ማሸነፍን ከበላይ…ይድረስ ለድምፃዊ በላይ መልሴ

Date:



ከተመስገን ኡካሬ (የሐጌ ልጅ)


ተወዳጁ የዘመናዊ የሙዚቃ አቀንቃኝ ድምፃዊ በላይ መልሴ ለሙዚቃ የከፈለው መስዋዕትነት እና የተጓዘበት መንገድ የዋዛ አይደለም፡፡ የተወለደው በመዲናይቱ አዲስ አበባ ‹‹አዲስ ከተማ›› ነው፡፡ መርካቶ ለእርሱ አድባሩ ናት፡፡ ከሰፈሩ አብነትም በርካታ ነገሮችን ቀስሟል፡፡ ሙዚቃ ከነፍሱ ጋር የተተዋወቀችው ገና ብላቴና ሳለ ነበር፡፡ በልጅ እድሜው ተሰጥዖውን በጊዜ በማወቅ ጉሮሮውን ለመፈተን አልተቸገረም፡፡

በሚሽን በሚማርበት ወቅት የሕብረ መዝሙር ዜማዎችን በመዘመር እና በቤት ውስጥ የበርካታ ሙዚቀኞችን የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን መርጦ በመጫወት ጉሮሮውን ለማሰልጠን ታትሯል፡፡ የተሾመ አሰግድ፣ ጌታቸው ካሳ፣ ጋሽ ጥላሁንን ገሠሠ፣ ዓለማየሁ እሸቴና ሌሎችም ደግሞ የሙዚቃ አንደበቱን የፈታባቸው ባለውለታዎቹ ናቸው፡፡


ድምፃዊ በላይ መልሴ የሙዚቃ ጅማሮው በዚህ መልክ በልጅነት እድሜ ይሁን እንጂ፣ ብቃቱን በአደባባይ ያስመሰከረው በአንድ ድንገቴ አጋጣሚ ነበር፡፡ ‹‹አጋጣሚዎችን በአግባቡ ስንጠቀም አቅጣጫችን ሁሉ ያምራል›› እንደሚባለው ኾነና እርሱም ከእለታት በአንዱ በቤታቸው በተሰናዳ ትልቅ የሽኝት ፕሮግራም ላይ አጋጣሚውን ተጠቀመ፡፡

በሰዓቱ ‹‹ልዑል ሚካኤል›› ባንድ በቤታቸው ለዚያ የሽኝት መርኃ ግብር ተገኝተው የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር፡፡ ድምፃዊ በላይ መልሴም ይንን እድል እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ፣ በደጉ ቀን ያሟሸው ጉሮሮውን ከባንዱ ጋር ለማስማማት ማይክ ጨበጠ፡፡ የድምፃዊ ተሾመ አሰግድን ‹‹ይቺ አጋጣሚ›› የሚለውን ሙዚቃም ተጫወተ፡፡ በቦታው የነበሩት ሁሉ ‹‹አጀብ›› አሉ ፤ ተገረሙ፡፡ ከሁሉም አንደበት ልብን የሚያሞቅ ከፍተኛ አድናቆት ተወረወረለት፡፡ እንኾ ከዚያች ቅጽበት በኋላ የሙዚቃ ፈተና እና ስኬቱ ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ፡፡


የፈተናው መነሻ ቤተሰቦቹ ወደ ሙዚቃ መሳቡን አለመውደዳቸው ነበር፡፡ የነፍሱ ጥሪ ወደ ሙዚቃው ዓለም መኾኑን አምነው መፍቀድ አልቻሉም፡፡ ይኽ አብዛኞቹ ድምጻውያን የሚጋጥማቸው ችግር ነው፡፡ በላይ መልሴ ግን ከዚህም ጠጠር ያለ ነገር ገጠመው፡፡ ቤተሰቦቹ ወደ ባሕር ማዶ ሔዶ ሙዚቃን እስከወዲያኛው እንዲላቀቃት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ወጣቱ አቀንቃኝ ግን የሚበገር አልኾነም፡፡ የሙዚቃ ፍቅሩንና የነፍሱን ጥሪ በዚህም በዚያም ማስታገሱን ቀጠለ፡፡ ጫናዎቹን ሁሉ ተቋቁሞ ስኬቱ ጋር የመድረስ ሩጫውን አጠናከረ፡፡


በድብቅ ወደ ተለያዩ ምሽት ክበቦች እየሔደ ከአንጋፋና ወጣት የወቅቱ ኮከብ ድምጻውያንም ጋር ሠራ፡፡ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ማንዲንጎ አፈወርቅ፣ አበበ ተካ፣ ላፎንቴን፣ ብዙአየው ደምሴ፣ ኃይለ ኢየሱስ ግርማ እና ከመሳሰሉት ጋር ያገኘው የመሥራት ዕድልም የስኬቱን መንገድ ጠረገለት፡፡


ድምጻዊ በላይ መልሴ ለመጀመርያ ጊዜ በባንድ ደረጃ የሰራው በ‹‹ክስታኔ ባንድ›› ነው፡፡ በጊዜው ከእነ ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አብነት አጎናፍር፣ ፀጋዬ ስሜ (ኦሴባሳ) በጋራ በመሆንም ብዙ ተጫውቷል፡፡ ከክስታኔ ባንድ በኋላ ደግሞ ሸበሌ ጋርደን ባንድን ተቀላቅሎ የተወሰኑ ጊዜያት ሠርቷል፡፡


በላይ በዚህ መልክ በድብቅ እየነጎደ ከነፍሱ ጋር የተቆራኘውን የሙዚቃ ፍቅር ሲወጣ ቆየ፡፡ ከቤተሰቦቹ የሚደርስበትን ቁጣ ሳይቀር የሚያበርደው በሙዚቃ ነበር፡፡ ቤተሰቦቹም ቢኾኑ የዋዛ አልነበሩም፡፡ መንገዱን ስላልወደዱት ሌላ ቀመር ከማዘጋጀት አልቦዘኑም፡፡ እናም እርሱን ከሙዚቃ እስከወዲያኛው ለመለያየት አንድ ውሳኔ ወሰኑ፡፡ ይኸውም ከሀገር እንዲወጣና አዲስ ሕይወት፣ አዲስ ኑሮ፣ አዲስ አየር እንዲጋፈጥ ይግባኝ የሌለው ፍርድ ማሳለፋቸው ነበር፡፡ ፋታ አልሰጡትም፡፡ የውጪ ‹‹ፕሮሰሱን›› አፋጥነው ወደ ጀርመን እንዲበር አደረጉት፡፡


ቅድመ ስደት በነበረው የሀገር ቤት ሕይወቱ ተወዳጁ ድምፃዊ በላይ መልሴ፣  በድምፃውያን አስመስሎ የመዝፈን ወድድር ላይ ተሳትፎ አሸናፊ ጭምር እስከመኾን ደርሶ ነበር፡፡ በዚያ የጥላሁንን ገሠሠ፣ የምኒልክ ወስናቸው እና የዓለማየሁ እሸቴ ዘፈኖች ለውድድር በቀረቡበት መድረክ፣ ድምፃዊ በላይ መልሴ የዓለማየሁ እሸቴ ‹‹የወይን ሐረጊቱ›› ሥራን ተጫውቶ ነበር አሸናፊ ለመኾን የበቃው፡፡ በወቅቱ ሽልማቱ 500 መቶ የኢትዮጵያ ብር ነበር፡፡ ከበርካታ ተወዳዳሪዎች መካከል ተመርጦ እና በአንጋፋ ድምጻውያን ተዳኝቶ በማሸነፉም ትልቅ ሥም ገነባ ፤ ሥሙም ከዛን ጊዜ አንስቶ እስከዛሬ መነገርና መወሳቱ አልቆመም፡፡ ያ መድረክና ወቅት ድምጻዊ መሆኑን ያረጋገጠበት መኾኑን መለስ ብሎ በትውስታ ያነሳል፡፡


እንኾ ኑሮውን በስደት ዓለም መምራት ከጀመረ በኋላ ያለው ሕይወቱም ቢኾን ከዚህ ምትሓታዊ የሙዚቃ ፍቅር የሚያናጥበው አልኾነም፡፡ ከሀገር ከቤተሰብ ራቀ እንጂ ከሙዚቃ ለአንዲትም ቅጽበት አልሸሸም ፤ ልክ እንደትናንቱ አሁንም እንደተጣበቀ አለ፡፡ ድካም አይበግረውም፣ የሚመኘውንም ለማሳካት ጥግ ድረስ ይጓዛል፡፡ በጀርመን እና ከጀርመን ውጪ ባሉ የተለያዩ ሥፍራዎች በመጓዝ ሐበሾች በሚሰባሰቡባቸው ክበቦች የሙዚቃ ሥራውን ያቀርባል፡፡


በላይ የተለያዩም ነጠላ ሙዚቃዎችን ለአድማጭ ጆሮ አድርሷል፡፡ ሙዚቃዎቹ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና መደናነቅን ዓቢይ ጭብጣቸው አድርገዋል፡፡ ‹‹ያንጎለላት››፣ ‹‹በቃ››፣ ‹‹ቅበጪልኝ››፣ ‹‹ውበት ሲለካ›› የተሰኙት ሙዚቃዎች ከእነዚህ መሃል ናቸው፡፡


****
ለመኾኑ ድምጻዊ በላይ መልሴ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ስለ ሥራዎቹስ ምን ይለናል? በሚሉት ነጥቦች ዙርያ ከዚህ ጽሑፍ አሰናጅ ጋር በቴክኖሎጂ የታገዘ አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡


አዲስ አበባ አንድ ሰሞን መጥተህ ተገናኝተን ነበር፡፡ ኑሮህ ባሕር ማዶ እንደኾነም ነግረኸኝ ነበር፡፡ ተመልሰህ ስትመጣ ምን ታዘብህ?
በላይ፡- ልክ ነው፣ አዲስ አበባ የመጣው ጊዜ ተገናኝተን ነበር፡፡ በፋና ላምሮት የቴሌቪዥን ውድድር ላይ  አብረን ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ ለሰጠኸኝ አስተያየትም አመሰግናለሁ፡፡ በወቅቱ ጥሩ ድምፃውያኖችን ተመልክቻለሁ፡፡ ባንዱም በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሳውንዱ ሲዲ የምሰማ ነበር የመሰለኝ፡፡


በባሕር ማዶ ቆይታህና አሁን ያለህበት ኹናቴ ምን ይመሥላል?
በላይ፡- እዚህ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ኮንሰርቶች ላይ ተጫውቻለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ ኤፍሬም ታምሩ ያሉ ድምጻውያን በተጋበዙባቸው ዝግጅቶች ላይ ጭምር ዘፍኛለሁ፡፡ ኮሜዲያን እሸቱ እና ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም ባዘጋጇቸው የተለያዩ መድረኮችም ላይ እንዲሁ ሙዚቃ የመጫወት ዕድልን አግኝቻለሁ፡፡


በብዛት በዘፈኖችህ ባሕላዊ ሙዚቃዎችን ታዘወትራለህ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በላይ መልሴ የሚመቸው የሙዚቃ ቅኝት የቱ እንደኾነ ሊነግረን ይችላል?


በላይ፡- እኔ ዘመናዊ ሙዚቃ ተጫዋች ነኝ… ከቅኝት አንጻር ከኾነ ደግሞ አንቺሆዬ እና ማይነር ዘፈን እወዳለሁ፡፡


‹‹ቅበጪልኝ›› የተሰኘው ሥራህ ብዙ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ከሙዚቃ አቀናባሪው ሔኖክ ነጋሽ ጋር የሰራችሁት ይኽ ሙዚቃ እንዴት ተሰራ? ሐሳቡስ እንዴት መጣ?


በላይ፡- ቅበጪልኝ በጣም ተወዳጅ ሥራዬ ነው፡፡ በወቅቱ በተለያዩ ቻናሎች ዘፈኑ ቀርቧል… ዜማ እና ግጥም እንዲሁም ቅንብሩ የሄኖክ ነጋሽ ነው፡፡ በአንድ አጋጣሚ ለሌላ ሥራ ሄኖክ ጋር በሔድኩበት ሙዚቃውን ሲያሰማኝ ወደድኩት ፤ በአራት ቀን ያለቀ ሥራ ነው፡፡


እስካሁን ከታላላቅ ድምፃዊያን ከእነማን ጋር የመሥራት ዕድል ገጥሞሃል?


በላይ፡- ከቴዲ አፍሮ፣ አስቴር አወቀ፣ ጋሽ ማሕሙድ አሕመድ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ሐመልማል አባተ፣ አለማየሁ እሸቴ፣… በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ሀገር ቤትም እዚህም

ከበርካቶች ጋር አሬ የመዝፈን ዕድሉን አግኝቻለ፡፡
አሁን ካሉት ወጣት ድምፃ
ውያንስ የማን አድናቂ ነህ?
በላይ፡- አሁን ካሉት ድምፃዊያኖች ማስተዋል እያዩን በጣም ነው ማደንቀው፡፡ በተጨማሪም ዳዊት ፅጌን አደንቀዋለሁ፡፡


አሁን ላይ በባሕር ማዶ ቆይታህ ምን እየሠራህ ትገኛለህ? ምን አዲስ ነገርስ እንጠብቅ?


በላይ፡- በባሕር ማዶ ቆይታዬ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ አዲስ ነገር ላልከኝ፣… ቢኒያሚር የሰጠኝ አዲስ ግጥም እና ዜማ አለ፡፡ እሱን ስመጣ ሰራዋለሁ… ይህ ነው፡፡
****


ውድ አንባቢያን፣ ከድምፃዊ በላይ መልሴ ጋር ከነበረባት የሎንደን ከተማ በዘመኑ ቴክኖሎጂ ያደረግነው ቆይታ በጥቂቱ ይኽንን ይመሥላል፡፡ ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ እንደሚኖረን ተስፋ አለኝ፡፡ ለእኔም ኾነ ለአንባቢያን ለሰጠን ጊዜ እጅጉን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...