የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል፣ 85 ያህል የኦሮሞ ምሁራን ሰሞኑን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ “በርካታ ስህተቶች” እና “መሠረት ቢስ ውንጀላዎች” ያሉበት ነው በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ዛሬ ምላሽ ሠጥተዋል።
አለመግባባቶችን ለመፍታት ትክክለኛው መንገድ፣ በደብዳቤው ጸሃፊዎችና በኤርትራዊያን አቻዎቻቸው መካከል “የፊት ለፊት ውይይት” ማድረግ እንደኾነም የማነ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በዘንድሮው የኤርትራ ነጻነት በዓል ላይ ስለ “ፖለቲካዊ ኦሮሙማ” ያነሱት ነጥብ፣ አንዳንድ “ወካይ ያልኾኑ” አካላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያራምዱትን አስተሳሰብ ብቻ የሚመለከት መኾኑንም የማነ አብራርተዋል።
የማነ አያይዘውም፣ ባኹኑ ወቅት በቀጠናው የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ የሚገኙት “የኤርትራን ሉዓላዊ ግዛቶች በኃይል መያዝ የሚፈልጉ አካላት” እንጅ ኤርትራ አይደለችም ብለዋል።
የኦሮሞ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት ለመብቱ ሲያደርገው ለቆየው ትግል፣ ኤርትራ አጋርነቷን ስትገልጽ መቆየቷንም የማነ ገልጸዋል።
በውጭ የሚገኙ የኦሮሞ ብሄር ምሁራን፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢትዮጵያ መንግሥትን ፖሊሲ ሲወቅሱ ኦሮሙማን በተሳሳተ አረዳድ አቅርበውታል በማለት፣ ባለፈው ሳምንት ለፕሬዝዳንቱ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈው ነበር።
ዋዜማ
