና ሹፌራቸው የታጠቁትን ቦንብ ወደ ተጠጋቸው የጠላት ሀይል ለይ ወረወሩ። ከፊታቸው ከተደቀነው ጠላት ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ከሚወጋቸው ጋ እልህ አስጨራሽ ውጊያ በዛች ጠባብ ግቢ ውስጥ እውን ሳይሆን ፊልም በሚመስል መልኩ አደረጉ። ጥቂት ጓዶች በውጊያው መሀል ቆሰሉ ተሰው። ሀረር እና አለሙን የመሰሉ ጀግኖች እየተፋለሙ በእራሳቸው ጓዶች ከጀርባቸው ተመተው ወደቁ። ሀረር ተመልሶ አልነቃም፡፡

ጀግናው የአማራ ልዩ ሀይል ሶረቃ ለይ የነበረውን ጠላት ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር ደምስሶ ከፊቱ ያገኘውን እየመነጠረ አዛዡ የተከበቡበት ግቢ በአጥር እየዘለለ ገባ። የሞት ሽረት ትግል ለይ የነበሩት አባላት አይናቸውን ማመን አቃታቸው። የአማራ ክልል ልዩ ሀይሎች ከምድር ይፍለቁ ከሰማይ ይዝነቡ እስካሁንም መልስ ያላገኙለት ጉዳይ ነው። ክብር እና ምሥጋና የጦር ሜዳ ውሎ እና ገድላቸው በሽለላ እና በዘፈን ደምቆ ላልተነገረላቸው የአፋር ክልል ልዩ ሀይሎች‼

የምዕራብ ትንታጎቹ

መላክ በቃሉ (ከግዳጅ ቀጣና)

ከጥቅምት 24ቱ የህወሓታዊያን ባንዳዎች የክህደት ጥቁር-ምሽት ጀምሮ ከምዕራቡ የአገራችን ክፍል ወደ ሰሜን የተመሙት የምዕራብ ዕዝ ትንታጎች ከዳንሻና ባዕኸር በመነሳት ቲርካን ላይ የመሸገውን ጠላት  ኩማንዶ ነው ብሎ በሻለቃ ያደራጀውን ሀይል በመደምሰስ የጀመረው ግስጋሴያቸው ኢንዱስትሪ ፓርክን ፣ ሁመራ ፣ ሽራሮ ፣ ሽሬ ፣ ሀውዜን ፣ ውቅሮ እና መቐለን ከጁንታው ሀይል በማፅዳት ወደ ተምቤን ዙሪያ-ገቦች በመፈርጠጥ ዋሻ ገብቶ የተሸሸገውን የጁንታ አመራሮች በማደን ለአፍታ እረፍት ሳያሻቸው ሌት ተቀን ተግተው ወደር የሌለው ጀግንነት በመፈፀም ህዝብ አኑረዋል ፤ አገር አሻግረዋል፡፡

በተከዜ ሸለቆዎችና በተምቤን ጉራንጉሮች በአሸባሪው ህወሀት ተዘርፈው የነበሩ ዲፖዎችንና በዘራፊ ቡድኑ ተወስደውና ተቀብረው የነበሩ መጠነ-ብዙ የአገር ሃብቶችን በማስመለስ ለተቋሙ ገቢ ያደረጉት የምዕራብ ዕዝ ትንታጎች የሽብር ቡድኑ ሴራ ወጣኝ የነበረውን አቦይ ስብሃት ነጋን ጨምሮ የጁንታውን ቁንጮ አመራሮች ከተደበቁበት በማውጣት ለህግ በማቅረብ የፈፀሙት ግዳጅ በደማቅ ቀለም ተፅፎ ለታሪክ ተቀምጧል።

የሽብር ቡድኑ ድል ተነስቶ ወደ ሽምቅ እንቅስቃሴ ቢሸጋገርም የዕዙ አባላት በፀረ-ሽምቅ ተጋድሏቸው ወሳኝ ፍልሚያዎችን አድርገው ጠላትን ድባቅ መተዋል። በሁዋላም በመንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ መሰረት ከተምቤን በየጭላ ወደ ደጀን ሲወጣም ከጁንታው ሀይል እና የጁንታው የአላማ ተጋሪ ከሆነው ሃይል ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ከቀጣናው መውጣት ችለዋል።

ዕዙ ተጨማሪ ግዳጅ በመቀበልም በማይፀብሪ ፣ አዲርቃይ እና በዘሪማ ሾልከው በመግባት ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመፈፀም ያደረጉትን ሙከራ ማክሸፍ ችለዋል። ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ አገራችንን ወደ ታላቅ የእድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለአንዳች እንከን እንዲከናወኑ ተግተው የሚገኙት የምዕራብ ትንታጎች የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድንን አከርካሪ በመስበርም ወደር የላቸውም፡፡ እነሱ እንዳሉት አሁን ሳይሆን ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ የፍርሻ ጋብቻ እንደፈፀሙ ያወጁትን የህወሓትና የኦነግ ሸኔ ቡድኖችን የሴራ ትብትብ ለመበጣጠስ በሚያውቁበት የጀግንነት ብልሃት የፈረጠመ ክንዳቸውን ለማሳረፍ ዝግጁ ናቸው፡፡

መላው የዕዙ አባላት ያላቸው አሁናዊ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና እና ስሜት የዕዙ አባል የሆነው መ/አ ዘሪሁን ኑሪ በቅርቡ ያሰፈረውን አንድ ፅሁፍ ያስታውሳል። “በራሳችን ተይዞ የነበረውን ሰዓት አሻሽለን መቐለ እንገባለን!!” ብሎ ነበር መኮንኑ፡፡ አዎ የምዕራብ ትንታጎች የትህነግ አሸባሪ ሀይሎችን አንገት በመቁረጥ ልክ በመጀመሪያው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ወቅት መቐለን ቀድሞ በመቆጣጠር በራሳቸው ተይዞ የነበረውን ሰዓት በራሳቸው አሻሽለው ከሃዲያንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ቃላቸውም ታድሷል። ትጥቃቸውም ጠብቋል። የሚጠብቁት አንድ ነገር ብቻ ነው – የበላይ አካልን የመጨረሻ ትዕዛዝ፡፡