ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከትግራይ የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጋር መወያየታቸውን ገልፀዋል።
በውይይቱ በተለይም የተፈናቃዮች ጉዳይ፣ የትግራይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚዊ ሁኔታዎች ላይ በዋናነት ምክክር የተደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች እንደነበሩ ተገልጿል።
በፐብሊክ ዲፕሎማሲው አባላት በኩል በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን፤ መንግስት ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት እና ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀቱን ሊቀጥል ይገባል የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰራጩት መልዕክት ገልጸዋል።
በመልዕክቱ፤ በፐብሊክ ዲፕሎማሲው አባላት ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ውይይት እና የትግራይ ህዝብ ድምጽ በትክክል የሚሰማባቸው ክፍት መድረኮች መቋቋም እንዳለባቸው አሳስበዋል ብሏል።
