እስራኤል ለሶማላንድ የሉዓላዊ ሀገርነት ዕውቅና መስጠቷን የተቃወሙ በሺዎች የሚቀጠሩ ሶማሊያዊያን ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች አደባባይ ወጡ ።
ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በተለይ በዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾ በሚገኘው ስታድዮም የሶማሊያ እና የፍልስጤም ባንዲራ በመያዝ ተሰባስበው እስራኤልን የሚያወግዝ መፈክር ሲያሰሙ ውለዋል።
«ማንም ሉአላዊነታችንን እንዲዳፈር በፍጹም አንፈቅድም» ያሉት ሰልፈኞቹ የእስራኤል እርምጃ «ዓለማቀፉን ሕግጋት የሚጥስ» ነው ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ሰልፈኞቹ ከሞቃዲሾ በተጨማሪ በሰሜን ምስራቃዊዋ ከተማ ላስካኖድ ፣ በማዕከላዊ ሶማሊያ በምትገኘው ጉሪሴል እና የባይዶዋ ከተሞች ተመሳሳይ ሰልፎች በድምቀት መካሄዳቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ቱርክ የሚገኙት የሶማሊያዉ ፕሬዚደንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ዛሬ ከቱርክ ፕሬዚዳንት ጋር በወቅታዊው ጉዳይ ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና ከሰጠች በኋላ ለተከፈተባት ዓለማቀፍ ተቃዉሞ መልስ ሰጥታለች። እስራኤል በዚህ ምላሿ የትኛዉም ሀገር «በውጭ ፖሊሲዬ ጣልቃ ሊገባ አይችልም » ስትል የሃገራቱን ተቃዉሞ አጣጥላለች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ማንም እስራኤል ከማን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታደርግ ሊወስን አይችልም” ሲሉ ጽፈዋል።
