በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ወደ ሀገር ለመመለስ እየተሰራ ቢገኝም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለ እያወቁ የስራ እድል አለ በሚል የሚሄዱ ዜጎች እያጋጠሙት መሆኑን ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ሆኖም በህጋዊ መንገድም ሄደዉ ችግር የሚያጋጥማቸው ኢትዮጵያውያንን መብት ለማስጠበቅ ቆንስላ እና ኤምባሲ ትኩረት ሰጥተዉ እንዲከታተሉ ቋሚ የስራ መመሪያ ተሰጥቷል ተብሏል።
የኢትዮጵያዉያኑ ክብር እና መብት ተጠብቆ እንዲቆዩ ከሚሲዮን መሪዎች በተጨማሪ ይህንን ጉዳይ ብቻ እንዲከታተሉ ዲኘሎማቶች መመደባቸዉን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ተናግረዋል።
ከማይናማር በተጨማሪ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዉ ነበሩ የተባሉ 26 ሺህ ዜጎችን በአምስት ወራት ዉስጥ ማስመለሱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ለስራ የተጓዙ ኢትዮጵያዉያን ከአንድ የስራ ቦታ ወደ ሌላ የስራ ቦታ ለመለወጥ ወይም ወደ ሀገር ለመመለስ እንዲሁም የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ እንዲሁም ከደሞዝ ጋር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነዉ ተብሏል።
በጅዳ፣ ሪያድ ፣አቡዳቢ፣ዱባይ እንዲሁም በኩዌት ቆንስላ ፅ/ቤት ይህንን ለማድረግ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ያልሄዱ እና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የስራ ስምምነት ያላደረገችበት የስራ ጉዞ ያደረጉ ዜጎች ለዘርፈ ብዙ ጥቃት የተዳረጉ መሆናቸዉ ተገልጿል።
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ዛሬ በእንደራሴዎች ምክር ቤት ተገኝተው ከአባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
