)
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
በሰሜኑ አካባቢ ተከስቶ የነበረው ግጭት፣ ስለጦርነቱ መንስኤ፣ አሁን በክልሉ አለ የሚባለው ውጥረት እንዲሁም ከሻዕቢያ ጋር የተያያዙ ነጥቦች የውይይቱ አጀንዳ ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) ” የሻዕብያ ስርኣት በሃገራችን ግዛት ገብቶ የተለያዩ ሴራዎችን በደሎችን እየፈጸመ እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች እየተገለጸ ይገኛል በዚህ ጉዳይ ላይ ያሎት አቋም ምን ይመስላል ? ” የሚል ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር።
ምን መለሱ ?
” የሰሜን እዝ እንደተጠቃ የቀረው ኃይል ወደ ኤርትራ ካቀና በኋላ የኤርትራ ህዝብ እና ሻዕቢያ ለሠራዊታችን ያደረገው ድጋፍ የሚሞገስ ነው።
የተደረገው ድጋፍ በምን ምክንያት ነው የሚለውን ወደ ጎን ትተን፣ ለአወንታዊ አስተዋጽዖ በወቅቱ አመስግነናል ይህ በግልፅ የታወቀ ነው በአደባባይም ያደረግነው ነው።
ድጋፉን አመስግነን የፈፀሟቸውን እኩይ ተግባራት ደግሞ እናወግዛለን ችግሩን እንደ ችግር መነሳት ስላለበት አውግዘናል ፤ ይህ እኩይ ተግባር እኩይ፣ መልካሙ ተግባር ደግሞ መልካም በማለታችን ቅር አይለንም።
የኤርትራ ሠራዊት የሰሜን እዝ ስለተጠቃ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደ ትግራይ መግባቱ ይታወቃል።
መንግሥት በዚያን ወቅት የውጭ ኃይልን ለመከላከል የሚያስችል ሁኔታ ላይ አልነበረም ኃይላችን ውስን ነበር። ከህወሓት ጋር ውጊያ ላይ ነበር የነበረው የውጭ ኃይልን መከላከል አንችልም ነበር።
ስለሆነም የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ ገብቶ ከባድ ወንጀል ፈፀመ፣ ንፁሐንን ገደለ፣ ተቋማትን ዘረፈ የሲቪልና ማህበራዊ ተቋማትን አወደመ በተለይ በአክሱም ከተማ በሁለት ቀናት ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ጨፈጨፈ።
ያን ጊዜ ነው የተለያዩ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን ወደ አስመራ ልከን የነበረው።
በአክሱም ብቻ ሳይሆን ዓድዋ፣ ዓዲግራት፣ ሽሬን ጨምሮ ቤቶችን አፈረሰ ፣ ኢንዱስትሪዎችን አወደመ፣ ማሽነሪዎቹንም ዘርፏል።
ከዚያም ወደ መቐለ እንዳይገባ ብለን ታክቲካዊ በሆነ መንገድ ዘግተነው ነበር ምክንያቱም በገባበት ከተማ ሁሉ ጥፋቶችን ይፈፅም ስለነበር ነው፤ አሁንም አለው ለማለት ብቅ ጥልቅ እያለ ነው።
ለሻቢያ ያለኝ መልዕክት ፣ ለኤርትራ ሠራዊት፣ ለሁሉም ያለኝ መልዕክት ‘ ቀንጠብጠብ፣ ትብል ዳዋ፣ እትምጽኦ አለዋ ‘ ማለት ብቻ ነው የምፈልገው። ” ብለዋል።
ሻዕቢያ ያለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁመና ምን ይመስላል ?
” የሚገርመው የሻዕቢያ ሥርዓት በባሰ መንገድ በልማት አያምንም በሥልጣን ሽግግር አያምንም ልጆቹን፣ የልጅ ልጆቹን ሳይቀር አያምናቸውም።
እንደሚታወቀው የኤርትራ ህዝብ የሥራ ፍቅር ያለውና ሥራ ፈጣሪ ነው ነገር ግን የሚሆነውን መንግሥት ማግኘት አልቻለም።
ሁላችንም እንደምናውቀው ሻቢያ ሥልጣን ሲይዝ ከሦስት መቶ በላይ ፋብሪካዎች በኤርትራ ነበሩ ዛሬ ሁሉም በሚባል ደረጃ የሉም።
ያኔ አስመራ ዩኒቨርሲቲ የምትባል አንድ ዩኒቨርሲቲ ነበረች እሷም ተዘግታለች ኤርትራ እንደ ሀገር አንድ ዩኒቨርሲቲ የላትም።
ኤርትራዊ ሀገሩን ትቶ ወደ ስደት አምርቷል የሚታወቅ ነው ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ በሁሉም ሀገራት ተሰደዋል ኤርትራ ባዶ እየሆነች ነው።
እነዚህ ከሀገራቸው የተሰደዱት በስደት ላይ ሰርተው እንዳይኖሩ ከእነርሱ ጋር ሰላዮችን ጭምር እየላከ ማነው ጤነኛ ማነው በሽተኛ የሚለውን ለማወቅ አስቸጋሪ ስለሆነ ሰላማዊ የሆኑት ችግር ላይ እየወደቁ ነው።
እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ኤርትራውያን እንደ ሀገራቸው ይሥሩ የሚል አቋም ነበረን ችግር እየፈጠረ ያለው ከጤነኛው ጋር ተቀላቅሎ የሚመጣው በሽተኛ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ስላሉ ነው ማነው ጤነኛ ማነው በሽተኛ ለማለት ያስቸግራል።
በሀገራቸው እንዳይኖሩ ሰላም እያሳጣቸው ነው ስደት ላይ ሆነውም ሰላም እያሳጣቸው ይገኛል።
ይህ የክፋት ሁሉ መሠረት ነው ሰው በሀገሩም በውጭም መኖር ካልቻለ በጣም አስቸጋሪ ነው ይህ ይቅር ሊባል የማይገባው በደል ነው የሚመስለኝ ይቅርታ የማይገባው ሰብዓዊ በደል ነው።
እኛ ከልምዳችን ቀረብ ብለን ለመስራት ሞክረን ነበር ከልምዳችን የተማርነው ምንድነው ካልከኝ፣ ከዚህ ኃይል ምንም ጥሩ ነገር ማግኘት የማይታሰብ ነው።
ስለሆነም አቅም ካገኘ ሀገርን ከመበጥበጥ ወደ ኋላ አይልም ይሁን እንጂ አሳምረን ስለምናውቀው ዳግም ህዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጥም ምናልባት ከሞከረ ደግሞ የመጨረሻ ሙከራው ነው የሚሆነው ብዬ ነው እኔ የማምነው ” ብለዋል።
ሙሉ ቃለምልልሱ https://www.facebook.com/61588053582297/posts/122104691121268452/?app=fbl
@tikvahethiopia
