“ግዮን” የኢትዮጵያውያን የኃያልነት ተምሳሌት

Date:

የኢትዮጵያን ምድር እንደሚከብብ በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የተነገረለት የግዮን ወንዝ ዓመታዊ ክብረ በዓል ያስፈልገዋል፡፡ ዛሬ ላይ የአፍሪካ ብቻ ሳይኾን የዓለማችን የውሃ ፖለቲካ ማጠንጠኛ የኾነው የግዮን ወንዝ መዘከርም ሲያንሰው ነው፡፡ ሲሳይነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው የቀጠናው ሀገራት መኾኑ እሙን ነው፡፡ ይህ ወንዝ ላለፉት ሺህ ዓመታት እየተገማሸረ ኢትዮጵያን ትቶ የበርኸኞች ሲሳይ ኾኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ግን ለእናት ሀገሩም እጥፍ ሲሳይ ለመኾን ተዘጋጅቷል፡፡ ለዘመናት ለዘፈኑለት እና ለተቀኙለት የሀገሩ ልጆች ተገርቶ ሊመግባቸው ወተት ኾኖ ሊጠግናቸው፣ ውሃ ኾኖ ሊያለመልማቸው፣ ጸሐይ ኾኖ ሊያበራላቸው ወስኗል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ወንዝ ይፋዊ እውቅና ባለው መልኩ ዓመታዊ ክብረ በዓል ማዘጋጀት የሚደነቅ ተግባር ነው፡፡

ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ግዮንን አስመልክቶ ኦሪት ዘፍጥረት 2፤13 ላይ የሚከተለውን ይላል፡፡ “የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ኹሉ ይከብባል።” ግዮን ከኤደን የሚመነጭ፣ ገነትን የሚያጠጣ፣ ውኃ ብቻ ሳይኾን ጥበብ የሚፈልቅበት፣ ሥልጣኔ የሚገኝበት፣ ታሪክ የተመላበት ከቀደምት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ቅኔ የሚቀኝለት፣ ታላቅ ወንዝ ነው፡፡ ይህ ወንዝ የኢትዮጵያ የሥልጣኔ፣ የኃያልነት እና የሀብት ምንጭና ምልክት ነው፡፡ አበው “ግዮን” ማለት ምን ማለት እንደኾነ ሲያስረዱ የሚያስፈራ፣ ትልቅ ነጎድጓድ የመሠለ ድምጸት ያለው እንደኾነ ይጠቁማሉ፡፡ አንድም ግዮን ማለት “ዘየሐውር በኃል ወይርዕም ወደምፀ ማዩ ዐቢይ ወግሩም” ማለት ነው ብለው ያክላሉ፡፡

ግዮንን ዓባይ ወይንም ግሽ ዓባይ ብለው የሰየሙት አቡነ ዘርዐ ብሩክ እንደኾኑ ገድላቸው ያስገነዝበናል፡፡ ገድላቸው እንደሚተርከው አቡነ ዘርዓ ብሩክ የንጉሥ ጭፍሮች ሊገድሏቸው ሲያሳድዷቸው ግዮን ወንዝ እንደደረሱ ከጠላቶቻቸው ለማምለጥ የያዙትን ዳዊትና ወንጌል እንዲሁም ስብከተ ወንጌል ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ሰባት መጻሕፍት ሁሉ ለግዮን ወንዝ አደራ  ሰጥተው ሸሹ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ሲመለሱ “ኦ ግዮን ግሥኢ መጻሕፍትየ፤ ግዮን ሆይ መጻሕፍቴን ግሺ /መልሺልኝ/” አሏት፡፡ ግዮንም አንድም የውኃ ጠብታ ሳይኖርባት መጻሕቶቻቸውን መለሰችላቸው፡፡ እርሳቸውም ዘሩፋኤል ለተባለው ደቀ መዝሙራቸው ባሳዩት ጊዜ ከእርሳቸው ጋር አብሮ ያየውን ተዓምርና የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቀ። አቡነ ዘርዐ ብሩክም ግዮንን ባርከው “ይኩን ፈውስ ዐብይ በውስቴትኪ፤ በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ” አሉ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መካኖች ይወልዱ፣ ድዉዮች ይድኑ ጀመር፤ “ወእም አሜሃ ተሰምየት ዐባይ ይእቲ ፈለግ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይህች ዐባይ ተብላ ተጠራች።” (ገድለ አቡነ ዘርዐ ብሩክ)

ዓባይ ከኢትዮጵያ እንደመነሳቱ ሙሉ በሙሉ ባለቤትነቱ ለእርሷ እንደሚገባ በማመን በዘመናት የተነሱ መንግሥታት ከግብፅ እንዲሁም ከተባበሩት የዓለም መንግሥታት ድርጅቶች ጋር በመወያየት ወንዙን በሀገሩ ለማስቀረት ብዙ ጥረዋል፡፡ በተለይም ከዛግዌ ዘመነ መንግሥት በኋላ የኢትዮጵያውያን ወንዙን የመገደብ ፍላጎት አይሎ እዚህ እኛ ዘመን ላይ እውን ሊኾን ችሏል፡፡ ያው እንደሚታወቀው ሀገራችን ተመጽዋች የኾነችው በድርቅና ጦርነትን ተከትለው በሚመጡ ቀውሶች ነው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ ዓባይና እርሱን የመሰሉ ወንዞቿን ገድባ መጠቀም ይኖርባታል፡፡ ስለዚህ በሀገራችን ከሚገኙ ታታላቅ ወንዞች ታላቅ ክብር የሚሰጠው ወንዝ ግዮን ወይም ዓባይ ነው፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድም የሚደነቅም የሚከበርም ወንዝ ነው፡፡ በሰከላ ግሽ ተራራ ግርጌ የሚፍልቀው ግዮንን መምጣቱን የሚናፍቁት፣ አብዝተው የሚጠብቁት፣ ሕይወታቸው በእርሱ ላይ የመሠረቱም ብዙዎች ናቸው፡፡ ግብጽም የእርሱው ተመጽዋች ነች፡፡ ስለዚህ ሀገራችን ፈጣሪ በጸጋው ያቀረበላትን ግዮን ወንዝ ከዚህም በላቀ አልምታ ልትጠቀምበት ይገባል፡፡

ግዮን የኢትዮጵያን የረዘመ ታሪክ የሚዘክር፣ ቅድስናን፣ ታማኝነትን፣ ቀዳሚነትን የሚመሰክር፣ ምሥጢሩ የረቀቀ፣ በዓለም ዳርቻዎች ኹሉ የታወቀ፣ ሥልጣኔ እንደ ውኃው ሁሉ የሚፈስስበት፣ ከዥረቱ ጋር የሚጓዝበት፣ ዕውቀት የሚቀዳበት፣ ጥበብ የሚጠጣበት ስለመኾኑ ይነገራል፡፡ ለግዮን መፍለቂያ ከተከፈተው ከግሽ ተራራ ግርጌ መነሻን አድርጎ ታላቁን ወንዝ ቢከተሉት፣ በጥበብ ቢመረምሩት፣ በአስተውሎ ቢመለከቱት እልፍ ምስጢር እንዳለው ስለወንዙ የጠለቀ መረዳት ያላቸው ወገኖች ያወጋሉ፡፡ ጥበብን ከምንጩ ለመቅዳት የሚሻ ሁሉ በየጊዜው ወደ ሠከላ ግሽ ተረራ ግርጌ ይገሰግሳል፡፡ በዚያ ውስጥም የኢትዮጵያን ውበት፣ የምድር በረከት ያያል፣ ይታዘባል እውቀትን ይሰንቃል፡፡

የዚህ ታላቅ ወንዝ መነሻ የኾነችው ሰከላ ከባሕር ዳር ከተማ በ164 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ሰከላ በኢትዮጵያ ወተትና ማር በሚፈስበት፣ ነጭ ጤፍ በሚታፈስበት፣ ጥበብ በሚፈልቅበት፣ በጎጃም ክፍለ ሀገር ከግሽ ተራራ ግርጌ ትገኛለች፡፡ ይህ ወንዝ ከግሽ ተራራ ግርጌ መንጭቶ፣ ከምስጢራዊ ሐይቅ ከጣና ጋር ተገናኝቶ፣ በጣና ሐይቅ ላይ አልፎ ምድርን እያረሰረሰ ሲና በርሃን አቋርጦ ከታላቁ ሕንድ ውቅያኖስ ይቀላቀላል፡፡ ሰሞኑንም ለዚህ ወንዝ መታሰቢያ ይኾን ዘንድ ለአራተኛ ጊዜ የግዮን በዓል የወንዙ መነሻ በኾነችው ሰከላ ወረዳ ግሽ ዓባይ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉም ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችም ተካሂደዋል። በበዓሉ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ዘካርያስ እና የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ እንግዶችና ታዳሚዎች ተሳትፈዋል። የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዘካርያስ የግዮን ወንዝ ካለው ሃይማኖታዊ አንድምታና በዓሉን ከማክበር ባሻገር “ሁልጊዜ የዓባይ ልጅ መባል ትርጉም የለውም፤ ትርጉም የሚኖረው ይህን ታላቅ ወንዝ ከመሠረቱ ለማልማት በጥንካሬ መሥራት ስንችልና ስንለወጥ ነው” ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ደግሞ የዓባይ ወንዝ ከመሠረቱና ከምንጩ በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባና ለዚህም ክልሉም አስፈላጊውን ኹሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። በዕለቱ “የዓባይ ወንዝን ከመሠረቱ በማልማቱ ሂደት ምን ልናደርግ ይገባል” በሚል ሐሳብም የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የአካባቢው ተወላጆች የተሳተፉበት ውይይት የተደረገ ሲኾን በውይይቱ ዓባይን ከምንጩ ለማልማት የደብረ ማርቆስ፣ የእንጅባራና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የክልሉ መንግሥት በበላይነት የሚከታተለው ኮሚቲ ተቋቁሞ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲሠራ መግባባት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል። የግዮን በዓል ሰከላ ላይ ከምንጩ የመከበር ዋነኛው ዓላማውም ወንዙን ከመነሻው በማልማት የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መኾኑን የበዓሉ አዘጋጆች ጠቅሰዋል። እኛም ደግመን እንላለን፡- “ይኩን ፈውስ ዐብይ በውስቴትኪ” ይኽን ጽሑፍ ለማጠናቀር የማኅበረ ቅዱሳንን ድረ ገጽ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬት ዘገባዎችን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...