በአዲስ አበባ ከተማ በትንሹ በቀን አራት ሕጻናት የተለያዩ አካባቢዎች መንገድ ላይ ተትተው እንደሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ የሴቶች እና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአሐዱ ገልጿል።
ቢሮው ወላጆቻቸው መንገድ ላይ ትተዋቸው የሚሄዱ ሕጻናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱም አስታውቋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች በመንገድ ላይ ተትተው ወይም ተጥለው የሚገኙት ሕጻናት አብዛኛውን ጊዜ ጤነኛ ሆነው እንደማይገኙ የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ፤ በዚህ አይነት መልኩ የተገኙ ከ280 በላይ ሕጻናት “ክበበ ፀሀይ የሕጻናት መርጃ ማዕከል” ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የከፋ የምግብ ችግር ያጋጠማቸው ከ38 ሺሕ 500 በላይ ሕጻናት ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ በ26 ማዕከላት ምገባ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከሕጻናቱ ጋር በተያያዘም ለማሳደግ የሚፈልግ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እየበዛ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡
የልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕጻናት በተመለከ በትምህርት ቤቶች ትምህርቱ እንዲሰጥ እና ትምህርት ቤቶቹም እንዲበዙ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የአምሮ እድገት ውስንነት እና የባህሪ እክል ለገጠማቸው ልጆች አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ እና ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑም ተመላክቷል።
በ2017 ዓ.ም ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ከ137 በላይ ቤተሰቦች በሕጋዊ መንገድ በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ልጆችን ከመንግሥት ተቀብለው ለማሳደግ ወረፋ እየተጠባበቁ መሆኑን ሚኒስቴሩ ስለማስታወቁ አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
