የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የምግብና የአይነት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች፤ 98 ቢሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት እና የቁሳቁስ እርዳታ ማድረጉን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃና ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ፍራኦል በቀለ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በዚህ ዓመት በተለያዩ ችግሮች የምግብ እና የዓይነት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ዜጎች እርዳታው ተደርጓል፡፡
በዚህም ኮሚሽኑ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የጥራጥሬ ምርት እንዲሁም 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹ ሲሆን፤ ከምግብ በተጨማሪ የንፅህና መጠበቂያ በማካተት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የተደረገው ድጋፍ ዓመቱን በሙሉ የተደረገላቸው ዜጎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ አንድ ግዜ ብቻ የተደረገላቸው ዜጎች ስለመኖራቸውም አንስተዋል።
የተደረገው ድጋፍ በአጠቃላይ በተለያየ ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ያሉትን ዜጎች ያካተተ መሆኑን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ በዚህም በበጀት ዓመቱ በመላው ኢትዮጵያ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ 1 ነጥብ 2 ሚልዮን ተፈናቃዮ 29 ቢልዮን ብር የሚገመት የዓይነት እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ አስረድተዋል።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ አዳጋች እንደነበረ አስታውሰው፤ ከሚመለከታቸው የዞን፣ የወረዳ እና የክልል መስተዳድሮች ጋር በመሆን በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በአማራ ክልል 69 ሺሕ 112፣ በትግራይ ክልል ለ527 ሺሕ ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙና የዕለት ደራሽ እና መሰረታዊ እርዳታ እንደቀረበላቸው አስረድተዋል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል እና በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
“ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ ቀዳሚው መፍትሔ ነው” ያሉት ዶክተር ፍራኦል በቀለ፤ ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ የመኖሪያ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራው የሚከናወነው በተፈናቃዮቹ ፍላጎት ላይ ብቻ ተመስርቶ በመሆኑ፤ በዓለም አቀፍ ሕግጋትን በተከተለ መንገድ የአካባቢዎቹ ደህንነት ከተረጋገጠ በኋላ ወደ አካባቢያው የተመለሱ እንዳሉ አስታውሰዋል።
ተፈናቃዮች ባሉበት ክልልና ዞን ሆነው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መሰረታዊ ነገሮችን ለማሟላት እና ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃና ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ፍራኦል በቀለ አክለውም፤ “ለተቋሙ ችግር የሆነበት የተፈናቃዮችን ቁጥር በማጋነ ለፓለቲካ አላማ የሚጠቀሙ የተለያዩ ተቋማት መኖራቸው ነው” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በጦርነት፣ በግጭት እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2024 ያወጣው መረጃ ያሳያል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
