ሶማሊያ 24 የሚደርሱ ‘JF-17 ተንደር ብሎክ III’ ተዋጊ ጄቶችን ለመግዛት ከፓኪስታን ጋር ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ድርድር እያደረገች ትገኛለች ሲሉ የሶማሊያ እና የፓኪስታን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ይህ የጦር መሣሪያ ግዢ ስምምነትም 900 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ተብሎ ይገመታል።
ይህ ስምምነት ከተጠናቀቀ፣ እ.ኤ.አ. በ1991 የማዕከላዊው መንግሥት ከፈረሰ በኋላ ሞቃዲሾ የፈጸመችው ትልቁ የመከላከያ መሣሪያ ግዢ ይሆናል ተብሏል።
ይህ ድርድር መነቃቃት ያሳየው፣ በኮማንደር ማሕሙድ ሼክ አሊ የሚመራ የሶማሊያ አየር ኃይል ልዑክ በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ኢስላማባድ ካደረገው ጉብኝት በኋላ ነው። ጉብኝቱ ሞቃዲሾ ከአሥርተ ዓመታት ግጭት እና በሌሎች አገራት ላይ ከነበራት ጥገኝነት ተላቃ፣ የአየር ኃይሏን ዳግም ለመገንባትና የአገሪቱን የአየር ክልል ሉዓላዊነት መልሳ ለመቆጣጠር ያላትን ቁርጠኝነት አመላካች ነው።
አንድ የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ለቀጣናው መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፤ ይህ ግዢ የሶማሊያ አየር ክልል “በራሳቸው በሶማሊያውያን እጅ እንዲጠበቅ” የሚደረገውን ጥረት የሚያንጸባርቅ ነው ተብሏል። ባለሥልጣኑ አክለውም ስምምነቱ አገሪቱ እያከናወነችው ያለው ሰፊ ተቋማዊ መልሶ ግንባታ አካል መሆኑን ገልፀዋል።
‘JF-17 Thunder’ የተሰኘው ተዋጊ ጄት በፓኪስታን ኤሮኖቲካል ኮምፕሌክስ እና በቻይናው ቼንግዱ ኤርክራፍት ኮርፖሬሽን በጋራ የበለፀገ ነው። ተዋጊ ጄቱ ዋጋቸው ውድ ከሆኑ የምዕራባውያን የጦር መሣሪያዎች አማራጭ ለሚፈልጉ አገራት ተብሎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በዝቅተኛ ወጪ በርካታ ወታደራዊ ተግባራትን ማከናወን የሚችል ተዋጊ ጄት ተደርጎ በገበያ ላይ ቀርቧል።
የፓኪስታን የመከላከያ ምርት ሚኒስትር ራዛ ሐያት ሐራጅ ቀደም ሲል እንደገለጹት፤ የአንድ ‘JF-17’ ተዋጊ ጄት ዋጋ ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ከምዕራባውያን ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም ያነሰ ነው። ይህም ጄቱ ውስን በጀት ላላቸው ገዥ አገራት ትልቅ አማራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
ተዋጊ ጄቱ ቀደም ሲል ለምያንማር፣ ለናይጄሪያ እና ለአዘርባጃን የተሸጠ ሲሆን፤ ሌሎች የእስያ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራትም ጄቱን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ተዘግቧል።
አገሪቱ ድርድሩን እያከናወነች እንደምትገኝ የተገለፀው፣ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በሶማሊያ ላይ ተጥሎ የነበረውና ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ እንዳታስገባ አግዶ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እ.ኤ.አ. በ2023 መነሳቱን ተከትሎ ነው።
የስምምነቱ የገንዘብ ምንጭን በተመለከተ እስካሁን ጥያቄዎች ይነሳሉ። በሪፖርቱ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ከሶማሊያ ዓመታዊ የመከላከያ በጀት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ በመሆኑ፤ ታዛቢዎች የውጭ አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ስለዚህ ጉዳይ የተሰጠ ይፋዊ ማረጋገጫ የለም።
ይህ በግምት እስከ 900 ሚሊዮን ዶላር፣ አንዳንዶች ደግሞ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል የሚሉት ስምምነት ከተጠናቀቀ፤ የሶማሊያን የአየር ኃይል አቅም ከመቀየር ባለፈ፣ ፓኪስታን በተለይም በአፍሪካ ያሉ አዳዲስ ገበያዎችን በመቆጣጠር ረገድ ያላትን የመከላከያ መሣሪያዎች ሽያጭ የማስፋፋት ፍላጎቷን እንደሚያሳካላት ተመላክቷል።
